አንድ ሺሕ ልኡካን ዛሬ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ይወያያሉ፤“ከዋነኛ ትኩረቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በመነሣት ርምጃ ይወሰዳል”/ሚኒስትሩ/
- የዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ውይይቱን በቡድናዊ አካሔድ የመቆጣጠር ሙከራ ተነቅቶበታል
- አማሳኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በመወንጀል መሸፈን እንደማይችሉ ሚኒስትሩ አሳስበዋቸዋል
- “ስለ መልካም አስተዳደር ከሚደረሰው መግባባት በመነሣት መንግሥት ርምጃ ይወስዳል”
ከአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ከማኅበረ ካህናት፣ ከሰባክያነ ወንጌል፣ ከሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች እና የሀገረ ስብከቱ አንድነት አመራሮች ጋር በተናጠል ሲወያይ የቆየው፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የማጠቃለያ ውይይት ያካሒዳል፡፡
የመርሐ ግብሩን አስተባባሪዎች ጨምሮ ከ800 – 1000 ያኽል ተወካዮች በውይይቱ እንደሚሳተፉ ተገልጧል፡፡ ከተሳታፊዎቹ የሚበዙት ከ169 የሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት የተውጣጡ አምስት፣ አምስት ልኡካን ሲኾኑ እነርሱም አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች እና የአንድነቱ ተወካዮች የሚገኙበት ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር ሓላፊዎችም በውይይቱ እንደሚሳተፉ ተጠቅሷል፡፡
ልኡካኑ፣ “ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል” በሚል በሚኒስቴሩ የተለዩ ናቸው ተብሏል፡፡ ይኹንና የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት እና የምእመናን ተወካዮች ቀጥተኛ ተሳታፊ አለመኾናቸው ጥያቄ አስነሥቷል፡፡ የካህናት ተወካዮቹም “የንስሐ ልጆች ያላቸው” ከሚል በስተቀር በአመራረጣቸው በርግጥም ካህናቱን ሊወክሉ የሚችሉ ስለመኾናቸው አለመረጋገጡ ተመልክቷል፡፡

ከዛሬ ነሐሴ 29 ቀን ጠዋት 2፡00 ጀምሮ ለኹለት ቀናት በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የስብሰባ አዳራሽ የሚካሒደው ውይይት፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲኾን እነርሱም፡- በሰላም አብሮ የመኖር የቆየ ወርቃማ ተሞክሯችንን እንዴት ማስቀጠል እንችላለን? አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በውስጣችን አለ ወይ? እንዴትስ መታገል እንችላለን? የቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ሥርዐት ይገኙበታል፡፡ መድረኩ÷ ባለፉት ጊዜያት በተናጠል ውይይት የተካሔደባቸውን ጉዳዮች በጋራ መግባባት በማጠቃለል እና ሰፊ ጥናት በማድረግ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡
የውይይት መርሐ ግብሩን ለማመቻቸት እና አቅጣጫ ለማስያዝ፣ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በራሳቸው የመረጧቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡
የማጠቃለያ መድረኩ፣ 1000 ያኽል ተሳታፊ ልኡካኑ በ10 ቡድኖች ተከፍለው በቡድን የሚወያዩበት መርሐ ግብርም እንዳለው ታውቋል፡፡
የውይይት ሒደቱንና የጋራ አቋሞችን ተቆጣጥረው ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያሰቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በዛሬው ምክክር፣ እነኃይሌ ኣብርሃንና ዘካርያስ ሐዲስን የመሳሰሉ አማሳኞችን በአካል ይዘው በመቅረብ ጭምር የቡድን ውይይቱ መሪዎች እንዲኾኑ ሐሳብ ከማቅረብ አልፎ ደልዳይም ኾነው ታይተዋል፡፡
የቡድን ተወያዮች(በተለይም በአማሳኞቹ አለቆች የቅጣት፣ የእገዳ እና የዝውውር ተጽዕኖ የሚደረግባቸው ካህናት) ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይሰጡ ለማሸማቀቅ የታሰበበት ይኸው ስልት፣ የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚኾን በሚጠበቀው የሙስና ጉዳይም ከአለቆቹ ተጠርጣሪዎች እንዳሉበት በመጠቆም ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡
በሚኒስትሩ ዶክተር ሺፈራው ተክለ ማርያምም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ አማሳኞቹ ስለ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በሚደረገው ውይይት እንደለመዱት ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለው ራሳቸውን በመሸፈን የውይይቱን ሒደት እና የጋራ አቋም ለመቆጣጠር ተዘጋጅተው ከኾነ፣ “ጊዜአችኹን አታጥፉ” ብለዋቸዋል – ሚኒስትሩ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ፣ ዋናው የውይይቱ ትኩረት በቤተ ክርስቲያን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ እንደሚኾንና መንግሥት በቀጣይ የሚወስዳቸው ርምጃዎችም በዚኽ ዋነኛ ነጥብ ላይ በሚያዘው የጉባኤው የጋራ መግባባት ላይ እንደሚመሠረት ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአድባራቱ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ጥናታዊ ሪፖርት፣ አስከትሎ ባመጣው የአማሳኞቹ የሕግ ተጠያቂነት ጉዳይ ቋሚ ሲኖዶሱ የጋራ አቋም ላይ እንዳይደርስ ብፁዓን አባቶችን በተለያዩ መንገዶች ለመከፋፈል እየጣሩ ለሚገኙትና የቤተ ክርስቲያንን ዐበይት ችግሮች ውጫዊ ለሚያደርጉት እነየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ኃይሌ ኣብርሃ እና መሰሎቻቸው፣ ይህ ዐይነቱ የሚኒስትሩ አቋም በእጅጉ አስከፍቷቸዋል፤ አስደንግጧቸዋልም!!
በአንጻሩ በፀረ ሙስና እና በፀረ ኑፋቄ የተጋጋለ ንቅናቄ ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለፍትሕ መስፈን የቆሙ የለውጥ ኃይሎች በጠንካራ የአስተሳሰብ፣ የመረጃ እና የሞራል የበላይነት ቁመና ላይ ይገኛሉ፤ አማሳኞች እና የለውጥ ኃይሎች በትይዩ በሚቆሙበት መድረክ÷ ወይ አማሳኝነት ወይ ተቋማዊ ለውጥ ያሸንፋል፡፡
የሃይማኖት ተቋሞቻችን የተመሠረቱበት ዘመናት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ሥርዐታቸው፤ ለተከታዩ ሕዝብ ያላቸው ግልጸኝነት እና የተጠያቂነት ጉድለት ለኪራይ ሰብሳቢነት ከፍተኛ ተጋላጭነትን እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳት ነው፡፡ መሪ ተቋማቱ በሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲያጡና ከተለያዩ ጫፎች ተነሥተው ተቋሙ እንዲወገዝ ምክንያት የሚኾነው ብልሹ አሠራሮች የሚፈጥሩት የተከማቸ ቅሬታ ነው፡፡
በተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ሀብት እና ንብረት ለኪራይ ሰብሳቢነት በስፋት የሚጋለጥበት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድ፣ በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ በአጠቃላይ ሀብት እና ንብረት የት እና በማን እጅ እንደሚገኝ የማይታወቅበት ነው፡፡
የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ተከታዮች የሚተቹበት እና አስተያየት የሚሰጡበት መንገድ፤ የሃይማኖቶቹ የልማት ሥራም ይኹን ሌላ ለተከታዩ ቀርቦ ግልጽ ውይይት የሚደረግበት፤ የግልጸኝነት እና የተጠያቂነት አሠራር የሚባል ጉዳይ የተተከለ አይደለም፡፡
ስለዚኽ በውስጣቸው የሥልጣን ሽኩቻ፣ የሙስና እና የአስተዳደር በደሎች ይህንኑ ለመሸፈንና ለመቃወም በሚደረግ ትግል የሚፈጠር ቀውስ ተጋላጭነትን ያስከተለ ነባራዊ ኹኔታ ኾኗል፡፡
አክራሪነት እና ጽንፈኝነት ከሕገ መንግሥታችን ጋር ያለው የማይታረቅ መሠረታዊ ቅራኔና መፍትሔው፤ ገጽ 84 – 85