‹አርቲስቶቹ›ን ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን
አንድ ጆሮና ጊዜ የገጠሙለት ሰው ነበር አሉ፡፡ ሰውዬው የተማረው ትምህርት የለውም፡፡ ሁለት ችሎታ ግን ነበረው፡፡ ሲባል የሰማው እውነትም ይሁን ስሕተት ልቅም አድርጎ ይይዝና ሌላ ቦታ ሄዶ የተማረው ያህል ያንደቀድቀዋል፡፡ ሁለተኛው ችሎታው ደግሞ አፈ ጮሌ ስለሆነ ነገር በምላሱ ይቆላል፡፡ ያንንም ይኼንንም እያቆላመጠ ከተማሩትና ከተመራመሩት በላይ ከብሮና ታፍሮ ይኖራል፡፡ አንድ ቀን የማያውቀውን ቀለም ሲያዜም የሰሙት ሊቅ አፍረው አቀረቀሩ፡፡ እርሱ ግን ከዕውቀት የደነገለ ነበርና አልገባውም፡፡ በኋላ ቀረብ ብሎ ‹ደኅና ነዎት የኔታ› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹ደኅና ነህ›› ብለው ዝም አሉት፡፡ እርሱም ያላወቁት ስለመሰለው ‹አላወቁኝም መሰል መሪጌታ እኮ ነኝ› አላቸው፡፡ሊቁም ‹ዐዉቄሃለሁ› አሉት፡፡ እንዳቀረቀሩ፡፡ ‹ታድያ ምነው ካወቁኝ ከነ ማዕረጌ ሳይጠሩኝ ቀሩሳ› አላቸው፡፡ ‹አንተን አከብራለሁ ብዬ ሞያውን እንዳልሰድበው ፈርቼ ነው›› አሉት ይባላል፡፡
እኔም ‹እርቲስቶቻችን› የሚለው ቃል በትእምርተ ጥቅስ ያደረግኩት ሊቁ የፈሩትን ፈርቼ ነው፡፡ እንዳልተውባቸው ደግሞ ምን ብዬ እንደምጠራቸው ግራ ገብቶኝ፡፡ የአዲስ ዓመት ዋዜማውን መርሐ ግብር በዕለቱ ለማየት ስላልቻልኩ ቪዲዮውን ነው የተመለከትኩት፡፡ ሊነግሩን የፈለጉት ስለ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ፣ ስለ ሀገራችን ዕድገት፣ ስላለፈው ስኬታችን ቢሆንም እንኳን የቀረበው ዝግጅት ግን አደገች የምትባለውን ኢትዮጵያን የማይመጥን፣ ጥበብ ዞር ብላ ያላየቺው፣ ከንግግር ከፍ፣ ከፉከራ ዝቅ ያለ፤ ከፕሮፓጋንዳ ወረድ፣ ከዲስኩር ራቅ፣ ከድንፋታ ጠጋ ያለ ወለፈንዲ ሆኖ ነው የታየኝ፡፡
በሀገራችንኮ የልቅሶ ሥነ ሥርዓት እንኳን ወግ አለው፤ ጥበብ አለው፤ ትርዒት አለው፤ ፍሰት አለው፤ ድባብ አለው፤ ፈጠራ አለው፤ ርቀት አለው፣ ምጥቀት አለው፤ ደረጃ አለው፡፡ ይኼኮ ወግ የለው፣ ጥበብ የለው፣ ትርዒት የለው፣ ፍሰት የለው፣ ፈጠራ የለው፣ ደረጃ የለው፡፡ ድፍረት ብቻ፡፡ መሪዎቻችን ግን ለምንድን ነው የጥበብ አማካሪ የማይኖራቸው? ለምንድን ነው ጥበብን ከሚሰድቡ ሰዎች ጋር አብረው የሚቆሙት? ለምን ‹አርቲስቶቹን› እናከብራለን ብለው ሞያውን ይሰድቡታል? ይህቺ ሀገርኮ ሰማየ ሰማያት ደርሰው የመጡ፣ ድንጋዩን አቅልጠው ጥበብ የሚያፈልቁ፣ አራት ጸሐፊ አስቀምጠው አንድ አንድ ምዕራፍ እየነገሩ መጽሐፍ የሚያስጽፉ፤ መሰንቆ እንደ ሰው፣ ክራር እንደ ወፍ፣ በገና እንደ መልአክ የሚያናግሩ፤ ስንትና ስንት ጠቢባን ነበሩባት፡፡ ከሐይቅ ዳር የሸንበቆ ውዝዋዜ ተነሥተው ኅሊና የሚመስጥ አቋቋም የቀመሩ፣ እያዜሙ ሲሄዱ እንኳን ገበሬውን በሬዎቹን የሚያስደምሙ ጠቢባን ነበሩባት፡፡ እንዴት በጥበብ ሀገር በኢትዮጵያ ጠቢብ ነኝ የሚል ሰው ‹ከዕውቀት ርቆ፣ ንጽሕ ጠብቆ› በድፍረት ይኖራል? ይኼኮ ሀገርን መድፈር ነው?
አገሪቱ አድግበታልሁ፣ እመነደግበታለሁ፣ እለወጥበታለሁ፣ አሰላለፌን አስተካክልበታለሁ ብላ የደከመችበት የአምስት ዓመት ዕቅድ እንዴት በስሕተትና በድፍረት በተሞላ መድረክ እንዲታወጅ ይፈቀዳል? ይህንን ዕቅድ ባስታወስን ቁጥር ያንን ትልቅ ስሕተት እንድናስታውስ ለምን ተፈረደብን? ጥበብ ሳይሆን ድፍረት ትዝ እንዲለን ለምን ተገደድን?
ጥበብ ምንም ዓይነት ይዘት ይኑረው የጥበብን ደረጃ ማሟላት ግን አለበት፡፡ ልማታዊም ሆነ አብዮታዊ፣ ዲሞክራሲያዊም ሆነ አምባገነናዊ፣ ይዘቱ ይለያይ እንጂ የጥበብ ደረጃው ግን አንድ ነው፡፡ ጥበብም የሚያሰኘው የጥበቡ ደረጃ እንጂ የያዘው ይዘት አይደለም፡፡ እንዴት ምግብ ቤቶቻችን ለምግብ አሠራርና አቀራረብ የሚጨነቁትን ያህል ለሀገራዊ መድረክ የሚጨነቅ ይጥፋ? እንዴት የበያይነቱ ምግብ ያህል ጥበብ በሀገራዊ መድረክ ላይ እንጣ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ሀገራችን የራስዋ የሆነ ልዩ የዘመን አቆጣጠር አላት› ብለው ነገሩን፡፡ እውነት ነው ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሀገር ባህል ልብስ ለብሰው በነገሩን የሀገራችን ልዩ የዘመን ቆጠራ እንስማማለን፡፡ ‹አርቲስቶቹ›› ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳስተዋል፤ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር የላትም›› አሉን፡፡ ‹‹አዲስ ዘመንም የሚብተው እንደ አውሮፓውያን በእኩለ ሌሊት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የዘመን አቆጣጠራችን የተለየ ነው ያሉት ተሳስተው ነው›› አሉን፡፡ ኧረ እባክዎን ይጠይቁልን? ለምን ‹‹አርቲስቶቹ›› ጠቅላይ ሚኒስትሩን መቃወም ከፈለጉ የፖለቲካ ድርጅት መሥርተው በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ተቃዋሚ ፓርቲ አያቋቁሙም? ደግሞስ ለሌሎች ያልተፈቀደ እንዴት ለእነርሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የቀጥታ የዓመት በዓል ሥርጭት እንዲቃወሙ ተፈቀደላቸው? እንደ አሜሪካ የምርጫ ክርክር በቀጥታ ሥርጭት ተቃዋሚና መንግሥት በአንድ መድረክ የሚቀርቡ ከሆነማ እውነትም ሀገሬ ተለውጣለች?
የዛሬ ዓምስት ዓመት እንዲሁ ያለ ስሕተት ‹አርቲስቶቹ› ሲሠሩ ዐውቀው በድፍረት ሳይሆን ሳያውቁ በስሕተት ነው ተብሎ ታለፈ፡፡ ዘንድሮ እንዳይደገምም ብዙዎች በሚችሉት ሁሉ አስቀድመው አሳሰቡ፡፡ ሰሚም መስሚያም ጠፋና ስሕተቱ በባሰ ሁኔታ ተደገመ፡፡ ሰውና ሰይጣን የተለያዩትኮ ከስሕተት በመታረምና ባለመታረም ነው፡፡ ወደ ሥልጣኔው መሄድ ሲገባን ወደ ስ…
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ፤ አሁን ማንን እንመን? እርስዎን እንመን ወይስ ‹አርቲስቶቻችንን››?