‹‹እንደሚታረድ በግ ዘቅዝቀው ገርፈው ነው ያሳመኑኝ›› ዛሬ ነሃሴ 18/2007 ዓ.ም በአራዳ ምድብ ችሎት የታዘብኩት

‹‹እንደሚታረድ በግ ዘቅዝቀው ገርፈው ነው ያሳመኑኝ››  Getachew Shiferaw ..

..
ዳኛው፡- ‹‹ስራ?››
ተከሳሽ፡- ‹‹ጫኝና አውራጅ!››
ዳኛው፡- ተከሳሽ ክሱ እንደደረሰው ካረጋገጡ በኋላ ማንበብ ጀመሩ፡፡ ‹‹በ1996 የወጣውን —— ህግ በመተላለፍ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት ወይንም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ሲል ከወይዘሮ—- 700 ብር የሚያወጣ ቴክኖ ሞባይል በመንጠቅ ላልተያዘው ግብረ አበሩ ሰጥቷል›› የሚል ክስ አነበቡ፡፡ አንብበው ከጨረሱ በኋላ ‹‹ክሱን ትቃወማለህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡለት፡፡
ተከሳሽ፡- ‹‹አልቃወምም!››
ዳኛው፡- ‹‹ጥፋተኛነትህንስ ታምናለህ?››

ተከሳሽ፡- አንዳች የንዴት ስሜት ይነበብበታል፡፡ ብስጭት! እልህ! ‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ አይደለሁም፡፡ የሚባለውን ነገር አልሰራሁም፡፡ የማላውቃቸው ሲቪሎች እንደ በግ ዘቅዝቀው አስረው ገርፈውኛል፡፡ እንደ በግ ዘቅዝቀው ገርፈው ነው ያሳመኑኝ፡፡ የተገረፍኩትንም ልብሴን አውልቄ ሰውነቴን ላሳይ እችላለሁ፡፡›› አሁንም ንዴቱ ይታይበታል፡፡

ዳኛው፡- ተከሳሹ ስለሚለው ምንም አላሉም፡፡ ምንም! ምንም የተሰማቸውም አይመስሉም፡፡ ምንም ስሜት ሳይሰጡትም ‹‹አቃቤ ህግ ምን አስተያየት አለዎት?›› አሉ!

አቃቤ ህግ፡- ‹‹ተከሳሽ ክሱን ክደው የተከራከሩ ስለሆነ ምስክሮች እንዲሰሙልን››፡፡ ዳኛው ምንም ያልተሰማቸው ማስከሰስና ማሳሰር ስራው የሆነው አቃቤ ህግማ ተደበደብኩ፣ ተገረፍኩ ስለሚለው ምስኪን ምንም ሊል አይችልም፡፡ ምን አልባትም በሆዱ ‹‹እሰይ!›› ይል ይሆናል!

ዳኛ፡- ‹‹ምስክሮች ይግቡ!›› የተደበደበውን የሚያይለት አልተገኘም፡፡

በተከሳሹ ቁስል ላይ ቁስል የሚጨምሩበት ምስክሮች ገቡ፡፡ ምክስክሮቹ ሲገቡ፣ ተከሳሾ የጎሪጥ አያቸው፡፡ የንዴቱን ፈገግታውን እያሳየ፣ አንገቱን ነቀነቀ፣ አይኖቹ እንባ ሞሉ፡፡ ምን አልባት ምን አልባት በፖለቲካ አመለካከቱ (በአጋጣሚ በሰጠው አስተያየት) ካድሬዎች አጥቅተውት ይሆናል፡፡ ምን አልባት የባለ ጊዜዎችን ቀይ መስመር ተሸግሮ ይሆናል፡፡ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ የሚያቀርበውን ጥያቄ፣ የሚያሰማውን ሮሮ ግን የሚሰማው አላገኘም፡፡ በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲህ ነቻ! የባለ ጊዜ! ምስኪን ደግሞ በሀሰት ተገርፎም ቢሆን ይከሰሳል፣ ሮሮውን የሚሰማው አያገኝም!

(ዛሬ ነሃሴ 18/2007 ዓ.ም በአራዳ ምድብ ችሎት የታዘብኩትን ነው)