የኢኮኖሚ እድገታችን እዳ ከፋዮች
(አዲስ ከድሬዳዋ) መንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግና በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ኢንቨስትመንቶችን በማስተናገድ ኢኮኖሚው እያደገ ነው፡፡ ዋነኛው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የስራ እድል ፈጣሪ መንግስት በሆነበት ሁኔታ በመንግስት ሜጋ እና ትናንሽ ፕሮጄክቶች አማካኝነት ወደገበያው እየተለቀቀ ያለው ገንዘብና ከገበያው የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ልዩነቱ ሰፊ በመሆኑ የግሽበት ተጋላጭነታችን ከፍተኛ ነው፡፡ ባንድ ወቅት ከ40 ፐርሰንት በላይ ደርሶ የነበረው የሀገራችን የዋጋ ግሽበት አሁን ወደ ባለአንድ አሀዝ ግሽበት(ከ10 ፐርሰንት በታች) መውረዱ እንደትልቅ ስኬት እየተነገረ ነው፡፡ ለመሆኑ ቀድሞ ነገር ኢንፍሌሽኑ እንዴት ጀመረ፣ አሁንስ እንዴት ሊቀንስ ቻለ ኢንፍሌሽኑ የጀመረው በተደጋጋሚ እንደሚነገረው መንግስት በሚያስተገብራቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደገበያው እየለቀቀ ስለሆነ ነው፡፡ በኢኮኖሚስቶች የሚመከረውና መንግስት ኢንፍሌሽኑን ለማረጋጋት መውሰድ ያለበት እርምጃ በዋናነት ወደገበያው እየለቀቀው ያለውን ገንዘብ መቀነስ ነው፡፡ መንግስት ግን ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ያቀዘቅዝብኛል በሚል ተመራጭ እርምጃ አድርጎ አልወሰደውም፡፡ አንድ አመት በከፊል ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ቀጣይነት ግን አልነበረውም፡፡ መንግስት ይልቁንም በገበያው ላይ ያሉ ተጫዋቾች ላይ ቁጥጥሩን በማጥበቅ፣ ቁጠባን በማበረታታትና የግብር መሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ነው ችግሩን ለመፍታት የሞከረው፡፡ በእርግኑን ይህንን አማራጭ በመከተሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ሳይቀዛቀዝ ኢንፍሌሽኑን በእጅጉ መቀነስ ችሏል፡፡ ሆኖም ለዚህ የተወሰኑ ዜጎች ያለአግባብ ዋጋ እንዲከፍሉም ተደርጓል፡፡ ሁለቱን ልጥቀስ የመንግስት ሰራተኞች፡- በ1994 ዓ.ም. የነበረው 400 ብር የመግዛት አቅም በ2004 ከነበረው 1000 ብር ጋር ተመጣጣኝ በሆነበት ሁኔታ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ በእነኚህ አስር አመታት 250 ፐርሰንት ሊያድግ ይገባ ነበር፤ […]