የዕብድ ኀሙስ
የታደለ አገልጋይ የበላዩን ከስሕተት ይጠብቃል፡፡ ‹አማካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ› እንዲሉ፡፡ አክዓብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት(871-852 ቅልክ) የነበረ ንጉሥ ነው፡፡ የሚስቱን የኤልዛቤልን ቃል ሰምቶ ነቢያተ እሥራኤልን ሊያጠፋ ተነሣ፡፡ ብዙዎች በሰይፉ ጠፉ፣ ብዙዎችም አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ በአክአብ ቤተ መንግሥት ውስጥ ግን አብድዩ የተባለ ልብ ያለው ባለሟል ነበር፡፡ ንጉሡን ከጥፋቱ ማዳን ቢያቅተው በንጉሡ ስሕተት ባለመስማማቱ 100 ነቢያትን በሁለት ዋሻ ውስጥ ደብቆ የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየመገበ ከአክዓብ ጥፋት አድኗቸው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ነቢያት የእሥራኤል የዕውቀትና የእምነት መሪዎች ናቸው፡፡ የእሥራኤል ባህል፣ ታሪክ፣ ትውፊትና ዕውቀት የሚተላለፈው በነቢያት ትውፊት ነበርና፡፡ ነቢያቱን ማጥፋትም ሀገሪቱን ያለ ታሪክ፣ ዕውቀት፣ ባህል፣ ሥርዓትና ቅርስ ማስቀረት ነበር፡፡ ለዚህ ነው አብድዩ የንጉሡን ዐዋጅ ማስቀየር ቢያቅተው ነቢያቱን ደብቆ እየመገበ ሀገሪቱን ከከባድ ጥፋት የታደጋት፡፡
ይህንን ሥራውን ማንም እንዲያውቅለትም፣ እንዲያውቅበት አላደረገም፡፡ ዓላማው ዕውቅና ጥቅም ማግኘት ሳይሆን ሀገር ማትረፍ ነውና፡፡ የንጉሡን የጥፋት ዐዋጅ ማስቀረት አልችልም ብሎ ዝም አላለም፤ ነገር ግን በዐቅሙ የሚችለውን በማድረጉ በእውነትም እሥራኤል የዕውቀት፣ የታሪክና የባህል ጥፋት እንዳይገጥማት አደረገ፡፡ ያን ክፉ ዘመንም አሻገራት፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የበላዮቻቸውን ጥፋት ከማስቀጠል ይልቅ በራሳቸው ዐቅም የሚችሉትን መልካምነት የፈጸሙትን ብቻ ሳይሆን፣ ‹ትእዛዝ ከበላይ እግር ወደ ላይ› ከማለት አልፈው አለቆቻቸውን ከጥፋት የታደጉ የበታች አገልጋዮችንም ታሪክ እናገኛለን፡፡ የሶርያው ንጉሥ የቤን ሐዳድ 2ኛ የጦር አዛዥ ንዕማን ወደ ሰማርያ መጥቶ ነቢዩ ኤልሳዕን ባገኘው ጊዜ ከለምጽ ሕመሙ ይድን ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲጠመቅ መክሮት ነበር፡፡ ንዕማን በዚህ ደስተኛ አልሆነም፡፡ ተቆጥቶም ወደ ሀገሩ ሊጓዝ ተነሣ፡፡ አንደኛው ባለሟሉ ግን ለጦር አዛዥ የሚገባ ምክርን መከረው ‹‹ጌታዬ ምን ቸገረህ፣ ውረድና ተጠመቅ፤ ከተፈወስክ እሰዬው፤ ክልሆነ ግን ከሰማርያ ጋር የምንዋጋበት ምክንያት እናገኛለን››፡፡ የጦር አዛዡ ንዕማን በዚህ የወታደሩ ሐሳብ ተስማማ፡፡ ዮርዳኖስ ወርዶም ተጠመቀ፡፡ ዳነም፡፡ አገልጋዩም አዛዡን ከጥፋት አዳነው፡፡ ንዕማንም ሊፈጽመው በነበረው ስሕተት ተጸጸተ፡፡
በታሪክ ውስጥ ግን እንደ አብድዩና የንዕማን ወታደር የበላዮቻቸውን ስሕተት የማይደግሙ ወይም አለቆቻቸውን ከስሕተት የሚታደጉ የበታቾች ብቻ አይደሉም የነበሩት፡፡ ያሉትም፡፡ አለቆቻቸው ያላሰቡትን ጥፋት በመሥራት አለቆቻቸውን ያስደሰቱ መስሏቸው ሀገር ያጠፉም አሉ፡፡ ‹ከለማበት የተጋባበት› እንዲሉ፡፡ ‹ጌታዬ እንዲህ ባደርግለት ይደሰታል› ብለው በማሰብ ከልክ እያለፉ፣ የሌለ እየጻፉ፣ ያልታዘዘ እየፈጸሙ ግፍ ሲሠሩ የኖሩ፡፡ ያዘው ሲባሉ ጣለው፤ እሠረው ሲባሉ ግደለው፤ አምጣው ሲባሉ ስቀለው፤ ተቀበለው ሲባሉ ቀማው የተባሉ እየመሰላቸው ሕግ ሲያልፉ፣ ገደብ ሲጥሱ የኖሩ አሽከሮችም ነበሩ፡፡ አሉም፡፡
በሀገራችን ከነነዌ ጾም በኋላ የሚመጣው ኀሙስ ‹የዕብድ ኀሙስ› ይባላል፡፡ ቀኑ አለቆቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ በግፍ ላይ ግፍ፣ በክፋት ላይ ክፋት፣ በመከራ ላይ መከራ፣ በቅጣት ላይ ቅጣት፣ በእንግልት ላይ እንግልት በሕዝብ ላይ ለሚጨምሩ አሽከሮች መታሰቢያ ነው፡፡ እንደ አብድዩና የንዕማን ወታደር ‹እስኪ ነገሩን እንየው› ከማለት ይልቅ ጭካኔ፣ ግፍ፣ ቅጣትና በደል አለቆቻችንን ይበልጥ ያስደስትልናል ብለው ለሚያስቡ አሽከሮች መታሰቢያ፡፡
በሸዋው ንጉሥ አስፋ ወሰን ዘመን ንጉሡ ለዘመቻ እየተጓዙ በደብረ ብርሃን አልፈው አንጎለላ ደረሱ፡፡ ይህን ጊዜ ጎሜ ጎሹ የተባለ አሽከር አስፋ ወሰንን በምን ላስደስታቸው ይልና በራሱ ጊዜ ዐዋጅ ያውጃል (‹መቼም ንጉሡ ሥራ በዝቶባቸው ረስተውት ነው እንጂ ይህን ሳያውጁ አይቀሩም‹ ብሎም ይሆናል)፡፡ ‹‹በዚህ ሀገር ያለውን ሰው ሁሉ አንድ ሳታስተርፍ በለው ብለውሃል› የሚል ዐዋጅ፡፡ ሠራዊቱም የንጉሥ ዐዋጅ መሰለውና አእምሮው ትቶ ጉልበቱን በማሠራት ፈረሱን እየጋለበ ከበሬሳ እስከ አያብር፣ ካንድ ዐርብ እስከ መገዘዝ የነበረውን ሀገር ሁሉ በነነዌ ፋሲካ ዕለት ኀሙስ ዘምቶበት ዋለ፡፡ ሕዝብ አለቀ፣ ተሰደደ፣ በሀገርም ላይ መከራ ወረደ፡፡ ንጉሡም የሆነውን ሲሰሙ አዝነው ጎሜ ጎሹን ‹‹ማን አዞህ ዐወጅክ?› ቢሉት ‹‹ጌታዬ መቼም የዘመትነው ለዚህ ነው ብዬ ነው›› አለ ይባላል፡፡ ቃላዊ መረጃዎች እንደሚነግሩን አስፋ ወሰን ጎሜ ጎሹን ቀጥተውና አሥረው ከዘመቻ ወደ አንኮበር ላኩት፡፡
ሕዝቡም ‹‹ወይ ጎሜ ጎሹ ወይ ጎሜ ጎሹ
በድፍን ሀገር ዕዳ ነስናሹ› ብሎ ገጠመበት፡፡ ቀኑም ‹የዕብድ ኀሙስ ተባለ›› ይላሉ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት የዳግማዊ ምኒሊክ ታሪክ ላይ፡፡
የቻለ እንደ ንዕማን ወታደር አለቃውን ከስሕተት ይታደጋል፣ ከጥፋት ያድናል፤ ያልቻለም እንደ አብድዩ የበላዩን ስሕተት ማረም ቢያቅተው እርሱን ስሕተቱ ይዞት እንዳይጠፋ ራሱን ከስሕተቱ ያድናል፣ ከጥፋቱም ይጠብቃል፡፡ ለሌሎችም የመዳኛ ምክንያት ይሆናል፡፡ እንደ ጎሜ ጎሹ ‹አለቃየ ይህን ባጠፋለት ደስ ይለዋል› ብሎ የሚያስብ አሽከር ግን ‹በድፍን ሀገር ዕዳ ይነሰንሳል›፡፡ ጎሜ ጎሹዎች ትንሽ ቀዳዳ ካገኙ አስፍተው ስለሚጓዙባት አለቆቻችን ምንም አይሉንም ብለው ያስባሉ፤ እንዲያውም አብልጠው በማሰባቸው እንደሚሸለሙ ያምናሉ፡፡ ጎሜ ጎሹዎች የአለቆቻቸውን በር በመዝጋት፣ እንደ አለቆቻቸው ሆነው በመወሰን፣ ቁጣውን ወደ ጥፊ፣ ጥፊውን ወደ ግርፊያ፣ ግርፊያውን ወደ ግድያ በማሳደግ የተሻለ አፈጻጸም ለማሳየት ይተጋሉ፡፡
አብድዩና የንዕማን ወታደር የበዙላት ሀገር ዶፍ ዝናብን በጣራ፣ ካፊያን በጥላ እንደሚከለል ሰው፣ ከላይ የሚመጣውን ጥመት አቃንተው፣ የሚወርደውን ጥፋት አርመው፣ ቁጣውን በትዕግሥት፣ መዓቱን በምሕረት ስለሚለውጡት ድፍን ሀገር ዕዳ ሳይሆን ፋታ ያገኛል፡፡ ጎሜ ጎሹዎች ሲበዙ ግን በበሆር ላይ ቆረቆር፣ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፣ በዕዝል ላይ እንጥልጥል፣ በራቁት ላይ ብርድ፣ በጥማት ላይ ንቃቃት ይሆናል፡፡ ሕዝቡ እንዳለው ጎሜ ጎሹዎች ‹በድፍን ሀገር ዕዳ ይነሰንሳሉ›፡፡ እነርሱ ለዕለቱ የሚያገኙትን ሹመት ሽልማት፣ ጉርሻና ድርሻ እንጂ አለፍ ዘለቅ አድርገው የችግሩን ውጤት አያስቡትምና ጎሜ ጎሹዎች የሚያመጡትን ዕዳ ሀገር ስትከፍለው ትኖራለች፡፡
በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያችን ጎሜ ጎሹዎች ሳይሆን አብድዩዎችና የንዕማን ወታደሮች የሚበዙባት ሀገር ትሁን፡፡