የበረኪና ሽብር ? ( ሄኖክ የሺጥላ )
የበረኪና ሽብር ? ( ሄኖክ የሺጥላ ) =======
ድሮ ድሮ ፣ ሕይወት ብርቅ በነበረበት ጊዜ ፣ አባት እና አናትን ማክበር እንዲህ እንደዛሬው ቀልድ ሳይሆን ፣ ያኔ ከጋብቻ በፊት ማርገዝ እንደ ትልቅ ነውር ይታይ በነበረበት ዘመን ፣ ድሮ ማለቴ ነው፣ ያኔ በደጉ ዘመን፣ አንድ ሰው << ዋ !ታንቄ ነው የምሞተው >> ካለ ፣ በቃ የነብስ አባት መጥቶ ይገዘታል ፣ አቡነ ሰበ-ሰማያት ይደገማል ፣ እንደው ጭንቀት ከሆነ ይለቀው ዘንድ እራቅ ወዳለ ዘመድ ጋ ሄዶ ፣ ከርሞ እንዲመጣ በአጃቢ ይላካል ። ፍቅር አጃኢብ የነበረበት ዘመን ። የልብስ በረኪና ፣ የመትረየስ ወይም እንደዛሬው << የፌደራል ፖሊስ ያኸል >> ማስፈራሪያ የነበረበት ጊዜ ።
አንድ ሴት ልጅ << ልጃገረድ > ፣ የአመት’ባል ልብስ ካልተገዛላት ፣ ወይም በድንገት ካረገዘች ፣ ወይም የእንጀራ እናቷ ካስማረረቻት ፣ << በአቅራቢያዋ ከሚገኝ ሱቅ >> በረኪና ገዝታ ጭልጥ ታደርግ ነበር ። አብዛኛውን ጊዜ ታዲያ ፣ እንዳይሞቱ ሆነው ነው የሚጠጡት ። አላማው በቤተሰብ ላይ ሽብር መንዛት ነው ። ልሞት ነው ፣ በቃ ከአሁን በሗላ አታገኙኝም ፣ ጠፍቼ ልሄድ ነው ። የአይጥ መርዝ ነው በልቼ የምሞተው ፣ እሌትሪክ ነው የምጨብጠው ፣ ውሃ ውስጥ ነው የምገባው ፣ በመኪና ነው የምገጭላችሁ እና ወዘተ ።
ያኔ ሽብር በየማጀቱ ነበር ፣ ግን በሬዲዮ አይወራም ፣ መንግስት ባጀት መድቦ ግዳዩን አይከታተልም ፣ በረኪና የሸጠው ሸምሱም ሆነ ፣ በረኪናውን ገዝታ የጠጣችው አስካለ ፣ << ለሽብር ጥፋቱ የሚሆናቸውን መሳሪያ ከዚህ አገኙ >> ብሎ ዜና የሚሰራ የፖሊስ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የለም ። ሽብር ግን ነበረ ! ያኔ ሽብርተኛው ፣ <<ግንቦት ሰባት ከሚባል አካል ጋር በመቀናጀት >> አይደለም ሽብሩን የሚሰራው ። ለሽብሩ ማስኬጃም የሚጠቀምባቸውን ግብዓቶች ፣ በድብቅ በነጠላ ሸፍኖ ፣ ከ- ጏዳ በአሳቻ ሰዓት በመግባት ፣ የሽብር ተግባሩን ይፈጽማል ። በአብዛኛው ታዲያ ሽብሩን የሚፈጽመው ፣ ሰው ሲመጣ ጠብቆ ነው ። ምክንያቱም አፋጣኝ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ።
ለምሳሌ ፣ የዛን ዘመን ሽብርተኛ << ባልቦላ ካጠፋ በሗላ ፣ የዔለትሪክ ገመዱን ሊይዝ ይችላል ። አሁን ግን ባልቦላ ማጥፋትም አይጠበቅበትም ። ለምሳሌ የዛን ጊዜ ሽብርተኛ << እጠፋላሁ >> ብሎ ካለ ፣ መንደሩ በሱ የእጠፋለሁ ዛቻ ይታመሳል ። በቃ እቤት ውስጥ ጠባቂ አብሮት እንዲሆን ይደረጋል ፣ ከቤቱ ድንገት ከወጣ << የሚጠፋው ልጅ !>> ተብሎ ይወራለታል ። እናቶች ፣ << የአከሌ ልጅ እጠፋለሁ አለ !>> ብለው በየ ቡና መጣጫው ያወሩለታል ። ያኔ መጥፋት እንኳ በጣም ብርቅ ነበረ ። በአሁኑ ጊዜ <<እጠፋለሁ!>> ብለህ ብትል ፣ << እስካሁን ምን ትሰራለህ ? እኩዮች ጣልያን ገብተው !>> ትባል ይሆናል ። ወይም ደሞ << እጠፋለሁ >> ብትል << አለህ እንዴ ?>> የሚል ጥያቄም ሊቀርብልህ ይችላል ።
ዛሬ አንድ ሰው በረኪና ጠጥቶ ራሱን ቢያጠፋ ፣ ቤተሰብ ቀድሞ የሚያየው የበረኪናውን ዕቃ ነው << እንዳለ ነው የጠጣችው ወይስ ትንሽ ለማጠቢያ የሚሆን አስተርፋልናለች ይቺ ጨካኝ ፣ በተወደደ በረኪና !>> የሚል ነው የመጀመሪያው ጥያቄው ( first-aid ) ማለት ነው ።
ታዲያ እንዲህ እንደዛሬው ፣ ሕጉ በረቀቀበት ሰዓት ፣ አንድ ሰው በረኪና ጠጥቶ ህይወቱ ከሞት አፋፍ ደርሳ ብትመለስ ፣ ዳኞች ፊት ራስ በማጥፋት ተከሶ ቢቆም ፣ የሚጠይቁት ጥያቄ የሚመስለኝ ። << ከአሸባሪው ግንቦት ሰባት ጋ ግንኙነት አለህ ?>> << ራስህን በበረኪና በማጥፋት ፣ መንግስታችን ፣ ከአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ግስጋሴ ለመግታት ; ከአልሸባብ እና ግንቦት ሰባት ጋ ተመካክረህ ያደረከው ነገር እንደሆነ ደርስንበታል !>> ። << በረኪናውንም ስትገዛ ገቢው ለኢሳት እንዲሆን ብለሃል አሉ ? ይህ እውነት ነው ? >> በረኪናውን በሰማያዊ ወረቀት ጠቅልለህ ወደቤትህ እንደገባህ ያየ ሰው ነግሮናል ፣ ይህም ለሰማያዊ ፓርቲ ያለህን አጋርነት ለማሳየት ነው !>> ከዚህ ቀደም ራስህን በገመድ ለማጥፋት ስትሞክር ፣ ጀግናው የፌደራል ሰራዊት በቦታው በፍጥነት ደርሶ እንዳተረፈህ ፣ ገመዱም ለግንቦት ስላሴ የተገዛ ሰንጋ የታሰረበት እንደሆነም ደርስንበታል !>> ይሉት ነበር ። ደግነቱ በረኪናም በሬም የለም እንጂ !
አዎ አሸባሪነት ፣ እንዲህ እንደዛሬው ፣ በመጻፍ ፣ በመናገር ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ፣ የህዝቦችን እኩልነት በመሻት ፣ ላይ የተመሰረተ አልነበረም ። አሸባሪነት ያኔ በበረኪና እና በገመድ ነበር ። ጊዜው ግን እንዴት ይሄዳል እናንተዬ !