እውነትን ውጠን ራሳችንን በማረም ከታሪክ ተጠያቂነት እንዳን::(ምንሊክ ሳልሳዊ)

እውነትን ውጠን ራሳችንን በማረም ከታሪክ ተጠያቂነት እንዳን::(ምንሊክ ሳልሳዊ)
 
…… ይጻፋል::…ይነገራል::…ይደሰኮራል::…ፕሮፓጋንዳው ተጣፍጦ ይቀርባል::..ራሳችን እናርም::ምን ጎደለ?የሚል ጠፋ::ተስፋ የተሰቀለ ዳቦ ከሆነ ለውጥ ሁሉ የጭብጨባ አሽኮለሌ ከሆነ ቆየ::ምንም ፈቀቅ የለም::ኑ እንዋቀስ:: ኑ እውነትን እንዋጥ:: ኑ እንገላልጠው::ባሌለ ነገር ላይ ባልተፈጠረ ነገር ላይ ባልተወረደ ጉዳይ ላይ ባልተሰራ ድርጊት ላይ ዝም ብለን በተባለ እስክስ እያልን አናላዝን::ለውጥ ከፈለግን እየተተራመሰ ወዳለው የወያኔ ጉጅሌ አገዛዝ መሰስ ብለን እንግባ::በወሬ ናዳ በዜና ፉጨት አሊያም በአፍ ሙሉ ሃሰት ሲሻም ያልተሰራ በመዘባረቅ ለውጥ አይመጣም::በአንድነት ሆነን በጽናት ከልብ በመነጨ እውነት ካለመወላወል ካለወረት ሕዝብን ማእከል አድርገን ለለውጥ እንነሳ::
 
ራሳችንን እንጠይቅ::ካለፈው የትግል ሂደት ምን ተማርን? በተናጠል ታገልን::የሌላውን ውህደት ለማብጠልጠል ሲሉም ለማዳሸቅ ትብብር አልን አሽሟጠጥን::የጋራ ትግልን ብልጭ አድርገን ጨለማ አለበስን:እርስ በርሳችን ተናቆርን::ለጠላታችን ወያኔ ክፍተት ሰጠን::ወያኔ ክፍተታችንን እየፈለገ እንዳሻው ተጫወተብን::በለውጥ ፈላጊ ሃይሉ ጎራ …በዝረራ ተሸነፍን ከሚለው ጀምሮ እስከ ጠላት ጎራ .. በሰራነው ስራ ድል አግኝተናልን እያነበብን ተዘባበትን::ግን አንዲችም ፈቀቅ አላልንም::ይባስ እርስ በእርስ ስንባላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ ተገደሉ በቶርች ተሰቃዩ::በሺዎች ተሰደዱ:;ለባህር እና ለቢላዋ ተዳረጉ::እውነት ለመያዝ ያልዳዳን መሆናችን ትግላችንን ቀርፋፋ ፍቅርን በመቻቻል ለለውጥ ለመጠቀም ፈቃደኛ አለመሆናችን ለከፋ ስህተት እየተዳረግን ነው::
 
በማእከላዊ የማሰቃያ እስር ቤት ወገኖቻችን ከብልት መቀጥቀጥ ጀምሮ እስከ ሴት ልጅ ገበና በአደባባይ መጋለጥ ድረስ ከዚህም የባሰ ጉድ አየን::እኛ ግን ባለንበት እየረገጥን ነው::የራሳችን ጠላቶች::ወዳጅነት እና ዝምድና እየመረጥን እከሌ ይፈታ በማለት ለከፍተኛ ስቃይ የተዳረጉትን ትልቅ መስዋትነት የከፈሉትን እንዲረሱ ያደረግን እኛው ራሳችን የራሳችን ጋሬጣዎች የትግል እሾሆች ነን::በአደባባይ የፖለቲካ ሰዎች ግድያና የዜጎች መፈናቀልም የዚሁ አካል ነው::እርስ በእርስ መጎሻሸም እና መሰዳደብ አለመብሰል ነው::በራስ መተማመን ስላሌለን የራሳችንን ስህተቶች ከራሳችን ላይ አውርደን ለሌላው አጋራችን የምንደፈድፍ ከትላንትና መማር ያልቻልን የጥቂት አፈ-ወርቅ ፖለቲከኞች የገደል ማሚቱ የውጪ ጠላቶች አሸርጋጅ ሆነን ራሳችን ደብቀን ሌላውን ለመወንጀል የምንዳዳ ብስለቱ የጎደለን በትንሽ ድል የምናሽካልል በትንሽ ሽንፈት የምንሰበር በፈጠራ ፕሮፓጋንዳ የምንታለል ባልተኬደበት መስመር ላይ የምጭበረበር ራሳችንን ማረም የሚያስፈልገን ::ግን አስከመቼ ? እንንቃ ጎበዝ!!!!
 
ዘላለማችንን ሕወሓትን ለመደምሰስ ሳይሆን ስለ ስራዎቹ ከባድነት እያወራን በሕዝብ ውስጥ ሽብር የምንለቅ የሃይል ሚዛን ፖለቲካ ያልገባን ባዶ ፕሮፓጋንዲስቶች ሆነን እስከመቼ እንቅጥላለን?እውነት ግልጹን መውጣት አለባት::ስህተታችንን ይዘን የምንቀጥል የአንድነት እና የጋራ ትግል እሾሆች ከሆንን ለውጥን እንደናፈቅናት እንኖራለን::እርስበእርስ እየተባላን ለውጥ የለም::የኔ መሳመር ብቻ ተከተል የኔን ድርጅት ብቻ ደግፍ እያልን ለጥ የለም::ለውጥ ከፈለግን በመቻቻል በፍቅርና በአንድነት ልንቆም ይገባል:: 2007 የለውጥ አመት እንዲሆን ሁላችንም ያላሰለሰ ጥረት ብናደርግም በወያኔ አገዛዝ ክፋት በውጪ ሃይሎች ጎታችነት እንዲሁም የኛ በጋራ አለመቆም ውጤት ልናገኝ አልቻልንም::በመጪ ዘመን ላይ ግን ከባለፈው የተለየ አዲስ የጋራ ትግል እና አንድነት ፍቅር እና መቻቻል ኖሮን ነጻነታንን ማረጋገጥ አለብን::ዝም ብለን ስለወያኔ ብቻ ከመጮህ ራሳችንን እያረምን ለትግሉ ታላቅ የሆነ ስኬት እና ለለውጥ ልንሰራ የዜግነት ግዴታ አለብን:: ራሳችንን ከታሪክ ተጠያቂነት እናድን::እውነትን ውጠን ራሳችንን በማረም ከታሪክ ተጠያቂነት እንዳን::#ምንሊክሳልሳዊ