በአስመሳይነት በአደባባይ መደስኮርና ዕውነተኛው ዲሞክራሲ ለየቅል ናቸው!
ደህና ሄደን ከመቆልመም ይሰውረን፡፡ የጀመርነውን በአግባቡ ለመጨረስ ጥናቱንም ፅናቱንም ይስጠን! በሙስና ከመመንደግ፣ ቁልቁል ከማደግ ዲበ-ኩሉ ይጠብቀን! ከሸፍጠኛ ዳኛ፣ ከአባይ መስካሪ ያድነን! የመጪውን ዓመት ትምህርታችንን ይግለጥልን! ያለፈውን ዓመት ስህተታችንን እንዳንደግም ልብና ልቡና ይስጠን፡፡
ከውጪ ሸረኛ፣ ከውስጥ ቂመኛ ይጠብቀን፡፡ ሀገራችን “ደንጊያና ቅል ተላግቶ፣ ዜጋና ሹም ተሟግቶ አይሆንም” የማንልባት ሀገር መሆን ይኖርባታል፡፡ ሹም ሲበድል ዝም ብለን የማናይበት፣ ዜጋ መብቱን ሳያውቅ ሲቀር ምክንና ውጤቱን በወግ በወጉ የምናስረዳበት ሁኔታ እንዲኖር መጣር ይኖርብናል፡፡
“እናቱ ወንዝ የወረደችበትም እናቱ የሞተችበትም እኩል የሚያለቅሱበት” ሀገር መሆን የለባትም፡፡ ከቶውንም ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ከፖለቲካዊ ጥቅም ፍለጋ ተለይተው የሚታዩበት ሀገር ታስፈልገናለች፡፡ ከሁሉም በላይ ዛሬ ሐሳዊ – ዲሞክራሲን መዋጋት ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በአስመሳይነት በአደባባይ መደስኮርና ዕውነተኛው ዲሞክራሲ ለየቅል ናቸው! የእከክልኝ ልከክልህን ዜማ ቅኝቱን በመሰረታዊ መልኩ መለወጥ ይኖርበታል፡፡
በተለይም ደግሞ በሂደቱ ውስጥ ዓይን እንደሚቆረቁር አሸዋ ሲያስቸግር የነበረውን ሙስና በቅጡ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ዛሬም የፍትህን፣ የሰብዓዊ መብቶችን፣ የትምህርት ሂደትን ጉዳይ በአፍዓዊ መልኩ ሳይሆን በልባዊ መልኩ መመርመር መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ይህ ካልሆነ “እያቃጠለ ከሚያጠግበኝ፣ እስኪቀዘቅዝ ይራበኝ” የሚለውን መጥቀስ ግድ ይሆናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!