የወያኔ ግፍ በደልና አፈና ሲጨምር ትግላችን የበለጠ ይፋፋማል!
ከዋስይሁን ተስፋዬ
ትግል ካለ የአምባገነኖች ጫናም የዛኑያህል የከፋ እንደሚሆን ግልፅ ነው። ወያኔም እያደረሳቸው ያሉት መጠነሰፊ በደሎች የዚሁ እውነታ ምስክሮች ናቸው። በትግል ሂደት እንቅፋቶችና ችግሮች መከሰታቸው አይቀሬ ነውና፤ የችግሩን ምንጭ ለይቶ ለማወቅና መፍትሄዎችን አበጅቶ ወደፊት ለመራመድ፤ ግልፅ በሆነ መንገድ መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ምኞቴ ለችግሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሄ ተገኝቶ፤ ሁላችንም የነፃነትን አየር በእኩልነት እየተነፈስን፤ በፍቅር፣ በሰላምና፣ በመከባበር መኖር እንድንችል ነው። ትኩረቴ ደግሞ የማምንበትን በግልፅ ለአንባቢያን በማቅረብ ሌሎችም የውይይቱና የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ለመጋበዝ የተቻለኝን መሞከር ነው። በሃሳብ ልዩነቶች ዙሪያ መወያየትን ከምንም በላይ እደሰትበታለሁ፤ ወደ መግባባት የሚያመራ ከሆነ ደግሞ የበለጠ ያኮራኛል። ስለሆነም ሃሳቤን በማካፈሌ ክፉ ነገር ሊመጣ ይችላል ብዬ የምቆጠብ የዋህ አይደለሁም። ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆኑኝ፤ እጅግ የማከብራቸው ወዳጆቼና ጓዶቼ፤ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድና፣ ፍቅረማርያም አስማማው ከቃሊቲና ከቂሊንጦ እስር ቤት የላኩትን መልዕክት አነበብኩ፤ ሰማሁ፤ በውስጣቸው ያለውን ስር የሰደደ ምሬታቸውንም ተመለከትኩ። ስለሃገራቸው ያላቸውን ታላቅ ፍቅር፤ ለጀግኖች ልጆቿም የሚሰጡትን ወደር የሌለው ክብርና ቦታ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊተገብረው የሚገባ እንደሆነ በድጋሚ ማስተጋባትን ወደድኩ። አምባገነኑ የወያኔ ቡድን በንፁሃን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ላይ እያደረሰ የሚገኘውን በደል፤ 100% አሸነፍኩ ያለበትንና የፖለቲካ ምህዳሩን ከላይ እስከታች ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረበትን የይስሙላ ምርጫ ድራማን፤ ባጠቃላይ በሃገርና በህዝብ ላይ የዘረጋውን ቅጥ ያጣ የአፈና መዋቅርና የጥፋት ተልዕኮን፤ ባጭሩም ቢሆን፤ በሚገባ አስቀምጠውታል፤ በዚህም ሙሉ ለሙሉ እስማማለሁ። ይሁንና እነኝህ ጀግኖች ጓዶቻችን ለነፃነት የከፈሉት መሥዕዋትነትና ለመታገል ያሳዩት ቁርጠኝነት፤ እንዲሁም ወደር የማይገኝለት የጥንካሬ መንፈስ፤ ታግሎ የሚያታግል አጋር ፍለጋ ሲኳትንና ያለቦታው ከጠላቶች እጅ ሲወድቅ ማየቱ አመመኝ። በመሆኑም ለጀግኖቻችን ከለላ መሆን የሚችል ጠንካራ ተቋም እንዲኖረን፤ ለችግሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሄዎችን ማምጣትና የሚበጁንን የትግል አማራጮቻችንን ማየት እንድንችል፤ ብሎም በጋራ ተቀናጅተን ለጋራ ህዝባዊ ድል በአንድነት መጓዝ ይቻለን ዘንድ፤ በነርሱ አማካኝነት የደረሰን መልዕክት ለሁላችንም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ስላመንኩ፤ በዚሁ ዙሪያ የማውቀውን፣ የተሰማኝንና፣ ይበጃል ያልኩትን ማካፈልን መረጥኩ፤ እንዲህም አልኩ።
ሶስቱም ወጣት ታጋዮቻችን የሰማያዊ ፓርቲ አመራር እንደነበሩና ዛሬ እንደ ሌሎቹ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ በወያኔ እስርቤት በስቃይ እየማቀቁ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ይህም በመሆኑ እጅግ ያሳዝነኛል፤ ያስቆጨኛልም። የወያኔን የአፓርታይድ አገዛዝ በትጥቅ ትግል ለመታገል ተገደው፤ በኤርትራ በረሃ መሽገው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያኖች ጋር አብረው ለነፃነታቸው ለመታገል ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ በጉዞ ላይ እንዳሉ በወያኔ ደህንነቶች እጅ ስርም እንደወደቁ መረጃ ዶት ኮም (mereja.com) ከሚባለው ድህረገጽ፤ በሗላም ከኢሳት ራዲዮ ሰምቼም ነበር። በወቅቱ፤ ሰማያዊ ፓርቲ የሚከተለውን የትግል ስልት በቅርበት ስለምከታተልና ስለማውቅ፣ እነርሱም ይህንን አምነውና እንደ እምነታቸው ተቀብለው እስከ አመራር ደረጃ ድረስ ከሚያገለግሉበት የፖለቲካ ድርጅት የትግል ስልት ይህን ያህል የተለየ ተግባር ይፈፅማሉ ብዬ ስላልገመትኩ፤ በሰማሁት ዜና እውነትነት መተማመን አልነበረኝም። ይበልጡን ደግሞ፤ በሰላማዊ መንገድ ከወያኔ ጋር አንገት ላንገት እየተናነቁ ለሚገኙ ቆራጥ ልጆቻችን ትልቅ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ስላመንኩ፤ የዚህ ዜና መናፈስን አልወደድኩትም፤ አስከፍቶኝም ነበር። በዚህ አጋጣሚ ህዝብ ነፃነቱን ተጐናፅፎ ዘለቄታዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፤ ብሎም የምንወዳት ሃገራችን ያለምንም ልዩነት ለሁላችንም እኩል እንድትሆን፤ ህዝባዊ የሰላማዊ ትግል ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በፅኑ የማምን ብሆንም፤ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም እስካልነካና ለህዝብ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማምጣት የሚሰራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል እስከሆነ ድረስ፤ ሁሉም በሚችለውና በመረጠው መንገድ መታገል እንዳለበት በፅኑ የማምን መሆኔን አንባቢያን እንዲያሰምሩልኝ አሳስባለሁ። እዚህጋ ሁላችንም አትኩሮት ሰጥተን ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ፤ ሶስቱም ታጋዮቻችን ሰላማዊ ትግል ለነፃነታችን እውን መሆንና ለችግሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማምጣት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ የሚረዱ የሰላማዊ ታጋዮቻችን ናቸው። ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት፤ ይፅፏቸው ከነበሩ መጣጥፎችና በተለያዩ መድረኮች ላይ ያስተላልፉ ከነበሩት መልዕክቶች የህዝባዊ ሰላማዊ ትግል መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችን፣ በውስጡ የያዘው እምቅ ጉልበትን፣ ለወያኔው አምባገነን ገዢ ቡድን የሚያስከትለው አደጋና ስጋትን፣ ለዘመናት አብረውን ለኖሩት የችግር አዙሪቶቻችን የሚያመጣው ዘለቄታዊ መፍትሄን፣ በዋነኝነት ደግሞ በህዝብ ዘንድ (በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ) የሚገነባው የስነልቡና ብቃት፣ ልበሙሉነትና፣ በራስ የመተማመን መንፈስ፤ ወደፊትም ቢሆን አምባገነናዊ ሥርዓትን በህዝብ ላይ ለመጫን አሰፍስፈው የሚገኙ ሃይሎች ካሉም የሚያስተላልፈውን ተስፋ የማስቆረጥ መልዕክት፤ በቅጡ የተረዱ መሆናቸውን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
ይሁንና ዛሬ፤ ያንን የመሰሉ ፅኑ ሰላማዊ ታጋዮቻችን፤ “ወያኔን ከጉልበት በቀር ሰላም እንደማይገዛው” በእጁ ስር መውደቃቸው እንኳ ሳያስፈራቸው፤ በቁርጠኝነት እውነቱን በይፋ ነግረውናል። ከዚህ በላይ ምን እንድንጠብቅ ይቻለን ይሆን!? በእርግጥም ይህ ክስተት ለበርካቶቻችን እንግዳ ሊሆንብን ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እውነታው ይሄው ነውና ሁላችንም ልንቀበለው ግድ ይለናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው፤ የወያኔ ቡድን፤ አርቀው ማየትና ማሰብ የተሳናቸው፤ በማንኛውም አጋጣሚ የሰላም በሮችን ለመዝጋት የሚታትሩ፤ የሃገር ሸክም ሆነው ሃገርን እየመሩ የሚገኙ የጭፍኖች ስብስብ ስለመሆኑ፤ እጅግ በርካታ በሆኑ አጋጣሚዎች አይተነዋል። ይሁንና፤ “ለሰይጣን በአለም ይፈቀድለታል… ” እንዲሉ፤ ወያኔዎች ለህልውናቸው አደጋ የሆነውን የነፃነት ትግል እንቅስቃሴዎችን ለይተው ማጥቃት የቻሉ ይመስለኛል። ላስተዋለ፤ ወያኔ በስልጣን ለመቆየቱ ስጋት የሆነበት የሰላማዊ ትግል እንደሆነ መረዳት እጅግ ቀላል ነው። ወያኔ ሰላማዊ ትግል ውጤታማ የሚሆነው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሲኖረው ብቻ መሆኑን በሚገባ ተረድቷል። ስለዚህ ዛሬ ወያኔ ህዝቡን፤ በተለይ የነፃነት ታጋዮችን፤ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ለማስቆረጥ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ለዛም ሌትተቀን በመትጋት ከ2002ቱ የምርጫ ድራማ ውጤት ወደ 2007ቱ በ100% አሸነፍኩ በመሸጋገር፤ የሰላማዊ በሮችን ሙሉለሙሉ መዝጋትን የመረጠው። ይህም ሆነ ያ፤ ግባችን ነፃነትን መጎናፀፍና ለችግሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሄን ማምጣት እስከሆነ ድረስ፤ በሰላማዊም ሆነ በሌላ መንገድ ታግሎ የሚፈለገውን የብዙሃን ምኞት እውን ማድረግ ከተቻለ፤ የምንጓዝበት መንገድ ብዙም ለውጥ አይኖረውም። ነገርግን ሊሰመርበት የሚገባው፤ ህዝባዊ ትግሉን አቀናጅቶ በተባበረ ክንድ መጓዝ መቻል፤ በተለይ አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁነታ አንፃር ማስተዋልንና ጥበብን እውን ማድረግ እንደሆነ ሁላችንም ልንረዳ ግድ ይለናል። ተቃዋሚው በተቀናጀ መልኩ መታገል ቢችል ኖሮ፤ ወያኔም የሰላማዊ ትግሉን ሊገፋ ባልወሰነ፤ ጠንካራው የጀግኖቻችንም የቆራጥነትና የትግል መንፈስ መድረሻው ጠፍቶት ግራ-ባልተጋባ ነበር። ይህንን ስል የትግል መንፈሳችን፤ እንዲህ ማረፊያ እንዳጣ አሞራ እንደበረረ ይኖራል ማለቴ እንደማይሆን መገመት የማይቻለው ለሃገር ተቆርቋሪ ታጋይ ይኖራል ብዬ አላምንም። ይሁን እንጂ፤ በቅርቡ፤ አንድ ቀን፤ ሁሉም የተቃዋሚ ሃይል እውነታውን ተረድቶ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም የራሱ የሚለው ጠንካራ መአከልን በእጁ ስር እንደሚያደርግ፤ እንደ ነብይም ባይሆን፤ የወቅቱ ህዝባዊ ጥያቄዎችን መሰረት አድርጌና እውነታዉን ተንተርሼ በሙሉልብ እናገራለሁ። ልብ ያለው ልብ ይበል! የዚህች አጭር ፅሁፌም ፍሬ ሃሳብ መነሻ ይሄው ነውና፤ ምክንያቶቼን አጠር አድርጌ ለማካፈል እሞክራለሁ። አንብቦ ሃሳቡን ለሚያካፍለኝ ያለኝን ታላቅ ክብርና አድናቆት ከጅማሮዬ ከመግለፅም አልቆጠብም። መልካም ንባብ!
የሠላማዊ ትግል ገደብ፤ እስከየት ድረስ?
የሃሳቤን ፍሬ ነገር በሁላችንም ጥያቄዎች ልጀምር፤ “እውን ሠላማዊ ትግል ውጤታማ የሚሆነው በወያኔ በጐ ፈቃድ ነውን?”፤ “እውን ሠላማዊ ትግል እኛ ጋር አይሰራም የሚባለው፤ ወያኔ በጨካኝ፣ በአፋኝ፣ ለህዝብ ርህራሄ በሌለው አውሬአዊ አስተሳሰብ የተሞላ ቡድን ስለሆነ ነውን?”፤ “ለመሆኑ ሰላማዊ ትግል ምን ማለት ነው?”፤ “ሠላማዊ ትግል አብቅቶለታል የሚባለውስ ጉዳይ ትክክለኛነቱ ምን ያህል ይሆን?”፤ “ይህን አይነቱ አስተሳሰብ ምን ያህልስ ሊያስኬደን ይችላል?”፤ “ስንቶቹ ናቸው ሰላማዊ ትግልን እጅግ አሳንሰው፤ በምርጫ ማሸነፍ ብቻ እንደሆነ ሁሉ፤ እየሰበኩን የሚገኙት?”፤ “በሃገራችን የነፃነት ትግል ታሪክስ ሰላማዊ የትግል ስልትን እምን ድረስ ገፍተንበታል?”፤ ስንቶቹ የፖለቲካ መሪዎቻችንና ድርጅቶቻችን ናቸው የሰላማዊ ትግልን እምቅ ጉልበት በሚፈለገው መጠን የሚጠቀሙት?”፤ “ስንቶቹስ በሠላማዊ መንገድ የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ይሆኑ፤ ወያኔ ካልተገደደ በቀር በፍቃደኝነት ስልጣን እንደማይለቅ አውቀውና በእምነታቸው ፀንተው እየታገሉ የሚገኙት?”። ከጅምሬ ለመጠቆም እንደሞከርኩት፤ እነኝህና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች፤ አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት በሰላማዊ ታጋይ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ርህራሄ የሌለው የሃይል እርምጃንና አፈናን መሰረት ያደረጉ፤ በተለይ በ100% ማሸነፉን በይፋ ካወጀ እለት ጀምሮ፤ በበርካታ ለሃገር ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ የሚመላለሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች በብዙ መድረኮች ላይ የተነሱ፤ በርካታ ዜጎችም እለትተለት የሚወያዩባቸው እንደመሆናቸው፤ የሃገሩን ጉዳይ ለሚከታተል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲስ እንዳልሆኑ አውቃለሁ። በዚህች አጭር ፅሁፍም መልስ እንደማይገኝላቸው ይገባኛል። ይሁንና ስለጉዳዩ በድጋሚ እንዳነሳ ያስገደደኝ ዋንኛ ምክንያት፤ ከላይ በስማቸው የጠቀስኳቸው፤ በወያኔው ማጎሪያ በስቃይ ዉስጥ የሚገኙ ታጋይ ጓዶቻችን የደረሱበት ውሳኔ እንግዳ ባይሆንም፤ ያስቀመጧቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ከጥያቄዎቹ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙና ምናልባትም የተዛቡ ምላሾችን የሚያመላክቱ ተደርገው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ስለገመትኩ፤ የበኩሌን የመነሻ ሃሳብ ማካፈሌ፤ ሌሎችም እንዲወያዩባቸው እድል ይከፍት ዘንድ በማሰብ ነው።
ዛሬ ለሁላችንም በቀረቡልን ፈታኝ ጥያቄዎች ምላሽ ዙሪያ ለመወያየት መነሻ ይሆን ዘንድ ስለሰላማዊ ትግል ጥቂት ከማውቀው በማካፈል ልጀምር። ሰላማዊ ትግል የተቃውሞ ሰልፎችን ከማካሄድና በምርጫ ከመሳተፍ እጅግ ያለፉ ሌሎች በርካታ ተግባራትንና ሂደቶችን በውስጡ ያካተተ ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። ሰላማዊ ትግል የህዝብን ችግር ለአገዛዙ ከማሳወቅና መብትን ከመጠየቅ (ማሳወቅ) የሚጀምር የትግል ስልት ነው። በምርጫ መወዳደር፣ ችግሩን ለመፍታት ከገዢዎች ጋር በይፋ መደራደር፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የችግሩን ምንነት ለአለማቀፍ ማህበረሰብ በማሳወቅ ትግሉ እውቅናና ድጋፍ እንዲያገኝ ማስቻል፣ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ባደባባይ ህዝባዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱና ችግሮቹ መፍትሄ እንዲያገኙ መጠየቅ ገና በጅማሮው ወቅት ከሚተገበሩ በርካታ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች መካከከል ይጠቀሳሉ። ይሁንና አገዛዙ ጥያቄዎቹን ፈቅዶ ሊመልስ ካልቻለ፤ ደረጃ በደረጃ ትግሉን ወደ ሁለተኛው እርከን (ህዝባዊ እምቢተኝነትና አመፅ) በማሳደግ፤ ህዝብ ለአገዛዙ ተገዢ ባለመሆን፣ ባለመተባበርና፣ ጫና በመፍጠር፤ አገዛዙ የህዝብን ጥያቄ መመለስ እንዲችል ማስገደድን ያካትታል። ይህም ካልሆነ ደግሞ፤ ሠላማዊ ትግሉን ወደ ሦስተኛውና የመጨረሻው እርከን (ሥርዓቱን ማስወገድ) አሸጋግሮ የተለያዩ የሰላማዊ ትግል ህዝባዊ እርምጃዎችን በመተግበር፤ ለአገዛዙ በህይወት መኖር ወሳኝ የሆኑ ቋሚ ዘንጐቹን አሽመድምዶ ከጥቅም ውጭ በማድረግ፤ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድን ያካትታል። ሰላማዊ ትግል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ የሚኖረው፤ ብሎም ስኬታማ የሚሆነው፤ 1ኛ መነሻውና መድረሻው ቀጥተኛና ግልፅ በሆነ ሁኔታ ለህዝብ የተገለፀ ሆኖ ሲገኝ፤ 2ኛ ማንኛውም የሚመለከተው አካል ሁሉ በቀላሉ እንዲገባውና የጠራ አቋም እንዲኖረው ለማስቻል፣ የችግሩን መሰረታዊ ምንጭና የትግሉን ምክንያት ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን፤ 3ኛ እውነታዎችን ብቻ መሰረት በማድረግ የሚታዩ ነባራዊ ሁነታዎችን በግልፅ ማስተጋባት ሲችል፤ 4ኛ ጥልቅና ውስብስብ የትግል ስትራተጂዎችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚተገብር ሲሆን፤ 5ኛ ጉዞው ከፍተኛ ትእግስትን፣ አርቆ አሳቢነትንና፣ ጥበብን የሚጠይቅ እልህ አስጨራሽ መሆኑን የተረዱ ጠንካራ መሪዎችንና አንቀሳቃሾችን በውስጡ ያቀፈ ሆኖ ሲገኝ፤ እንዲሁም ሌሎች በርካታ መሰል ብቃቶችን ያጎለበተ ሲሆን ብቻ ነው። ሰላማዊ ትግል በዋነኝነት ቅንነትንና የሚጨበጥ ተስፋን የተሞላ፤ ህዝብን መአከል ያደረገ መሆን ይኖርበታል።
በአለማችን የህዝብን እምቅ ሃይልና ወሳኝነትን የሚያረጋግጡ ብዙ የተሳኩ የህዝብ ሰላማዊ ትግሎች ተካሂደዋል። በህንድ በታላቁ ማሃተመ ጋንዲ መሪነት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1947 የተካሄደውና ህንድ ከእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ ካስቻላት ሰላማዊ ትግል ጀምሮ፤ በአሜሪካን በ1960ዎቹ በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ መሪነት የተደረገው የጥቁር ህዝብ ትግል፤ በደቡብ አፍሪካ በ1980ዎቹ የአፓርታይድ ስርዓትን የሰባበረው፤ በፊሊፒንስ በ1986 ለአምባገነኑ ፈርድናንድ ማርቆስ ውድቀት ምክንያት የሆነው፤ በፖላንድ በ1989 የኮሚኒስት ፓርቲውን ከስልጣን ያስወገደው፤ በታይላንድ በ1992 የወታደራዊ አገዛዙን ያንኮታኮተው፤ እንዲሁም በቅርቡ በቱኒዚያና በግብፅ የተካሄዱት የህዝቦች ሰላማዊ ትግሎች እንደምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። በማንኛውም የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሙሉ ስልጣኑና ጉልበቱ የሚገኘው በህዝብ ዘንድ ብቻ ነው። በአሜሪካን አገር ኒውዮርክ ከተማ የሚገኘው የአልበርት አንስታይን ኢንስቲቱት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጂን ሻርፕ በማንኛውም መንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ የህዝብ ወሳኝ ተፅዕኖንና መሪዎች ያለህዝብ ህልውና እንደሌላቸው ለማስገንዘብ፤ “ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ” በተሰኘው መፅሃፋቸው በተጨባጭ እንዳሰፈሩት፤ “መሪዎች በራሳቸው ታክስ ሊሰበስቡ፣ ጨቋኝ ህጎችን በህዝብ ላይ ሊጭኑ፣ …፣ ኬላዎችን ሊቆጣጠሩ፣ ገንዘብ ሊያትሙ፣ መንገዶችን ሊገነቡና ሊጠግኑ፣ ገበያዎች በሚፈለገው መጠን አቅራቦት እንዲኖራቸው ሊያስችሉ፣ … ፣ የጦርና የፖሊስ ሰራዊቶችን ሊያሰለጥኑ፣ … አይችሉም።”፤ “ይህንን በተግባር የሚፈፅምላቸው ህዝብ ነው። ህዝብ ይህንን አገልግሎቱን እምቢኝ ካለ አምባገነኖች ፈፅሞ መምራት አይቻላቸውም።” ብለዋል።
ይሁን እንጂ አምባገነኖች ህዝብ ታዛዥ አገልጋያቸው ሆኖ እንዲኖርና በስልጣናቸው መቆየት እንዲችሉ፤ ከመከፋፈል፣ ከማስፈራራትና፣ ሰላም ከመንሳት ጀምሮ፤ እስከ ማሰቃየት፣ ማሰርና፣ መግደል ድረስ የሚችሉትን ጭካኔ ሁሉ እንደሚፈፅሙ የሰላማዊ ትግል መሪዎች ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ ነው። አምባገነኖች ምንግዜም አምባገነኖች ናቸው። የህዝብ አደራን ተቀብሎ የመሪነት ሃላፊነትን መረከብ ደግሞ ከምንም በላይ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ማንኛውም በአመራር ደረጃ ለማገልገል ዝግጁ የሆነ የነፃነት ታጋይ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ስር ታቅፎ ለመጓዝ ከመወሰኑ በፊት፤ ድርጅቱ የሚከተለው የትግል ስልት ምንነትን ጠንቅቆ ማወቅና እርሱም በርግጠኝነት የሚያምንበት መሆኑን ከጅማሮው ማረጋገጥ፤ ብሎም እስከመጨረሻው ያለማወላወል አብሮ ለመጓዝ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል። በተለይ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ይህ አይነቱ ቁርጠኝነት የበለጠ ወሳኝ ነው። አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለመጠበቅ የሚያደርሱት በደል ከትግል አጋሮቹ የሚነጥለው ሳይሆን፤ የበለጠ የሚያጠነክረውና ለተነሳለት አላማ ከግብ መድረስ እስከመጨረሻው ፀንቶ እንዲታገል ብርታት ሊሆነው ይገባል። የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች በእንዲህ አይነቱ ሰላማዊ የህዝብ ትግል የመሪነቱን ድርሻ ለማበርከት እስከፈቀዱ ድረስ፤ መሰናክሎች በተፈጠሩ ጊዜ ተጣድፈው ያልተገባ ውሳኔ ላይ ከመድረስ ይልቅ፤ ፀንተው ከህዝብ የተቀበሉትን ሃላፊነት ከዳር የማድረስ ግዴታና ሃላፊነት አለባቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝብን፤ በዋነኝነት ደግሞ ተከታዮቻቸውንና የሚመሩትን ድርጅት፤ የሚከፋፍሉ ማንኛውም ተግባራትን ላለመፈፀማቸው ከጅምሩ እርግጠኞች መሆን ይኖርባቸዋል። በነገራችን ላይ ከላይ በስም የጠቀስኳቸው ሶስት ቆራት ታጋዮቻችን እዚህ የዘረዘርኩት ሃላፊነቶቻቸውን በሚገባ ጠንቅቀው እንደሚረዱ ሙሉለሙሉ የማውቅ መሆኔን ላረጋግጥ እወዳለሁ። እነዚህ የነፃነት ታጋዮች በውስጣቸው የታመቀውን ቁርጠኝነት ማሳየት የቻሉ፤ የወያኔ አፓርታይድ ሥርዓት የሚያደርስባቸው ከመጠን ያለፈ በደልና አፈና የሚከተሉትን የትግል መስመር በሚፈለገው መጠን ማራመድ እንዳይችሉ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ እንቅፋት ቢሆንም ይህንን ከበቂ በላይ የመቋቋም ብቃቱ ያላቸው፤ ነገር ግን ይህንን በጋራ ለመመከት የሚችል፤ ጠንካራ የተቃዋሚ ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት፤ ራሳቸውን አምነውና ፈቅደው ወደ ችግር ለመግፋት የተገደዱ የምንግዜም ጀግኖቻችን ናቸው። የሃገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚያሳየን፤ በቅንጅቱ ጊዜ የታየው የመሪዎች አለመግባባትና ለአንድነትና ለመኢአድ መፍረስ ዋንኛ መሰረቱ (የተነገረው ምክንያት ምንም ሆነ ምን) ይሄው ችግራችን መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል። ይህን ሁልጊዜ የሗሊት የሚጎትተንን ችግር በመፍታት ረገድ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶችና፣ ሌሎች ያገባናል የሚሉ አካላትም የየራሳቸው ሃላፊነቶች ይኖሯቸዋል። ሁሉም ከራሳቸው የግል ፍላጎትና አስተሳሰብ ይልቅ፤ ለትልቁ ሃገራዊ የነፃነት ትግል ስኬት የበለጠ ስፍራ በመስጠት፤ የችግሩን ምንጭ በሚገባ አጢነው ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግደታና ሃላፊነት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል። ልብ ያለው ልብ ይበል!
ማጠቃለያ
አበው “ነገር በምሳሌ …” እንዳሉት፤ ማጠቃለያ ይሆነኝ ዘንድ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2011 በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ስለተካሄደው ህዝባዊ አመፅ (የአረብ ስፕሪንግ) ትንሽ ላውጋ። ቱኒዚያ የአረብ ስፕሪንግ ጀማሪዋ ሃገር መሆኗ ይታወቃል። የህዝብ አመፁ በቱኒዚያ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀና አምባገነኑ ቤንአሊም ከተባረረ በኋላ፤ ይህ የህዝብ አመፅ ወደ ግብፅ ሊሄድ ይችላል ይሆን? በሚለው ጥያቄአዊ ሃሳብ ላይ የፖለቲካ ጠበብቶች ብዙ ብለው ነበር። በተለይ “ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም ስለዚህ የህዝብ አመፁ እንደ ቱኒዚያ ሁሉ በግብፅ ሊከሰት አይችልም።” የሚለውን አስተሳሰብ ደግፈው ምክንያታቸውን ሲደረድሩ የነበሩ በርካቶች ነበሩ። “ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም” የሚል ሃሳባቸውን ለማስረዳት ሲጠቅሷቸው ከነበሩት ምክንያቶች መካከል፤ “በቱኒዚያ ህዝብ መካከል ያለው የሙስሊሙና የክርስትናው ሃይማኖቶች ውጥረት ግብፅ ካለው እጅግ በጣም ያነሰ ስለሆነ የግብፅ ህዝብ አንድ ሆኖ ሊታገል አይችልም፤ ቤንአሊ እንደ ሙባራክ ጨካኝ አይደለም፤ ሙባራክ ጠንካራ የጦር ሰራዊት አለው ስለዚህ በቀላሉ ከህዝብ መካከል ጥቂቶችን ገድሎ ትግሉን ባጭሩ ሊቀጨው ይችላል፤ ቱኒዚያዎች ከግብፆች የበለጠ የተማሩ ናቸው፣ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችንም ቱኒዚያዎች በስፋት ተጠቃሚዎች ስለሆኑ ግብፅ ውስጥ እንደ ቱኒዚያ ያለ አመፅ ሊከሰት አይችልም፤ ሌላም ሌላም…” እያሉ ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል። ይታዩአቸው ከነበሩት ምክንያቶች መካከል፤ ግብፆች በሙባረክ አምባገነናዊ አገዛዝ ለአመታት ብዙ ተረግጠዋል፣ ተጎድተዋል፣ ተበዝብዘዋል፤ ለአመታት እነርሱ (የግብፅ ህዝብ) በድህነት እየማቀቁ ሳሉ ጥቂት ግለሰቦች በሃብት ሲትረፈረፉ ምንም እርምጃም ሆነ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረው አያውቁም፤ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ነገር ግን ፍፃሜው ላይ የታየው እውነታ፤ ግብፆች እጅግ ማራኪ የሆነ የህዝብ ትብብርና ሰላማዊ ተጋድሎን በአደባባይ ለአለም ህዝብ በሚገባ ማሳየታቸውና፤ ‘አስፈሪና ጨካኝ፤ በአለማችን ከሚገኙ የሃገር መሪዎች ዋንኛ የአሜሪካንና የምዕራባዊያን ወዳጅና የቀኝ እጅ’ እየተባለ ሲነገርለት የነበረውን፤ የሙባረክ ስርዓት ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረው መጣል መቻላቸው ነው። በዚህ ዙሪያ ምሁሮቹና ፖለቲከኞቹ ያለማስተዋል ችላ ብለውት የነበረው ዋናው ቁምነገር የህዝብ እምቅ ሃይል በአምባገነኖች አስፈሪነት ሊሟሽሽ ፈፅሞ እንደማይችል ነበር። የወያኔ ቡድን ከተፈጠረ ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ ስርየሰደዱ ችግሮችንና በደሎችን ሲፈፅም ኖሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ የተጫነበት ህመም ከግብፅና ከቱኒዚያ እጅግ የከፋ ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ 11ኛው ሰአት ላይ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልፅ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ግብፆቹ ሁሉ፤ የወያኔ ጦር ሰራዊት መብዛት፤ ፍቅር እያለው በዘር በሃይማኖት ሳይወድ መከፋፈሉ፤ ጥቂቶች ሲበለፅጉ እርሱ ግን በድህነት መማቀቁ፤ በተቃውሞ ሰልፍ ብሶቱን ለማሰማት በወጣ ቁጥር በአጋዚው የወያኔ ሃይል በተደጋጋሚ በግፍ መጨፍጨፉ፤ መታሰሩና፤ ስቃይን መቀበሉ የህዝብን እምቅ ሃይል በበለጠ ያጎለብትለት እንጂ ሊያዳክመው ፈፅሞ አይቻለውም።
ነገር ግን በግብፅ የተደረገው የተሳካ አመፅ ዝም ብሎ በመላምት የመጣ አይደለም። ይልቁኑስ የአመፁ መሪዎች፣ አስተባባሪዎችና፣ አንቀሳቃሾች እጅግ በጣም በሳል፣ ጥበብ፣ ትእግስት፣ ፅናት፣ ቁርጠኝነትና፣ ቅንነት በደማቸው የፀረሰ በመሆናቸው፤ የሙባረክ ሥርዓት ለሃገርና ለህዝብ የማይበጅ አደጋ መሆኑን በመረዳት እውነታውን ለህዝብ ስላመላከቱትና በተግባርም አንድ ሆነው ስላሳዩት፤ ብሎም ህዝብ ወዶና በቃኝ ብሎ ትግሉን እንዲቀላቀል ስላስቻሉት እንጂ። የኛም ፖለቲከኞችና የድርጅት መሪዎች ፍፁም የሆነ የአመለካከትና የአካሄድ መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ፤ የህዝብ ቁስል ሊያማቸው፤ እውነታውንም ሊነግሩትና በአንድ መአከል ሥር የሚመራ፤ ለሁሉም እኩል የሆነ፤ ሁሉም ያለልዩነት የሚፈልገውና የሚደግፈው ተቋም መስርተው፤ ቀናይነታቸውንና በእውነት ለነፃነቱ መሥዕዋትነት ሊከፍሉ ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር በማስመስከር፣ ከዚህ እጅግ የመረረ ስቃይና መከራ ሊታደጉት ይገባል። ከላይ በዝርዝር ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ በእርግጥም የሠላማዊ ትግል በሃገራችን ጅማሮው በከፊል ታይቶ ይሆን እንጂ ተገፍቶበት አያውቅም። በእርግጥም በሃገራችን የሠላማዊ ትግል ታሪክ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት አብይ እርምጃዎች መካከል፤ በመጀመሪያው ደረጃ ከሚገኙት በርካታ እርምጃዎች ውስጥ ከሶስት የማይበልጡትን (ለዚያውም በከፊል) ከማከናወን ያለፈ ምንም አይነት ህዝባዊ እርምጃ ተወስዶ አያውቅም። በትጥቅ ትግሉም ቢሆን ከዚህ የተለየ ምንም ተከናውኖ አያውቅም። ይሁንና የሠላማዊ ትግልም ሆነ ሌላ ህዝባዊ ትግል የመጀመሪያ ደረጃ እንኳ በቅጡ ባልተተገበረበት ሁኔታ፤ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻችን ገና ከጅምሩ፤ አበው “ብቻውን…” እንዳሉት፤ የተለዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማፈን መትጋታቸው፤ የትግል ስልታቸውን ያለበቂ ጥናት በመላምት ቅንነት እየለዋወጡ መዋዠቃቸው፤ ብሎም የፖለቲካ አክቲቪስቶችን ጨምሮ፤ ሚዲያዎቻችን ይህንኑ ለማናፈስ መጣደፋቸው፤ እንዲሁም ሰላማዊ ትግልምሆነ ሌላው “ከእንግዲህ አበቃለት” የሚል የተዛባ መልዕክትን ባደባባይ ለመስበክ መሞከራቸው፤ ‘አተርፍ ባይ አጉዳይ’፤ ‘አላዋቂ ሳሚ…’፤ ‘የጅብ ችኩል…’፤ አልያም ‘ጉልቻ ቢቀያየር…’ እንዳይሆን ስጋቱ አለኝ። ነገር ግን ግቡ ነፃነት እስከሆነ ድረስ፤ ነባራዊ ሁኔታዎችን በስፋትና በጥልቀት መርምረው፤ በጋራ የትብብር መንፈስ በአንድነት ለመጓዝ ቢሞክሩ ይበጃልና፤ የየግል ፍላጎታቸውን ለጊዜው ወደጎን ትተው፤ ሰፊውንና ትልቁን ሃገራዊ ራዕይን አስቀድመው በመተባበር፤ ሃገራችንን ከጥፋት፤ ህዝባችንን ደግሞ ከባርነት ነፃ ለማውጣት፤ ትግላቸውን ለማቀናጀት በአንድ መአከል ወደሚመራ ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ ተቋም መምጫው ጊዜ አሁንና አሁን ብቻ መሆኑን ተረድተው፤ አፋጣኝ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እማፀናለሁ። ሃሳቤን ለመረዳት ፅሁፌን በትዕግስት ስላነበባችሁልኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Email: [email protected]