ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ ስምንተኛ አልበሟን አውጥታለች
በአለማየሁ አንበሴ
የፍቅር አዲስ – “ምስክር”
ታዋቂዋ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ፤እንደ ብዙዎቹ ድምጻውያን ሁሉ ለብዙ ዓመታት ድምጽዋን ሳንሰማ ቆይተናል፡፡ 2007 ዓ.ም ሊሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩትና አዲሱ ዓመት ለመጥባት እየተሽኮረመመ ሲጠባበቅ እሷ በመሃል 8ኛ የዘፈን አልበሟን ይዛ ከተፍ አለች፡፡ ቢያንስ ፍቅር አዲስ በዚያው አልቀረችም ወይም ተስፋ ቆርጣ የሙያ ዘርፏን አለወጠችም፡፡ በዚህም ትደነቃለች፡፡ የፍቅር አዲስ የዘመን መለወጫ ስጦታዋ – “ምስክር; ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ታዋቂዋ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ፤እንደ ብዙዎቹ ድምጻውያን ሁሉ ለብዙ ዓመታት ድምጽዋን ሳንሰማ ቆይተናል፡፡ 2007 ዓ.ም ሊሰናበት ጥቂት ቀናት ሲቀሩትና አዲሱ ዓመት ለመጥባት እየተሽኮረመመ ሲጠባበቅ እሷ በመሃል 8ኛ የዘፈን አልበሟን ይዛ ከተፍ አለች፡፡ ቢያንስ ፍቅር አዲስ በዚያው አልቀረችም ወይም ተስፋ ቆርጣ የሙያ ዘርፏን አለወጠችም፡፡ በዚህም ትደነቃለች፡፡ የፍቅር አዲስ የዘመን መለወጫ ስጦታዋ – “ምስክር; ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ድምጻዊቷን የእንቁጣጣሽ እንግዳ አድርጓታል፡፡
አዲሱ አልበምሽ ምን አይነት ይዘት አለው? ዘመናዊ ነው ባህላዊ?
ዘመናዊ፣ ባህል ዘመናዊ እና ባህላዊ ዘፈኖች ናቸው የተከታቱበት፡፡
በግጥምና ዜማ እነማንን አሳተፍሽ?
ይልማ ገብረአብ፣ ተስፋ ብርሃን፣ አበበ መለሰ፣ ፀጋዬ ደቦጭ፣ ቢኒያሚር አህመድ፣ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም (በተለይ “እናት” የሚለውን ከአቤ ጋር በመተባበር የገጠመው ዮናስ ነው) የሙዚቃ አቀናባሪው ወንድሜነህ አሠፋ ራሱ አንድ ዜማ ሠርቶልኛል፡፡
ባለፈው ጊዜ ቴዲ ማክ ብቻውን ይመስለኛል አልበምሽን ያቀናበረው፡፡ አሁን ደግሞ የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ——
አዎ ወንድሜነህ አሠፋ ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ነው ያቀናበረው፡፡ ሃብታሙ የሻምበልና ብርሃኑ ሞላ ማሲንቆ ተጫውተዋል፣ ክራር ደግሞ አበበ መለሰ አለ፡፡ ሌላው አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ ነው፡፡ ሣክስ ሚካኤል መላኩ አለ፤ሊድ ጊታር ግሩም መዝሙር ነው የተጫወተው፡፡ ማስተሪንግና ሚክሲንግ—-በአጠቃላይ በዋናነት የሠራው ወንድሜነህ አሠፋ ነው፡፡
በአዲሱ አልበምሽ በተለየ የድምጽ አወጣጥና ቅላጼ እንደመጣሽ የሚናገሩ አድማጮች አሉ፡፡ በእርግጥ አልበሙን የተለየ ለማድረግ ሞክረሻል? የተቀየረው ነገር ምንድን ነው?
አዎ—- ስንሰራውም ጥሩ እንደሆነ አውቀነዋል፡፡ የሠራው ሰው ደስ ካለው፣ ሌላውም እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም፡፡ በፊት ቅኝቶች ብዙም ሠርቼ አላውቅም፡፡ አሁን ትዝታ ማይነር አለ፣ ትዝታ ማይነሩ “ባሻ ወልዴ” ነው መጠሪያው፡፡ ግጥሙን ይልማ ገ/አብ ነው የፃፈው፡፡ የድሮን ትዝታ የሚቀሰቅስና የሚያስታውስ ነው፡፡ አራዳ አካባቢ ፈርሶ፣ የምፈልገውን ልጅ አጣሁት የሚል አይነት ነው፡፡ ለሱ መጥፋት ምክንያት የሆነው የከተማው መስፋት ነው፣ የሚል ይዘት ያለው ቆንጆ ግጥምና ዜማ ነው፡፡ ግጥሙን ይልማ በደንብ ነው ያስጠናኝ፤ ተጨንቀንበት የሠራነው ስራ ነው፡፡ እንግዲህ በአጠቃላይ ዜማዎቹን ጥሩ አድርጌ እንድሠራ የተለመደ ድጋፉን ያደረገልኝ ባለቤቴ አቤ ነው፡፡
የአሁኑ አልበምሽ ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል?
እንግዲህ ስለ ፍቅር ብዙ ጊዜ አዚመን እናውቃለን፡፡ ይሄኛው አልበም ላይ ያለው የፍቅር አገላለፅ ግን ትንሽ ይለያል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው “በለው በለው” የሚለው ዘፈን፣ ዜማውን ለይልማ ስንሰጠው እንዴት አድርጎ አሳምሮ እንደሰራው ለኔም ይገርመኛል፡፡ ሌላው ቢኒያሚር የሰጠኝ “ባንተ ላይ” የሚለው፣ የትም ቦታ ሆኜ ጥፋት ባጠፋም ፍቅር አይናማ ነው፤የትም ቦታ ያየኛል የሚል ይዘት አለው፡፡ የሁሉም ግጥሞች ሀሳብ ደስ ይላል፡፡ “ምስክር” የሚለው ዘፈን እንዲሁ ጠንካራ መልዕክት ያለው ነው፡፡
ስለ “እናት” የዘፈንኩት ደግሞ የኔን ታሪክ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ዘፈን እናቴ ሳትሰማው እንዳትሞትብኝ እያልኩ ነው ያለፈችው፡፡ አሁን ታዲያ ውስጤ ይረበሻል፡፡ እኔና አቤ ይሄን ዘፈን ስንሰራ ሁሌ እናለቅስ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ከ6 ወር በፊት የእኔና የአቤ እናቶቻችን የሞቱብን በአንድ ቀን ልዩነት ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ሄደን ቀብረናቸው ነው የተመለስነው፡፡ እናቶች ለልጆቻቸው የከፈሉት መስዋዕትነት አለ፣ ትልቅ ሆነንም ቀልባቸው ከኛ ጋር ነው፡፡ ዘፈኑ ውስጥም ያለው ሀሳብ፣ #እንኳን እናት በህይወት እያለች ብታልፍም ምርቃቷ ይዞህ ይኖራል” የሚል ነው፡፡ አቤ በመጨረሻ የጨመረበት ስንኝ፣“በመጨረሻዋ ደቂቃ ስለ እናት ለማውጋት ምንም ጊዜ አይበቃም” ይላል፡፡ ዘፈኑም 5 ደቂቃ ነው፡፡ የእናትንም ውለታ ዘርዝሮ በ5 ደቂቃ ውስጥ መጨረስ አይቻልምና ይሄ የዘፈኑ ባህሪ ደስ ይላል፡፡ እኔ እውነቱን ልንገርህ እስካሁን ለእናቴ ሳልዘፍን መቅረቴ ይገርመኝ ነበር፡፡ በዚህኛው አልበሜ ባሳካውም እናቴ ሳትሰማልኝ በማለፏ ግን ይቆጨኛል፡፡
በአጠቃላይ አልበሙን ወድጄው የሰራሁት አስደሳች ስራ ነው፡፡ ይወደድልኛል ብዬም አምናለሁ፡፡ ዘመናዊና ባህላዊ ቅልቅል አልበም ነው፡፡ አንድ ዳንሶል ዘፈንም አለው፡፡ አቤ ነው የሰራልኝ፡፡ ርዕሱ “ስፈልግህ መጣህ” የሚል ነው፡፡
ከአልበም በኋላ ኮንሰርት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ እንዴት ነው ዕቅድሽ?
አዎ! መጀመሪያ ሲዲ ሪሊዝ አደርጋለሁ፡፡ መቼም ይሄን አልበም ፕሮዱዩስ ያደረግነውም የምናከፋፍለውም እኔና ባለቤቴ ነን፡፡ ግን በዚህ የአልበም ስራ ላይ ከኪነጥበብ ጎን ሁሌም የሚቆሙት ሞሃና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ አግዘውኛል፡፡ ስፖንሰር አድርገውኛል፡፡ እነሱ ባይደገፉት፣ ይሄ አልበም ለህዝብ መቅረብ አይችልም ነበርና ምስጋናዬ ወደር የለውም፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ድርጅቶች ባያግዙን፣ ሙዚቃን የመስራት ነገር የማይታሰብ ነበር፡፡
አልበሙ በህዝብ ዘንድ ያለው አቀባበል እንዴት ነው?
በእውነቱ በዚህች በሁለት ቀን ውስጥ ብቻ የነበረው አቀባበል አስደሳች ነው፡፡ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አመሰግናለሁ፡፡ በሁለት ቀን ውስጥ ባልጠበቅሁት መጠን ህዝቡ አልበሜን ገዝቷል፡፡ አመሠግናለሁ፡፡ በእውነቱ ህዝቡ አሁንም ከኪነጥበቡ ጐን እንደቆመ ያረጋጥኩበት አስደሳች አጋጣሚ ነውና አቀባበሉ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
በአዲሱ አመት ዋዜማና የበአሉ እለት አድናቂዎችሽ የት ሊያገኙሽ ይችላሉ?
ለዋዜማው ቀድሜ የያዝኩት ቤላቬርዲ ሆቴል ነው፡፡ እዚያ እገኛለሁ፡፡
ብዙ ጊዜ ለኮንሰርት ወደ ውጩ ስትሄጂ አትታይም፡፡ አሁንስ እቅዱ አለሽ?
እሱ እንግዲህ ስራው ነው የሚመራው፡፡ ስራ ከተሠራ—-ስራው ራሱ እያንኳኳ ይመጣል፡፡
አልበሙን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ፈጀብሽ?
አራት አመት ነው፡፡ ይሄም የሆነው ከጐኔ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስላደረጉልኝ ነው፡፡ በተለይ አቀናባሪው ወንድሜነህ አሠፋ፣ በትልቁ የማመሰግነው ሰው ነው፡፡ እስከ ሲዲ ህትመቱ ድረስ ያልተለየኝ፣ በጣም እውቀት ያለው፣ ሰው አክባሪ፣ ስራውን አፍቃሪ ሰው ነው፡፡ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡
