ታግዬ ለውጥ ማምጣት እችላለሁ!›› የሚል ትውልድ አይሸነፍም! – ድምፃችን ይሰማ
‹‹ታግዬ ለውጥ ማምጣት እችላለሁ!›› የሚል ትውልድ አይሸነፍም!
የአስተሳሰብ የበላይነት የትግል እና የድል መሰረት ነው!
እሁድ ነሐሴ 17/2007
ማንኛውም የመብት ትግል የሚጀምረው በበደል ነው፡፡ አምባገነኖች በደልን የሚያደርሱት እጅግ ስልታዊ በሆነ መንገድ በመሆኑና ለዚህ በደልም ሽፋን ስለሚያደርጉለት ብዙዎች የሚበደሉት እየተበደሉ መሆናቸውን ሳይረዱ ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው የትግል የመጀመሪያ እርምጃ የሆነው በደሉን ማወቅና መንቃት ለብዙሃኑ ቀላል ያልሆነው፡፡ ሰዎች በደል መኖሩን ቢረዱ እንኳን አምባገነኖች የሚፈጥሩትን የፍርሃት ድባብ ጥሰው መታገልና ‹‹ለውጥ ማምጣት እችላለሁ›› የሚል አስተሳሰብ ላይ መድረስ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ የመጀመሪያ እርምጃዎች ናቸው ረጅም ጊዜ እና ብዙ ጉልበት የሚጠይቁት፡፡ አንድ ማህበረሰብ መበደሉን ከተረዳና ይህንን በደሉን ታግሎ ማስተካከል እንደሚችል ፅኑ እምነት ካለው ቀጥሎ የሚኖረው የትግል ሂደት ምንም እንኳ ብዙ መስዋእትነት የሚያስከፍል ቢሆንም ብዙ ርቀት መጓዝ የሚችል ይሆናል፡፡
በደል መኖሩን ማወቅ፣ ታግሎ ማስተካከል እንደሚቻል ፅኑ እምነት ማሳደር፣ መስዋእትነት ለመክፈል ፍቃደኛ መሆን ለትግል መሰረታዊ የሆኑ አላባውያን ናቸው፡፡ ትግልም ፍቺ የሚሰጠው በእነዚህ አላባውያን ድምር ነው፡፡ አምባገነን መንግስታትም ህዝብ እነዚህን የትግል አላባውያን እንዳያሟላ ስልታዊ ጥቃቶችን ይፈፅማሉ፡፡ ከመነሻውም በደልን የሚፈፅሙት ህጋዊ ሽፋን ተጠቅመው ሲሆን በተለይም ተርታውና ብዙሃኑ ህዝብ በደሉን እንዳይረዳ በማያቋርጥ ፕሮፓጋንዳ እና ውትወታ አማካኝነት የአስተሳሰብ ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡ በደላቸውን የሚጀምሩት በተመረጡና ተፅዕኖ በሚፈጥሩ አካላት ላይ በመሆኑና ለዚህም ህጋዊ ከለላ ስለሚሰጡት ተርታውን ህዝብ በቀላሉ ማታለል ይችላሉ፡፡
በተለያዩ ህዝባዊ ጥረቶች ተርታው ህዝብ ሲነቃ ደግሞ ስልታዊነታቸውን ወደጎን በመተው ወደማስፈራራት ይሸጋገራሉ፡፡ በዚህም ህዝብ ምንም እንደማያመጣ፣ የመጋፈጥ አቅሙ ስለሌለው በደሉን በፀጋ ተቀብሎ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ለማድረግ የፍርሀት ድባብ ይፈጥራሉ፡፡ የተለያዩ የኃይል እርምጃዎችን በመውሰድ በአፈና፣ በእስርና በግድያ ህዝቡን በማስፈራራት ‹‹ተጨባጩን መለወጥ የሚችል አቅም የለኝም›› ብሎ እንዲያምን ይጥራሉ፡፡ ይህ የስነልቦና ጦርነታቸው የማህበረሰቡን ወኔና ብርታትን መግደልን ዓላማው ያደረገ ሲሆን በፕሮፓጋንዳና በኃይል እርምጃም የታጀበ ነው፡፡ይህን መቋቋም የቻለ ማህበረሰብ ትግሉን ከዳር ማድረስ ይቻለዋል!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
