“ፊሽካው ተነፋ” የትኛው ፊሽካ?
ከዘላለም ሽፈራው
መሪ ተዋናይ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ እንደ ኮማንደር
አርበኛ ዘምነ ካሤ እንደ ጦር ሜዳ ቃል አቀባይ
መሣይ መኮነን እንደ ዜና አቅራቢ
ቦታ ወልቃይት አንዲ ትግራይ አንዲ ጎንደር
በተወለድኩበትና ባደኩበት አካባቤ ወልቃይት ጠገዴ ፊሽካው ተነፋ (ነፋ) ሲባል ሁለት ትርጉም አለው። አንደኛው ፊሽካው ተነፋ ሲባል ለአንድ ተልእኮ፣ ሥራና ግዳጅ የመጠንቀቅ፣ የመዘጋጀት፣ የመጀመርና የመጨረስ ምልክት ነው። ሌላው ትርጉም ፊሽካውን ነፋ ወይም ተነፋ ማለት ውሸቱን ጀመረ፣ መቀደድ ጀመረ፣ የሀሰትና የፈጠራ ወሬውን ነፋ፣ አስተጋባ ማለት ነው። ሰሞኑን ኮማንደር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ኃይል በወልቃይትና ትግራይ ግዛት ወታደራዊ ጥቃት አድርሶ 50 የወያኔ መከላከያ አባላትን ገሎ፣ ከ60 በላይ አቁስሎ አካባቢውን ተቆጣጥሮ ወደ ጎንደር እየገሰገሰ ስለመሆኑ በኢሳት ሰበር ዜና በድምጸ መረዋው ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን እቅራቢነት ተነግሮናል። በተከታታይ ቀናት ጦርነቱ እንደቀጠለ በመግለፅ ቀላል የማይባል የወያኔ ጦር በአርበኛች ግንቦት 7 እንደመከነና እንደተገደለ በመግለፅ፣ የግንባሩ ቃል አቀባይ አርበኛ ዘመነ ካሤ እንዳሉት ይጠበቅ የነበረው ጦርነት ተጀምሮአል፣ ማለት ፊሽካው ተነፍቶአል፣ ከዚህ በኋላ በውጭና በውስጥ ያላችሁ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተቀላቀሉን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። የነጋሪቱ ወሬ እንደ ተበሰረና እንደተጎሰመ ኮማንደሩም ሸሚዛቸውን ጠቅልለው በሚሪላንድ ግዛት በኮሌጅ ፓርክ ከተማ ኢትዮጵያውያን ባዘጋጁት የእግር ኳስ ጨዋታና ባህላዊ ዝግጅት ላይ በድል አድራጊነትና በአሸናፊነት ስሜት ሲንጎራደዱ ታይተዋል።
ዜናው በዚህ ግፈኛና ከፋፋይ አገርና ትውልድ አጥፊ የሆነ የህዋት አምባገነን መንግሥትን የመውደቅ ጉጉትና ናፍቆት ላለው ኢትዮጵያዊ ዜናውን ከላይ ሲያዩት ያስደስታል። ነገር ግን ጦርነት ተካሄደበት የተባለበትን ቦታ ለሚያውቅ፣ አካባቢው ከኤርትራና ከሱዳን ድንበር ግንኙነት አንፃር ወያኔ ከፍተኛ የጦር ኃይል ያለው በዚሁ ክልል መሆኑን ለተረዳ ሁሉ ዜናው ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ግልጽ ነው። የምእራባውያን፣ በተለይ የዩናይትድ ስቴት ሽርካ በሚል ከግብፅና ከደቡብ አፍሪካ ባልተናነሰ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያስታጠቁትና ሁለገብ ወታደራዊ ሥልጠና የሰጡት ቢኖር ወያኔ ነው። የወያኔ ዋናው ቤዝ ደግሞ ይህው ትግራይ ክልል ነው። ወያኔ ወልቃይት ጠገዴንና አብደራፊን በጉልበት ከጎንደር ግዛት ነጥሎ በትግራይ ክልል ከአደረገ በኋላ አካባቢው የወታደር ቀጠና እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት ያለበት ክልል ነው። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ኃይል ከኤርትራ ተነስቼ፣ በክረምቱ ተከዜን ተሻግሬ፣ በዚህ ቀጠና ጥቃት ሰንዝሬ የወያኔን ሠራዊት ደምስሼ ድል አደረኩ፣ ትግራይ ገብቼ የጦርነት ትርኢት አሳየሁ አለን። ግንቦት ሰባት ይህን ታሪክ እንዴት ፈጠረው? ከምን ተነስቶነው ይህን የፈበረከው? የአካባቢው ተጨባጭ ታሪክ ምንድንነው?
እውነተኛው ነገር ሳንጃ፣ ዳንሻ፣ ላይና ታች አርማጭሆ፣ ማይ ፀብሪና አዳርቃይ የአካባቢው ህዝብ በጎበዝ አለቃ እየተመራ የሚደርጋቸው ውጊያዎችና አመፆች አሉ። ይህ ግን በፍፁም ከግንቦት ሰባትና ከኤርትራ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም። በዚህ ንቅናቄ ተጋድሎ ያላቸው መሪዎች አባቶቻቸውና የሥጋ ዘመዶቻቸውን በወያኔና ሻቢያ የተገደሉና ሰለባ የሆኑ የቆረጡ ጎንደሬዎች ናቸው። እነዚህን ብረት ያነሱ ወገኖች የማያውቅ የአካባቢው ተወላጅ የለም።
ወያኔ ሥልጣን ከመያዙ በፊትና በኋላ ከፋኝ በሚል እየተንቀሳቀሱ አንዴ ሲጠናከሩ፣ አንዴ ሲዳከሙ ባለፉት በርካታ ዓመታት ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንት እነዚህ ኃይሎች ከሱዳን እንደ ተለመደው በኮንትሮባንድ የመሣሪያ ግዥ አድርገው ወደ ወልቃይት ሲገቡ ከወያኔ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የከፋ ውጊያ አድርገዋል። በውጊው ቀላል የማይባል ህይወት በሁለቱም ኃይሎች አልፏል። የውጊያው ዜና በጎረቤት ሀገር ኤርትራና ሱዳን እንዲሁም እድሜ ለቴክኖሎጂ ወዲያውኑ ጀርመን፣ ካናዳና አሜሪካ ያለን ተወላጆች እሳት ዜና ብሎ ታሪኩን በርዞ ከማቅራቡ በፊት ሰምተነዋል። ይህ ግጭት ሲካሄድ እንኳን ሠራዊት ወፍ ከኤርትራ አልበረረም ወይም አልመጣም። ግጭቱ ሲካሄድ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የውጊያው ቃል አቀባይ ዘመነ ካሤ ኤርትራ ነበር። የግንባሩ ኮማንደር ደግሞ ሜርላንድ ነው የነበሩት።
እነ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋና ኢሳት የተሳሳቱት በሁለት ነገር ነው። አንደኛ ባለፉት አርባ ዓመት ወልቃይት ጠገዴና አርማጭሆ የጦርነት ቀጠና ሰለነበሩ ሁሉም ድርጅቶች ነፍጥ ያነሱበት የጦርነት ቤዛቸው ስለነበር በዚሁ ጦርነት የተሰደድንና አሁን በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና ካናዳ የምንኖር በርካታ ተወላጆች የአካባቢያችንን ሁኔታ በየጊዜው እንደምንከታተል ግምት አልሰጡትም፣ ወይም ንቀውታል። በእነርሱ ግምት ወልቃይት ጠገዴ ሲባል እንደ ሩቅ ምስራቅ አፍሪቃ ወይም ኤሽያ የመንደር ወሪ ዜናው ተሰምቶ የሚታመን አድርገውታል።
ሁለተኛው በዚህ የፈጠራ ወሬ ውጭ ያለውን ህዝብ በመጀንጀን ከሚደረገው የገንዘብ ማሰባሰብ ይልቅ እውነቱንና መሬት ላይ ያለውን የሚውቀው ህዝብ ነገ ምን ይለናል ብለው ለህዝብ ግንዛቤ፣ እውቀትና ትዝብት ከበሬታ አልሰጡም። ይህም እውነታው ሲወጣ ድርጅቱን የሚዋርድ ነው።
የወልቃይት ጠገዴና የጠለምት ታጣቂዎች በወያኔ ላይ ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ዛሬ ከወያኔ ጋር ይዋደቁ እንጅ ትናንት ሻቢያ በእነርሱ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይና በህዝቡ ላይ የፈፀመውን በደል በፍፅም አይረሱትም። እንደ ኤርትራ መንግሥትና ሻቢያ ለኢትዮጵያ ህዝብና ሉአላዊነት ክፉ እምነት ያለው የለም። ስለዚህ የነዚህን ጀግኖችና አርበኞች ተጋድሎ ከሻቢያና ምንጭንና ወታደራዊ መሰረቱን ኤርትራ ካደረገ ቡድን ጋር ለማያያዝ መሞከሩ ታሪካዊ ውንብድና ነው ።
ሀገር በፕሮፕጋንዳ ሥራ ብቻ ነፃ አይወጣም። ፕሮፕጋንዳ መሬት ላይ ካለው ሥራ ጋር ካልተዋሀደ ውሸታም፣ ቱሪ ናፋ፣ ፊሽካውን ነፋ፣ ጥሩምባውን ነፋ ያሰኛል። ይህ ስም ደግሞ ከተደጋገመ ለግንቦት ሰባትና ባጠቃላይ ለትግሉ ጥሩ አይሆንም።
ሌላው በሰሜን ጎንደር ተዋጊ ኃይል ይዞ ለመንቀሣቀስ ሁለት መሠረታዊ ጉዳይ ያስፈልጋል፤ አንደኛው፣ ኢትዩጵያዊነትን ያስቀደመ መሆን፣ ሁለተኛ፣ የአካባቢውን ህዝብ ማወቅ፣ ማመንና ማክበር።
በእኔ እምነት ግንቦት ሰባት ሁለቱንም አያሞላም። ግንቦት ሰባት የተቀመረውና የተደራጀው ኤርትራ ያሉ ከኢትዮጵያ ተገንጥለን የየራሳችንን ትናንሽ አገራት እንገነባለን የሚሉ ነፃ አውጭ ድርጅቶችን አባላት መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ስለዚህ ግንቦት ሰባት ለኢትዮጵያን ነፃነትና ለአንድነት ይቆማል፣ ታግሎ ለድል ያበቃል ለማለት ያስቸግራል።
ከኤርትራ ተነስቶ በወልቃይት ጠገዴ ላይ ወታደራዊ ጥቃት አድርሻለሁ ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት በኢሳት ያቀረበው ሰበር ዜና ውሸትና ቱሪ ናፋ መሆኑን አረጋግጨ ለወገኖቼና ለኢትዮጵያውያን ለማሳወቅ ይህን ለመፃፍ ስነሳ ስሜቴ ተነክቶ ስለ ግንቦት ሰባት ምንነት ለመዳሰስ ሞክሬአለሁ። ሻቢያ አሁንም ኤርትራ ነፃ አልወጣችም፣ የኤርትራ ነፃነት የሚረጋገጠው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ስትፈርስ ነው የሚል አቋም ያለው ድርጅት ነው። ለዚህም ሻቢያ ዘጠኝ ነፃ አውጭ ድርጅቶች አደራጅቶ የኢትዮጵያን ህዝብና የተቃውሞውን ጎራ ከፋፍሎ የበጠበጠልንን መርዝ አይናችንን ጨፍነን እንድንጠጣት ለማድረግ ግንቦት ሰባትን እየተጠቀመ ነው። ትኩረታችን፣ ኃይላችንና ጉልበታችን በወያኔ ላይ እንዳይሆን ሻቢያና ግንቦት ሰባት አዲስ አጀንዳ ሰጥተውናል።
በመጨረሻ ያለኝ መልእክት ለወልቃይት ጠለምትና ጠገዴ ማህበርና ለጎንደር ህብረት ማህበር ነው። ላለፉት አርባ አመታት ጎንደር፣ በተለይ ሰሜን ጎንደር የጦር አውድማ ነበር። ነፃ እናወጣሀለን ያሉት ድርጅቶች የከፋ ጊዜ ሲመጣ ጥለውት በመሸሽ ለደርግና ለወያኔ ጨካኞች አሳልፎ በመስጠት ህዝቡን አስጨፍጭፈውታል። ወያኔ መሬቱን አሳልፎ ለሱዳን ሰጥቷል። ሰፊ የጎንደር መሬት ወደ ትግራይ ተከልሏል። ይህን ግፍ በመቃወምና ወገናችን ነፍጥ ካናሳ ቆይቷል። ይህን ሁላችንም ስናበረታታና ስናግዝ ነበርን። ግፍና በደል ባለበት ቦታ ሁሉ እምቢተኛነት፣ ትግልና አመፅ አለና ወገኖቻችን በዚህ ደረጃ የሚደርጉት መፋለም የሚኮራ ነው። ነገር ግን ይህን የህዝባችንን አመፅና ትግል ግንቦት ሰባት በፈጠራና በተጭበረበረ ወሬ ለመጥለፍ እየሞከረ ይገኛል። ህዝባችን ለመብቱና ነፃነቱ የሚደርገውን ተጋድሎ በቦታው የሌሉ የግንቦት ሰባት አርበኛ ነን ባዮች እነርሱ እንዳደረጉት በማስመሰልና በዜና በማቅራብ ለህዝባችንና ለእኛ ያላቸውን ንቀት አሳይተዋል። ስለዚህ ልሣንና ድምፅ ልንሆናቸው ስለሚገባ በአስቸኳይ ማህበሩ መግለጫ እንዲያወጣ ያስፈልጋል። ወገናችን ነገ ሽብርተኛ ተብሎ በአይሮፕላን እንደ ሱማሌና የመን እንዲደበደብ የሚስደርግ ሥራ እየተሰራ ስለሆነ ይህን በተመለከተ ጠንካራ መግለጫ በማውጣት ለህዝባችሁ ድምፅ እንድትሰጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አደርጋለሁ።
ኢትዪጵያ ለዘላለም ትኑር!