ቄራዎች ድርጅት በልኳንዳ ነጋዴዎች ምክንያት አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አስታወቀ

ቄራዎች ድርጅት በልኳንዳ ነጋዴዎች ምክንያት አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠየቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት የዘንድሮው ሰኔ ፆም ሲፈታ አንድ ቀን ሲቀረው በልኳንዳ ነጋዴዎች ምክንያት አገልግሎቱ እንደተስተጓጎለበት አስታወቀ፡፡

ለ2,800 እንስሳት የዕርድ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ እንደነበር፣ ለእርድ አገልግሎት የቀረቡት ግን 900 እንስሳት ብቻ እንደሆኑ፣ ይህም ለሕገወጦች በር መክፈቱንና መንግሥትም ከአገልግሎቱ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ማጣቱን  የድርጅቱ ዋና ሥራ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህንን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በቁም እንስሳት ንግድ አዋጅ በከተማው ክልል ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ባዘጋጀው የተግባር ምዕራፍ ላይ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ገቢ በማሳጣት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ጤንነቱ ያልተመረመረ ሥጋ በመብላት ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጥ ማድረጉ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ 

ድርጅቱ ዕቅዱን ያላሳካው የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ችግር ሳቢያ እንስሳቱን ከመግዛት በመቆጠባቸው፣ በዚህም የተነሳ የንግድ ቤቶቻቸውን ዘግተው ለኅብረተሰቡ የሽያጭ አገልግሎት መስጠቱን እርግፍ አድርገው በመተዋቸውና በዚህም ምክንያት የሥጋ እጥረት በማስከተሉ ነው፡፡

 ከዚም በተጨማሪ ቄራዎች ድርጅት ለዕርድ አገልግሎት የ2,000 ብር ዋጋ ጭማሪ እንዳደረገ የተነዛው አሉባልታ፣ ለልኳንዳ ንግድ ቤቶች መዘጋትና ነጋዴዎቹም እንስሳቱን ላለመግዛት ለማንገራገራቸው ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት ለዕርድ አገልግሎት የሚያስከፍለው በአንድ እንስሳ 230 ብር ብቻ እንደሆነ፣ ይህም የተመረተውን ሥጋ በተሽከርካሪ እስከ ልኳንዷ ቤቶች ድረስ የማጓጓዙንም ሥራ እንደሚያካትት፣ ከዚህ ውጪ ግን ምንም ዓይነት ጭማሪ እንዳላደረገ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ማስታወቃቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ አገልግሎቱን የሚሰጠው የንግድ ፈቃድ ላላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተቋቋመው ጤናማነቱ የተረጋገጠ የዕርድ አገልግሎት ለከተማው ነዋሪዎች መስጠት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለተለያዩ ጉዳዮች ማለትም ሠርግ፣ ተዝካር፣ ወዘተ ላላቸው ወገኖች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር እንዲቀጥል እናበረታታለን፡፡ ከክፍያ አንፃር ግን ከነጋዴው የተለየ ጭማሪ ሳይደረግ ነው የዕርድ አገልግሎቱን የሚያገኙት፤›› ብለዋል፡፡

በተረፈ ለድርጅቱም ደረሰኝ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው፣ በተለይ እንስሳት ከገበያ ወደ ቄራ በሚጓጓዙበት ጊዜ ሲሞት ካሳ የሚከፈልበት አሠራር እንዳለ፣ በዚህም የተነሳ ደረሰኝ ላይ የሚታወቅ ሁኔታ ካለ በዚያው ልክ እንደሚከፈል፣ ይህ ባለመሆኑ የተነሳ ግን አንዳንድ ጊዜ ከዋጋው በላይ እየተጠየቀ ድርጅቱን ላላስፈላጊ ወጪ እንደተዳረገ አልሸሸጉም፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክተው እንዳብራሩት፣ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ባለፈው ሳምንት ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ስብሰባ አድርገው ልኳንዳ ነጋዴዎች ለገዙት በሬ ደረሰኝ እንደማይፈልጉ፣ ምክንያቱ ደግሞ ያለደረሰኝ መሸጥ ስለሚፈልጉ ነው የሚል መረጃ በተባራሪ ልኳንዳ ነጋዴዎች ጆሮ ይደርሳል፡፡ 

ይህ ጉዳይ ተጋግሎ እየመጣ ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ደረሰኝ ካላገኙ ከብት እንደማይገዙ በልኳንዳ ነጋዴዎች ዘንድ ጎልቶ ታየ፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ የማኅበሩ ቢሮ ድረስ እየመጡ ‹የሠራችሁልን ነገር የለም፣ በመብታችን ትደራደራላችሁ፡፡ እንዲያውም ማኅበሩን እናፈርሳለን› የሚል አቋም እንደያዙ ነው ምክትል ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡

በዚህም ምክንያት ልኳንዳ ነጋዴዎች ደረሰኝ ወይም ለሕጋዊነታቸው ማረጋገጫ ካላገኙ እንስሳት መግዛት አንችልም በማለት በራሳቸው መንገድ ንግድ ቤታቸውን እንደዘጉ፣ ማኅበሩም እስከ ፆም ፍቺው ዕለት ድረስ የማረጋጋት ሥራ ቢያከናውንም ሊሳካለት እንዳልቻለ አቶ አየለ ጠቅሰው፣ ‹‹በዚህም ምክንያት የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ለተፈጠረው ችግር የከተማይቱን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ንጉሴ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀ ጉባዔ 5,000 የሚሆኑ እንግዶች እየተስተናገዱ ባሉበት፣ የሰኔ ፆመኞች ፆማቸውን ሲፈቱ የልኳንዳ ንግድ ቤቶችን መዝጋት በማንኛውም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ ምንም ዓይነት ችግር ቢኖርም መዝጋቱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ የታወቅንበት መቻቻል፣ ሰላምና ፍቅር ደፍርሶ ሌላ ነገር እንዲከስት ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር ስብሰባ ስለማድረጋቸው ለቢሮው የደረሰ ምንም መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በተረፈ በቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት ውስጥ በጉልበት የታጀበ ጣልቃ ገብነትንና ሕገወጥነትን እንዲቀር ለማድረግ እንታገላለን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መተጋገዝ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡