የተደበቁ ሚስቶች (አደፍርስ ተሰማ)

የአንዳንድ ሃበሾች ህይወት እጅግ ከመጣመሙ የተነሳ ለማቃናት እጅግ አስቸጋሪ ነው። መሰረቱ በውሽት፤ በማታልል፤ ያለቅጥ በእዳ በመዘፈቅ፤ የሁለት ዓለም ኗሪ እየተሆነ ልብ ዋሽንግተን ቂጥ አዲስ አበባ ነው። ሰው የሚታወቀው በስሙ ሳይሆን በሚነዳው መኪና፤ በገዛው ቤት፤ በሚጠጣው የመጠጥ አይነት ነው። ከከፋም እንዴ ያ ጫት የሚቅመው እንዲህ ያልች ልጅ የሚያወጣው ይባልለታል። አውጪና ተወጪ ስም የሌላቸው ይመስል። እንጀራ ቀርቦ በሃሳብ መነታረክ፤ የሰውንና የራስን ሰላም ማደፍረስ ሙያ አርገው የያዙ ቁጥራቸው ብዙ ነው።

በቅርቡ አንድ በሰሜን አሜሪካ የሚኖር የልጅነት ጓደኛዬ ሃሎ ይለኝና የሚከተለውን ታሪክ ያጫውተኛል። ሰማ እባክህ እንድ ጉድ ሰምቼ ሰለ አስማማው ይለኛል። እንዴ የምን ጉድ? ሚስቱ ሃገር ቤት ሂዳ ሌላ ሚስት በናዝሬት እንዳለው ሰማችና ልጅትዋን አፈላልጋ በመገናኘት በፎቶና በፊልም (ቪድዮ) የተደገፈ መረጃ ይዛ በመምጣት ክስ መስርታበት በመርበትበት ላይ ነው አለኝ። ወየው ጉድ ሰው አብዶአል እንዴ? ባለንበት ዘመን ተደብቆ የሚቀር ምን ነገር አለ? ዛሬ የስው አጽም ቆፍሮ ማውጣትና ከቆመ ዘሙድ ጋር ዲነኤ እያመሳከሩ እያቀረቡ አይደለምን? ታዲያ እንደዚህ ያለ ብዙ መረጃ ያለበትን ነገር ደብቆ ለመያዝ መሞከር “ዝሆን የታለ ቢሉት ድካውን አሳዬኝ” እንዳለው ፌዘኛ መሆነ ነው። አበጀች አልኩት። ልቤ በወይዘሮዋ ተግባር ደስ ብሎት።

ተው አንተ ደግሞ የምን አበጀች ነው። ዝም ብላ ብታልፈው መልካም ነበር አለኝ። እንዴ አንተ ያምሃል መሰል አልኩት እንደመናደድ በማለት። እሱም የድምፁን ቃና ለወጥ አርጎ መናገር ጀመረ። ታስታውሳለህ? ምኑን አለኝ ለማወቅ ቸኩሎ። አንተ ከናኒ ጋር እያላቹህ የእኔን ምክር ብትሰማ ኑሮ አሁን የተለየ ህይወት ይኖርህ ነበር አልኩት። የእኔንና የናኒን ነገር ከዚህ ጋር ምን አገናኘው አለኝ በቁጣ መልክ። ይገናኛል ረጋ በል ላስረዳህ አልኩት በህሊናዬ ያ ልጆች ያድቦለቦሉት የጭቃ  በይ የመሰለው አይኖቹ ሲያጉረጠሩጡብኝ እየታሰበኝ። ይጠጣል፤ ያጨሳል፤ ይቅማል እረ ስንቱ። አንተ ናኒን መማታት በታቆም ኑሮ እስርቤት አትገባም፤ ፍችም አይመጣም ነበር። ያኔ እኔ ተው ችግር ላይ ተወድቃለህ ስትባል አሻፈረኝ በማለትህ የደረስብህን መከራ ከምትነግረኝ ጋር የሚያገናኘው የችግሩ መነሻ ወንድ ከመሆኑም በላይ ሁለታቹህም ውሸታሞች ሰለሆናቹህ ነበር። አንተ በጀርመን ውሽማ ይዘህ ቀኑን ሁሉ ኮምፒውተርና ስልክ ላይ ተጥደህ ስተውል ቢዝነስ ልጀምር ነው እያልክ ናኒን ታታልላት ነበር። ስትጋለጥም የቀረህ ምርጫ መደባደብ ነበር። ያኔ ለምን መታሃት አንተ ጤነኛ ሰው አይደለህም ስልህ ችላ ማሳለፍ ነበረባት ነው ያለክኝ። አሁንም የምትነግረኝን ታሪክ እኔ ደግፌ አበጀች ስል ተው ትላለህ። ተገቢ አይደለም። ወሪያችን በዚሁ አብቅቶ ቴሌፎኑን ዘጋን።

ያልሆነውን ነን፤ የሌለን አለን በማለት ራሳችን እያታለልን ሳናውቀው ከወጥመድ የገባንና መውጫው ጠፍቶን በር የተዘጋብን ስንቶች ነን። ሳንወደው ለጥቅም በለን በማይረባ ፍቅር ተቆራኝተን በማይጣፍጥ የኑሮ መሰናክል ውስጥ ሆነን ድረሱልኝ የምንለው በማጣት ያለምርጫ የሚኖር የሃበሻ መዓት ቤቱ ይቁጠረው። ድላው ፍጥጫው ስድቡ አያድርስ ነው። የውሽቱ በዛት እንደ ቀኑ የራሱ ገጽታና ቀለም አለው። ሰለጠንኩ ተምሬአለሁ ለሃገሬና ለህዝቤ እቆረቆራለሁ እያለ የልጁችን እናት በቡጢ የሚነርተው ሃበሻ በተግባሩ ህግ ፊት ሊቀርብ ይገባል። እናንተ ለዘብተኛ ሴቶችም ተደብድቦ መሳም ይቅርባቹህ። ለመብታቹህ ቁሙ። ከእናንተ በስተጀርባ የተደበቁ የሩቅና የቅርብ ሚስቶችንና ፍቅረኞችንንም ፈልፍላቹህ በማውጣት የሃበሻው ወንድ አንካሳ ሃሳብ ሊያቆም የሚያስችል እግር እንደለሌው አሳዩት። ጀግናዋ እህታችን በቪዲዮ የቀረጽችው የሰውን ምስል ብቻ አልነበረም። የተላኩ የገንዘብ ደረስኝ፤ በሁለተኛው ሚስት ያለ የጋብቻ ወረቀትና ፎቶ እንዲሁም የጎረቤት ምስክርነትን ጭምር ነበር። ጀግናዋ ያን እንደ ሙጫ ተጣብቆ ይሽቀጡ ማራገፊያ ያረጋት የነበርውን ደም መጣጭ ያሳፈረችው በስማ በለው አይደለም በመረጃ እንጂ። አጭበርባሪ ወንዶችና ሴቶች መነገዳቹህን አቁሙ። ይህ ታሪክ ትምህርት ይሁናቹህ።