የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ዐረፉ
የቀብር ሥርዐቱ ነገ በ5፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
በብሕትውናቸው፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው እና ኹሉን በሚያቀርበው ይውህናቸው የሚታወቁት የኢሉባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ዛሬ፣ ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማለዳ ላይ ዐረፉ፡፡
የእግራቸው ቁስለት ወደ ካንሰር የተባባሰባቸው ብፁዕነታቸው፣ በደቡብ አፍሪቃ ሕክምና ተደርጎላቸው ከተመለሱ በኋላ በሀገር ውስጥ በናሽናል ሆስፒታል ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ዛሬ፣ ማለዳ 12፡00 ላይ ዐርፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣ ሥርዐተ ምንኵስና የተቀበሉት በሰሜን ወሎ እመ ምዑዝ ፍቅርተ ክርስቶስ ገዳም ነው፡፡ ከስድሳ ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው የሚነገርላቸው ብፁዕነታቸው፤ በይበልጥ የሚታወቁት በተባሕትዎ ሕይወታቸው፣ ወገን ሳይለይ ኹሉን በሚያቀርበው የዋሃታቸው፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው እና ከደብር እልቅና እስከ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት በሚደርሰው የአስተዳደር ሥራቸው ነው፡፡
በፊት ስማቸው አባ ገብረ ማርያም ፈለቀ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፤ ባዕለጸጎችን አስተባብረው ነዳያንን ሲረዱ የኖሩበትን የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራልን በምእመናን ጥያቄ ተመድበው አስተዳድረዋል፤ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር እንዲኹም ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በእልቅና አገልግለዋል፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ እና በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከትም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሠርተዋል፡፡
ፍቅረ ሢመት የራቀላቸው ብፁዕነታቸው፣ ከሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጀምሮ ለኤጴስ ቆጶስነት ማዕርግ ቢታጩም፣ “ለዚኽ ማዕርግ አልበቃኹም” በሚል ሲሸሹት ቆይተው፣ ከሌሎች ስድስት ብፁዓን አባቶች ጋር ኅዳር ፬ ቀን ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተብለው የኢሉባቦር ጳጳስ ኾነው ተሹመዋል፡፡
አህጉረ ስብከታቸውን እንደያዙ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትንና የመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን ከ፲፱፻፺፯ – ፳፻፫ ዓ.ም. በበላይ ሓላፊነት መርተዋል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ምርጫ እና ውሳኔ ከ፳፻፫ – ፳፻፭ ዓ.ም. ግንቦት ወር ድረስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣ ከተማሪ ቤት ጀምሮ በእግራቸው ታፋ ላይ ሲያስቸግራቸው የኖረውና ቆይቶም ወደ ነቀርሳነት ለተባባሰው ቁስለት የሕክምና ክትትል ለማድረግ ካልኾነ በቀር በሀገረ ስብከታቸው ጸንተው በመሥራት ይታወቃሉ፤ “የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ካለቀ ለአንድ ቀን ማደር ይከብዳቸዋል” ይላሉ አንድ ወዳጃቸው፡፡
የብፁዕነታቸው ዜና ዕረፍት ዛሬ ማለዳ ከመሰማቱ አስቀድሞ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በንግድ ባንክ ብቸኛ ሒሳባቸው ያለውን ብር 9000፣ በሀገረ ስብከታቸው ላሳደጓቸው እና በዚኽ ዓመት ለመሰናዶ እና ለከፍተኛ ትምህርት ላበቋቸው ኹለት ልጆች እኩል እንዲከፋፈል አዝዘው እንደነበር ሲያስታምሟቸው የቆዩት ተናግረዋል፤ “ሌላ ሀብት እና ንብረት የለኝም” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ልጆቹ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱም ረዳት እንዳያጡ አደራ ሰጥተዋል፡፡
የብፁዕነታቸው አስከሬን ካረፉበት ናሽናል ሆስፒታል ዛሬ ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ሊቀ ሥልጣናት ኾነው ወዳገለገሉበት፣ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ታጅቦ ይደርሳል፡፡ ጸሎተ ፍትሐቱ በዚያው ሲከናወን አድሮ በነገው ዕለት ከቀኑ 5፡00 ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአህጉረ ስብከታቸው ሓላፊዎች፣ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ሥርዐተ ቀብሩ እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
![]()
