ስሜትና ፕሮፖጋንዳናን ከፖለቲካ የመደባለቅ አባዜና አደጋው Girma Bekele
ከሰሞኑ በአራት የትጥቅ ወይም ‹‹ ሁለገብ›› የትግል አማራጭ በሚከተሉ የ‹‹ነጻነት ›› ታጋይ ፓርቲዎች መካከል የትብብር ስምምነት ተፈርሞ የ‹‹ምስራች›› ተነግሮን ሳያበቃ ከተባባሪዎቹ የአንዱ /ደምኃት/ ሊቀመንበር ከትግል ሜዳው ‹‹መሸሽ›› ተከትሎ በዚሁ ፌስ ቡክ አምድ ላይ የሚጻፈው እጅግ አከራካሪና መረን የለቀቀ ግልብ ኃሳብ ስሜታዊነትንና ፕሮፖጋንዳን ከፖለቲካ ካለመለየት ወይም ከመደባለቅ ሌላ ስያሜና ትርጉም ስላጣሁለት እየተስተዋለ መባል አለበት በሚል…..
ትናንት የስምምነት ሰነዱ ተፈረመ ሲባል ተሸቀዳድመው ለመሪዎቹ የግል ባህሪይን ያካተተ ወደ ፍጹማዊነት የሚያቀርብ ‹‹አድናቆት›› እና መወደስ ሲያቀርቡ የነበሩትን ጨምሮ፣ በአድናቆትና ምስራች የፌስ ቡኩን አምድ በላይክና በኮሜንት ሲያጨናንቁ የነበሩ ልክ እንደ ‹‹ ሸሺው›› መሪ በቅጽበት ተገልብጠው መወድሱን በመወንጀል ሲገለብጡት ያስተዛዝባል፡፡ በዚህ ቢያቆሙ መልካም ነበር፤ አልፈው የመሪውን እርምጃ ከዘርና ከመንደር ጋር እስከማዛመድና በመቶዎች ኣመት ወደኋላ ወስደው ለመጋጣጠም ሲሞክሩ ማየት የበለጠ ያማል፡፡ በቅጽበት ‹‹ታጋይ›› ‹‹ሊቀመንበር›› አስተዋይ …. የሚሉትን የክብር ሞገሶችን ገፈው ከሃዲ፣ ባንዳ፣ አረም … የሚሉ ታፔላዎችን መለጠፍ ምን ይሉታል፡፡ይህ ህዝብን ከመናቅ ያለፈ ትርጉም ካለው ሊነግሩን /ሊያስረዱን ይገባል፡፡ ያለበለዚያ እነርሱ በፈለጉ ጊዜ የሚያወድሱት ሲጠሉ የሚያንቋሽሹት መርህ -የለሽ ምርቃትንም ሆነ እርግማን ለመስማት/ለማንበብ የምናባክነው ጊዜ እንደሌለን በግልጽ ሊነገር ይገባል፡፡ ከዚህ በርቀት ሄደው የትናንት የገዢው ፓርቲ አመራር/አባላት ልብ ገዝተው በስህተታቸው ተጸጽተው ውደ ተቃውሞ ትግሉ መቀላቀል የላባቸውም፣ ሲቀላቀሉም አትመኗቸው እየተባለ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት መ‹‹ግልጽ›› ነመገርና መነጋገር ካለበት ይህ ፍረጃና ጥርጣሬ የሚሰራው በትግራይ ክልል ተወላጆች ብቻ ነውን በሌሎች ክልሎችስ ይህ አልተስተዋልም? የኢትዮጵያ ህዝብ አበሳውን እያየ ያለው በማን ነው? የምንቃወመውስ ማንን ነው?…. እዚህ አገርቤት በአንጃ /መከፋፈል የተቋቋሙ አዳዲስ ፓርቲዎች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታዩ የፓርቲ አመራሮችንና አዳዲስ የተፈጠሩ ፓርቲዎች ላይ ለምን እንዲህ የመረረና የከፋ ሲጻፍ አናይም? …..
እኔ ጉዳዩን ከዚህ አሳልፌ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ወስነው በረኃ የገቡትን የተቀማጠለ ኑሮኣቸውን ትተው ‹‹ቤት ዱሬ ››ያሉትን መሪዎች ዓላማና ድርጅቶቻቸውን መርህና ተልዕኮ ካለመረዳት ትግሉን የሚጎዳ ተግባር ነው እላለሁ፡፡ የእነዚህን ፈጣን ፈራጆች ድርጊት/አስተያየት ግን እንደነርሱ ፈጥኜ አልፈርጅም፤ በእኔ በኩል ይህ ዓይነቱ አስተያየት የሚመነጨው ከስሜታዊነትና ፕሮፖጋንዳን ከፖለቲካ ለይቶ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው የሚል ግምት መውሰድን እመርጣለሁና የምንናገረውና የምንጽፈው ከስሜት የጸዳ እንዲሆን መጠንቀቅ እንዳለብን ፣ ይህ ካልሆነ ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚያስናሳና የምንጠብቀውን የለውጥ ቀን አርቀን እየወረወርነው እንደሆነ እንዲታወቅ ‹‹ ልብ ያለው ልብ ይበል›› እላለሁ፡፡ ለማንኛውም አሁንም ጊዜ ወስደን ስለሁኔታው እውነታውን ለመስማት ጊዜ እንውሰድ፡፡ ለእኔ እስከወዲያኛው እምነቴ ብቸኛው የዘላቂ ለውጥ መንገድ በብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ የሚያልፍ አካታች የሽግግር መንግስት በመሆኑ ይህን መንገድ አትዝጉብን እላለሁ፡፡ ደህና እደሩ፤ በቸር ያገናኘን//