የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ: ፈቃዷ ተሰርዞ ከመዘጋቷ በፊት መንበረ ፓትርያርኩ እንዲታደጋቸው ምእመናኑ ጠየቁ

  • “እንደ ረዳት ጳጳስ ነኝ” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ሕጋዊ ህልውናዋን ለአደጋ አጋልጠውታል
  • ምደባቸው፣ ከመንግሥት ሕግ እና ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ጥያቄ ተነሥቶበታል
  • ለስምንት ዓመታት የሒሳብ ሪፖርት ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አልቀረበም

በመላው ደቡብ አፍሪቃ ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በደቡብ አፍሪቃ መንግሥት አትራፊ ባልኾኑ ሕዝባዊ ድርጅቶች ዐዋጅ(NPO) ሕግ መሠረት እ.አ.አ በ26/01/1999 ሕጋዊ ፈቃድ አግኝታ፣ በቁጥር 006-083 መሠረት የተፈቀደላት እና የተመዘገበ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት አለመቅረቡ

ይህ ሲኾን ታድያ፣ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቷን ለደቡብ አፍሪቃ የገቢዎች ቦርድ (South Africa Revenue Service) ማሳወቅ ይኖርባታል፡፡ ይኹንና ላለፉት ስምንት ዓመታት ምንም ዐይነት የሒሳብ ሪፖርት አልቀረበም፡፡ ስለ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቢቆይም አንዳችም ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ፈቃዳችን ተሰርዞ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳትዘጋ ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀናል፡፡

ይህን ስጋታችንንና ሌሎች መሠረታዊ ችግሮቻችን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት አቅርበን ነበር፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የጉዳዩን አሳሳቢነት አምኖበት በጥቅምቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ከተነጋገረበት በኋላ፣ የሒሳብ ሪፖርቱ በአስቸኳይ ተሠርቶ ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ፤ በውጭ ኦዲተርም እንዲመረመር ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ይኹንና ትእዛዙ ከተላለፈ በኋላ ምንም ዐይነት ሒሳቡ ተሠርቶ፣ ሪፖርቱ ባለመቅረቡ ውሳኔው ተፈጻሚ መኾን አልቻለም፤ የውጭ ኦዲቱም አልተከናወነም፡፡

አጥቢያን ለማስተዳደር ያልቻሉት አባት የሀገረ ስብከቱም ሥራ አስኪያጅ መኾናቸው

ሌላው ዐቢይ ችግራችን፤ ከደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ከጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቆሞስ አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ በመኾን ተመድበዋል፤ ነገር ግን እኚኽ አባት ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኑን ለኹለት ዓመታት ባስተዳደሩበት ወቅት፣ በነበረባቸው የአስተዳደር ብቃት ማነስ ሳቢያ በራሳቸው ፈቃድ ሓላፊነታቸውን ትተው ወደ አገር ቤት ተመልሰው ነበር፡፡

ይህ መኾኑ እየታወቀ አንድን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለማስተዳደር ያልቻለን አባት፣ የሀገረ ስብከቱም ሥራ አስኪያጅ ኾነው መመደባቸው ችግሮቹ የበለጠ እንዲባባሱ አድርጓል፡፡ ለኹለት ዓመት ባስተዳደሩበት ወቅት ለስምንት ዓመታት የተረሳውን የሒሳብ ሪፖርት ለቅዱስ ሲኖዶስ አላሳወቁም፤ ከውሳኔ ቃለ ጉባኤው ለማረጋገጥ እንደሚቻለው፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቤት ብሎ ኹኔታውን ያሳወቀው አኹን በሥራ ላይ ያለው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው፡፡

አቅመ ቢሱ አስተዳዳሪ እና ሥራ አስኪያጅ እንደ ረዳት ጳጳስ ነኝ” አሉን – “ረዳት ጳጳስ”???

ቆሞስ አባ ጥዑመ ልሳን፣ ለኹለተኛ ጊዜ የመጡት በሦስት ወር የጉብኝት ቪዛ ነበር፡፡ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት በጉብኝት ቪዛ ሥራ መሥራት እንደማይቻል ቢነገራቸውም በማናለኝነት ሲሠሩ ተገኝተው በሚመለከተው የመንግሥት አካል(Home Affairs/Immigration) ክሥ መሥርቶባቸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት፣ በክሥ ቁጥር ጄ.ኤች.ቢ.337/2015 መሠረት የጉብኝት ጊዜአቸውን ጨርሰው ወደ አገር እንዲመለሱ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ወደ አገር ቤት ተመልሰው ነበር፡፡ ለ Waiver request ምላሽ ከአገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት

በቅርቡ ደግሞ፣ ለአምስት ዓመት እንደ “ረዳት ጳጳስ” /Deputy Bishop/ እንድሠራ የሥራ ፈቃድ ተሰጥቶኛል፤ በማለት ለሦስተኛ ጊዜ ተመልሰው መጥተዋል፡፡ “የቀጠርዎት ማን ነው? ማስረጃዎንም ያሳዩን?” ብለን ስንጠይቃቸው፤ “አላሳይም፤ ነገር ግን ከቅዱስ ሲኖዶሱ ተፈቅዶልኝ የአምስት ዓመት የሥራ ፈቃድ ተሰጥቶኛል፤” አሉን፡፡ በፓስፖርታቸው ላይም Deputy Bishop የሚል ፈቃድ ያሳያል፡፡ ጥያቄአችን፤ አባ ጥዑመ ልሳን በርግጥ Deputy Bishop ተብለው መጠራት ይችላሉ ወይ? ይህ ዐይነቱ ሢመት እና አሠራር በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያናችንና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ አለ ወይ?

የ“ረዳት ጳጳሱ” ጦስ የከፋ የሕግ ርምጃ ሳያስከትል መንበረ ፓትርያርኩ ይታደገን

ከደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የሥራ ፈቃድ ሰጪ አካል ባገኘናቸው ማስረጃዎች፣ የቀድሞው የፕሪቶርያ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ መርሻ ታደገ፣ የሀገረ ስብከቱ የበላይ ሓላፊ መስለው በመፈረም ለአባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ትኩ “ጳጳስ” ናቸው ብለው በማመልከት የሥራ ፈቃዱ እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን፣ ራሳቸው ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ፣ በ2006 ዓ.ም. የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያኑ የአስተዳደር ሓላፊነታቸው ተነሥተው በሌላ እንዲተኩ ውሳኔ የተላለፈባቸው መኾናቸው ነው፡፡

የመንግሥትንም ኾነ የቤተ ክርስቲያናችንን አሠራር ባልተከተለ መልኩ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ተግባር የሥራ ፈቃድ ሰጪው አካል ስለደረሰበት፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ለአባ ጥዑመ ልሳን አዳነ ትኩ ተሰጥቷል ስለተባለው ጵጵስና ማስረጃ እንዲያቀርቡ አመልካቹን ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ መርሻን ጠይቋል፡፡

የሀገሪቱን ሕግ በውል ለሚረዳ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሊወሰድ የሚችለው የሕግ ርምጃ የከፋ ሊኾን ይችላል፡፡ ችግሩ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ፣ ኹለቱም አባቶች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ብንመክርም ብናስመክርም ካለመስማታቸውም በላይ ይባሳችሁ ብለው ምእመኑን የሚከፋፍል እኩይ ድርጊት እየፈጸሙ በመኾኑ፣ መንበረ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና የሚታደግ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠን በመድኃኔዓለም ስም እንጠይቃለን፡፡ ለማስረጃ ይኾን ዘንድ ለሥራ ፈቃድ ማውጫ የተጠቀሙባቸውን ሰነዶች በከፊል እና የፓስፖርታቸውን ኮፒ አያይዘን ልከናል፡፡

ኃያሉ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላሙን ያውርድልን፡፡ አሜን፡፡

የመረጃ ማስተካከያ፡-

የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ዜና ዕረፍትን አስመልክቶ በቀረበው ዘገባ፣ ብፁዕነታቸው ባለፈው ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የደቡብ አፍሪቃ ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመድበው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይኹንና የብፁዕነታቸው ጉዞ የምደባ ሳይኾን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለአጭር ጊዜ የተሰጣቸው ተልእኮ እንደነበር የሀገረ ስብከቱ ምእመናን ከላኩት መረጃ ተረድተናል፡፡ በመኾኑም መረጃው በዚሁ መሠረት እንዲታረም ከታላቅ ይቅርታ ጋር እንጠይቃለን፤ ምእመናኑንም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕነታቸው ለሕክምና በመጡበት ወቅት ጎብኝተናቸዋል፡፡ ዕድሜ እና ብርታት ሰጥቷቸው ተመድበውልን ቢመሩን ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡

ብፁዕነታቸው ከሕክምናው ባሻገር ወደ ደቡብ አፍሪቃ የመጡት ግን፣ በወቅቱ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የመረረ ሐዘን እንዲያረጋጉ፤ አጽናንተውም እንዲባርኩ እንደነበር በቁጥር 233/422/2007 በቀን 17/09/2007 ዓ.ም. ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ከተላከው ደብዳቤ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ይህም በ28/04/2015 ለቅዱስ ሲኖዶስ በደብዳቤ በጠየቅነው መሠረት ለብፁዕ አባታችን የተሰጣቸው ተልእኮ ሲኾን በነበራቸው አጭር ጊዜም በብቃት ተወጥተውታል፡፡