ጠባብ ቡድናዊ አመለካከት አገራዊ እና ሕዝባዊ እሴቶችን ስለሚያፈራርስ ለአገርና ሕዝብ አደጋ ነው::
ጠባብ ቡድናዊ አመለካከት አገራዊ እና ሕዝባዊ እሴቶችን ስለሚያፈራርስ ለአገርና ሕዝብ አደጋ ነው::
#Ethiopia #Unity #Freedom #Change #MinilikSalsawi #Ethiopianism
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) – ላለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ትልቁ ችግር፣ ለዘመናት በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታወቁትን መልካም እሴቶች ለማገናዘብ አለመፈለግ ነው፡፡ በሐሳብ የሚለይን በጠላትነት በመፈረጅ ዓይንህን ላፈር ማለት ትልቁ መለያ ነው፡፡ ዞር ብለን ስናይ ግን ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ፣ ለትልቁ አገራዊ አንድነትና ክብር ቅድሚያ በመስጠት ነው የሚታወቁት፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ዜጎቻችን ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ አንድነታቸው ላይ በማተኮር በመተሳሰብ ሲኖሩ፣ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው አቅጣጫ ይጓዛሉ፡፡
ሥልጣን ላይ የወጣው ቡድን ተምረናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በብሔርና በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች ሲንዱ ይታያሉ፡፡ በአክራሪና በጽንፈኛ አመለካከታቸው የተቃኘውን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ እነዚህን የከበሩ እሴቶች ለማጥፋት ይታትራሉ፡፡ በአንድነት ውስጥ ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ ውበት መኖሩን ባለመቀበል ሁሉንም ነገር ከቡድናዊ ፍላጎት አንፃር ብቻ ማስተናገድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ጠባብ ቡድናዊ አመለካከት አገራዊ እሴቶችን እንደሚያፈራርስ ተገንዝበው ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡
ሥልጣን ላይ የሚወጣው ቡድን የተቀናቃኙን ነፃነት ባለመቀበል ለምን እኔ የምለውን አትሰማም በማለት ያስራል፣ ያጎሳቁላል፣ ይገድላል፡፡ ለሥልጣን የሚታገለውም ተቀናቃኙን ነገ አንተን አያድርገኝ በማለት ጊዜ ሲገኝ የሚወራረድ ዛቻ ይሰነዝራል፡፡ በዚህም ምክንያት በልዩነት ላይ ተነጋግሮ ችግሮችን በማስወገድ ነፃ ኅብረተሰብ እንዳይፈጠር በጠላትነት መፈራረጁ ይቀጥላል፡፡ ያለፉት 40 ዓመታት ጉዞ በደም የጨቀየውና በጥላቻ የተበላሸው የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማክበር ባለመቻሉ ነው፡፡ አገር የሚያውቃቸው አዛውንቶች ባሉበት አገር ውስጥ ሸምጋይ ጠፍቶ ፖለቲከኞች ለከፋ ነገር ሲፈላለጉ ማየት አስተዛዛቢ ነው፡፡ ‹‹የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል›› እንዲሉ፣ አንዳንዶቹ ከመካሪነትና ከመገሰጽ ይልቅ የመጠፋፋት አራጋቢ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የፖለቲካው መንደር ውስጥ ያሉ የማኅበረሰባችንን መልካም እሴቶች ማየት ካልቻሉ ለአገር አደጋ ነው፡፡