አንድነት እና ልዩነት በፕሮፌሰር መስፈን ወልደማሪያም

“አንድነት በምናስብበት ወቅት ምንግዜም ሁለት እኩል ባለመብት ሰወችን እያሰብን መሆን አለበት፥፥ ልዮነት ራሱ የተፈጥሮ ባህሪ ነው፥፥ ላይ ላዩን ለሚመለከት አንድነት እና
ልዩነት ተቃራኒ ብቻ ናቸው፥፥ ጠለቅ ብሎ ለሚመለከት ግን ልዩነት የ አንድነት መሰረት ስለሆነ አንድነት ትርጉም እና ሃይል ሊኖረው የሚችለው ማናቸውም አይነት ልዩነት በመሃከላቸው እያለ ከላይ እንደተጠቀሰው በመብት እኩል በሆኑ ሰወች ዘንድ ብቻ ሲገኝ ነው፥፥ልዩነትን የማይፈቅድ አንድነት መካንነት እና ባዶነት ነው፥፥እንደተዳመጠ ጥጥ ፈሬውን አጥቶ የጊዜና የ አጋጣሚ መጫወቻ መሆን ነው…
ለ አንድ ለሚንቀሳቀስ ህያው ለሆነ 21ኛው ምት አመት ህዝብ አንድነቱ ልዩነቱን አቅፎ እንዲይዝ ማድረግ አለበት፥፥ ልዩነት የ አንድነት ህይወት ነው፥፥ ሁላችንም በየቤታቸን እንደምናውቀው ቢለዋ ለመሳል አንዱን በ አንዱ እናፋጫለን፥፥ አሌክትሪክ ሃይል የልዩነት ፈሬ ነው፥፥ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴ በልዩነት ላይ የተመሰረተ ነው፥፥ ልዩነት ግጭትን እንደሚያረግዝ እንደሚወልድ ጥርጥር የለውም፥፥ እንዲሁም ወግና ስርዓትን የያዘ ግጭት የማናቸውም አይነት እድገትና መሻሻል መሰረት መሆኑ ጥርጥር የለውም፥፥ ፈረንሳዮች ልዩነትን ያኑርልን የሚል የ አነጋገር ፈሊጣቸው የልዩነትን ደግ መልክ በሚገባ በመረዳታቸው ይመስለኛል፥፥ ፓለቲካ ማለትም በጉልበት ወይም በሃይል የማይጠቀም ደንብና ስርዓትን የሚጠብቅ ከልዩነት የሚመነጭ የስልጣን ግጭት ወይም ትግል ነው፥፥
አንድነት አላማ ነው፥፥ አንድነት በታሪክ፥ በስሜት፥በጥቅም እና በመተሳሰብ ለመጠንከር የታቀደ አላማ ነው፥፥ አንድነት በ አንድ ህግና በእኩል መብት ለመተዳደር የተሰጠ ፈቃድ ነው፥፥ አንድነት ሃይል ነው የሚባለውም የቁጥርን ብዛት እና አካላዊ ሃይልን ብቻ ለመግለጽ ሳይሆን ጠቅላላ ንብረትን፥አልኝታን ሙሉነትን፥ ኩራትን እና ትምክህትንም ለማመልከት ይመሰለኛል፥፥ ለማደግ፥ ለመበልጸግ ፥ ለማየል እና ህዝብነትን አስከብሮ ለመኖር ሲባል አንድነት ተፈላጊ ነው፥፥ አንድነት የልዩነት መገለጫ ነው፥፥ ተቃራኒ ሆኖ መቅረብ የለበትም፥፥ ልዩነት ከሌለ ስለ አንድነት የሚያወራ የለም፥፥ ልዩነት ስላለ ነው ስለ አንደነት የምናወራው፥፥ ልዩነት ስላለን ነው ለአንድነት መንገድ የምንፈልገው፥፥ አንድነትን አላማ አድርገን የምንቀሳቀሰው፥፥ ስለዚህ እንደ ሁለት የተለያዩ ያማይገናኙ፥ የሚጋጩ፥ የሚጣሉ አድርገን መመልከት የለብንም፥፥ አንዱ በአንዱ ውስጥ ያለ አንዱ አንዱን ያረገዘ ነው አንድነት እና ልዩነት፥፥ አብረን መሄድ አለብን፥፥”