አቶ ዓባይ ወልዱ የሕወሓት ሊቀመንበር ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ከነሐሴ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመቀሌ የሰማዕታት አዳራሽ ሲካሄድ የከረመው 12ኛው የሕወሓት ጉባዔ አቶ ዓባይ ወልዱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ በድጋሚ መረጣቸው፡፡ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ከሁለቱ ሊቀ መናብርት በተጨማሪ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ አቶ በየነ ምክሩ፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ (ፖሊት ቢሮ) አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ሕወሓት ከነባር የፖሊስ ቢሮ አባላት መካከል አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ አባዲ ዘሞ፣ አቶ ቴድሮስ ሐጎስና አቶ ፀጋይ በረኼ በመተካካት ሸኝቷል፡፡ ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ አቶ ተወልደ ብርሃን በርኼና አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በፈቃዳቸው ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለቀዋል፡፡
ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት 50 አባላት ታጭተው 45 አባላት የተመረጡ ሲሆን፣ የአቶ ዓባይ ወልዱ ባለቤት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነ ማርያምና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያ ገብረ ሕይወት ሳይመረጡ ከቀሩት አምስት አባላት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በተካሄደው 11ኛው የሕወሓት ጉባዔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ከተመረጡት ውስጥ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነ ማርያምና አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ ሳይቀጥሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር አዳዲስ አባላት ሆነው ገብተዋል፡፡