የአምባገነኖች ክለብ “እከክልኝ ልከክልህ” በጉልህ የታየበት ጉባዔ። (Daniel Dirsha)

የአምባገነኖች ክለብ “እከክልኝ ልከክልህ” በጉልህ የታየበት ጉባዔ።  (Daniel Dirsha)

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ 10ኛ ጉባዔውን በመቀሌ ከተማ ዛሬ ነሐሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ጧት ጀምሯል። ሀገሪቱ ሠላማዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የማይቻል መሆኑን ያመኑ የትጥግ ትግል እያካሄዱ በሚገኙበት ሀገር “በሀገሪቷ ሠላም ሰፍኗል” እያለ ነው። በለምን ተተቸሁ “እልሁ” በነጻው ፕሬስ ጉሮሮ ላይ ቆሞ ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት ከዳረገ በኋላ መስማት የሚፈልገውን የሚናገሩለትን በመጋበዝ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ይገኛል። “ኮሙኒስታዊ” ጭብጨባና ድባብ የተስተዋለበትን የዛሬ ጉባዔ ግማሽ ቀን ውሎ የ”እህት” ፓርቲ ልዑካን ለኢህአዴግ ‘መወድስ’ አቅርበውበታል።
…ኢሠፓ ትዝ አለኝ። አማኑኤል አምደሚካኤል ታወሱኝ። ኬኔት ካውንዳ በሀሳቤ ተመላለሱ።
ሩብ ክፍለ ዘመን ሥልጣን የሙጥኝ ብሎ የሚንገዳገደው የአል በሽር ፓርቲ ‘ናሽናል ኮንግረስ፣ በነዳጅ ገንዘብ ሙስና ናላቸው ዞሮ ብዙዎችን ለዕልቂት 2 ሚሊየን ህዝብ ለፍልሰት የዳረገው የሳልቫ ኪር ‘ደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር’፣ ማሊማ እንዴት ተቃወመኝ ብሎ… ለግለሰቦች ሳይቀር ክስ ለማቀናበር የማይሰንፈው… ውስጡ የሚናጠው የሳውዝ አፍሪካው “አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ”፣ የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘ወዳጅ’ የርዋንዳው ፖል ካጋሜ ‘አርበኞች ግንባር’፣ የቻይናው አገዛዝ… ምናለፋችሁ ብዙዎቹ የኢህአዴግን “ጥበብ” እና “ብልሀት” በተመከክተ ዛሬ ሲያብራሩልን ውለዋል።
አሳዛኙ ነገር…
የአገዛዙን “ብቃት” ሲያነበንቡ ከዋሉት መሀል በጣም ቅርበት አላቸው የሚባሉት የርዋንዳው አርበኞች ግንባር ወኪል እንድ ዜ እንኳ የኢህአዴግን ስም አስተካክለው መጥራት አለመቻላቸው።
የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀደም ሲል የተደረገውን የአዲስ አበባ ስምምነት አስገድዶ ነው ያስፈረመኝ ያሉት የደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኪር መቀሌ የላኳቸው ሴትዮ በበኩላቸው “ከንፋሱ ጋር በማጎንበስ” ኃይለማርያም የሠላም ስምምነቱ ሲፈረም ጁባ መገኘታቸውን በእጅጉ ለማድነቅ የሞከሩ መስለው ለመታየት መሞከራቸው… ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን ማስተዋል አይከብድም። የአምባገነኖች ክለብ “እከክልኝ ልከክልህ” በጉልህ የታየበት ጉባዔ።
የታንዛኒያው ቻማቻ ምፒንዱዚ ተወካይ በመቀሌው ንግግራቸው “long live Hailemariam” ሲሉ ካውንዳና ኮ/ል መንግስቱ በዓይኔ ተመላለሱ። ኢሠፓ በሥልጣኑ የመጨረሻ ዓመት እንዲህ ዓይነት “የአምባገነኖች መወዳደሻ” ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር። የያኔው የፍትህ ሚኒስትር አማኑኤል አምደሚካኤል የመድረክ መሪነቱን ተቆጣጥረው “የኢትዮጵያ ትንሳዔና መሪ በዕውኑ ማነው? ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እይደሉምን?” እያሉ እዳራሽ ሙሉ ህዝብ አስጨበጨቡ። ዛሬ በመቀሌ “ሰማዕታት አዳራሽ” የሰማሁት ጭብጨባ ከዚያን ጊዜው ጋር ተመሳሰለ። የያኔዎቹ አጨብጫቢዎች ሰማያዊ ካኪ የለበሱ፣ የዛሬዎቹ ደግሞ ቀይና ብጫ ቲሸርትና ኬፕ ያጠለቁ መሆናቸው ይሆናል ልዩነቱ። …እኒያ አዳራሽ ሙሉ ህዝብ ሲያስጨበጭቡ የነበሩ የፍትህ ሚኒስትር ለካ እውነታቸውን አልነበረም። ይህ ከሆነ ብዙ የሚባል ቀን ሳይቆጠር ሚኒስትሩ ለህክምና ብለው አሜሪካ ከገቡ በኋላ እንዲያ ሲያወድሱት የነበረውን የኮሎኔል መንግስቱ አገዛዝ ያብጠለጥሉት ገቡ። ይለይላችሁ ብለው ደግሞ ኤርትራዊ መሆናቸውን ጠቅሰው የሻዕቢያ ደጋፊ መሆናቸውን ትፋ አደረጉ። ለካ… “መንግስቱ ጀግናው” በማለት ያን ሁላ ባለሥልጣን ሲያስጨፍሩ እና ሲያስጨበጭቡ የዋሉት የሻዕቢያ ሰው ነበሩና።
በዚያው ዕለት የዛምቢያ መሪ የነበሩት ኬኔት ካውንዳ ወደ መድረኩ ወጥተው “አንድ ህዝብ፣ አንድ መሪ፤ ያ አንድ መሪ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርበው “አንድ መሪ… እሱም መንግስቱ ኃይለማርያም” ሲሉ የራሳቸውን ጥያቄ መለሱ። ካውንዳ ይህን ብለው ዠማውን ሲያነሳሱ ከተቀመጡበት የፊተኛው ረድፍ ወንበራቸው ብድግ ብለው ጭብጨባውን ካደመቁት መሐል የኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ አንዱ ነበሩ። መንግስቱ ኃይለማርያም ከተገለበጡ ሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ እንኳ ሥልጣን ለመልቀቅ የማያስቡት ሙሴቪኒ ይኸው ዛሬም በፓርቲያቸው ስም የሚያስጨበጭብ እና የሚያጨበጭብ አንድ ሹም መቀሌ ድረስ ለመላክ አልሰነፉም።
ሳሞራ ማሼል እና መንግስቱ ኃይለማርያም ሶሻሊዝም ያስተሳሰራቸው “ወዳጃሞች” ነበሩ። በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው የሞዛምቢኩ መሪ ሳሞራ ማሼል አዲስ አበባ ተጋብዘው በመጡ ወቅት ከመንጌ ጋር ያላቸውን “የትግል አጋርነት” ለመግለጽ “አሉታ ኮንቲኒዋ” (ትግሉ ይቀጥላል) ሲሉ በቅኝ ገዢያቸው አፍ ተናገሩ። ይህ ከሆነ ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ የሞዛምቢኩ ፍሬሊሞ ፓርቲ ተወካይ በመቀሌ ተገኙ። ቃል እንኳን ሳይቀይሩ እንዲህ አሉ፦ “አሉታ ኮንቲኒዋ” (ትግሉ ይቀጥላል) የትኛው ትግል?… “ወይ የሰው መመሳሰል!”

Daniel Dirsha's photo.