“ያልተጻፈ መጻፍ ….“ የግጥም መድብል ወፍበረር ሲዳሰስ!
በኢዮብ ብርሃነ
በደራሲ ፊልጶስ ም. ወርቅነህ ተፅፎ የቀረበልን “ያልተጻፈው መጻፍ…..” የግጥም መድብል በ85 ገፆቹ ውስጥ 68 ግጥሞችን ሲያካትት ‘’መታሰቢያነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንልኝ!’’ ብሎ ለበቀለበት ማኅበረሰብ ችሮታል። ስለ ግጥም መድብሉ ውስጣዊ ይዘትና ትንታኔ ከመግለፄ አስቀድሜ ስለ ደራሲው ማንነት ማንሳቱ ሰናይ መስሎ ታየኝ። ፊልጶስን የማውቀው በተለያዩ መካነድሮች ወቅታዊና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ በሚያወጣቸው ጽሁፎቹና ግጥሞቹ ነው። በተባው ብዕሩ እኛነታችንን በገሃድ አውጥቶ ሕሊናችንን ሰርስሮ ይሞግተናል። ገዢዎቻችንን በመውቀስ ላይ ብቻ ካነጣጠረው ከተቃዋሚዎች ጎራ ፀሃፍት ለየት ባለ መልኩ “እኛስ ለአገራችን ቀናኢ የምናስብ ዜጎች ለምን ´ራሳችንን አናይም ?….. አንፈትሽም? ….ለምን ትግላችን እንደ ግመል ሽንት የኋልዮሽ ይሆናል?….. “ በሚል ዕይታ ዙሪያ ጽሁፎቹና ግጥሞቹ ያጠነጥናሉ:: የተቃዋሚዎች የትግል ስልት ላይ ገንቢና አራሚ ሂስ ይቸራል። በግጥሞቹ ገዥዎቻችንን ይሞግታል:: የሞራል ውድቀታችንን፣ የእኛነታችን የምንለው ክብራችን መኮስመኑን በገሃድ ይነግረናል።
መድብሎቹ ውስጥ የልቡን የተሰማውን ተናግሮና ተንፍሶ ሲያበቃ ”ለተጠቀምኩባቸው ያልተገቡ ቃላቶች አንባቢያንን ይቅርታ እጠይቃለሁ!” ይለንና ይሰናበተናል።
ደራሲ ፊልጶስ በስንኞቹ ውስጥ የአገር ናፍቆትን፣ የፍትሕ እጦትን፣ ፍርሃትና ተስፋን እናገኛለን። “ሞትን ለሚፈሩት “ በሚለው ግጥሙ መሰደድ ሞት መሆኑን በስንኙ እንዲህ ይነግረናል።
ሞትን ለሚፈሩት! ሞት መጣ ይሉኛል ቢመጣስ ምን ገዶኝ፤ ሀገሬ ሰው የላት የለ እሚያስጨንቀኝ። ለኔ ሲልስ ይምጣ ነገ ሳይል ዛሬ ድሮ ነው የሞትኩት ስሰደድ ካሀገሬ። መሰደድ መኖር ነው ይብላኝ ለሚሉት! ስደት ሞት መሆኑን ሳያውቁ ለኖሩት ሌላ ሞት ጠብቀው ሞትን ለሚፈሩት።
****ገፅ – 45 ላይ *******
ይህ ስንኝ ጠንከር ይልብኛል። ስደት ከማንነት ከቀዬ መፍለስ ብቻ ሳይሆን የማንነት መንተብንም ፍንትው አድርጎ ያሳየናል:: አገላለፁን ወድጄለታለሁ።
የመድብሉ ርዕስ የሆነው ”ያልተጻፈ መጻፍ…” ፍልስፍናዊ ይዘት አለው። የሁላችንንም የሰው ልጆች የመኖራችን ትርጉም፣ ዕጣፈንታ ክፍላችንን ሕይወት ምንድን ነው? መኖር ምን ማለት ነው? እስኮትላንዳዊው የብዝሃ ሕይወት ተመራማሪ ቻርለስ ዳርዊን ”To live means to exist & to survive” መኖር ማለት መቋቋምና መልመድ ማለት ነው ተቀራራቢ ትርጓሜው። ያለመዱትስ አልኖሩም ማለት ይሆን? ጥያቄውን ለሁላችሁም ትቼ ከስንኙ ልጋብዛችሁ።
“ያልተጻፈ መጻፍ…” ሕይወት… የሚሉትን፣ አስብ-አስብና ትላንትን-ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ-ጋር፣ አወጣ-አወርድና ብዕር-ወረቀቴን፣ አዘጋጀውና ሃ!…. ብዬ ልጀምር፣ ልከትብ እልና፤… ….ሕይወት – መነሻውን…. ….ሕይወት – መድረሻውን…. ….የመኖር – ትርጉሙን…. ማሰሪያ – መፍቻውን፣ ውሉን አጣውና፤…. ከመፀነስ በፊት፣ ”ምን ነበር እያልኩኝ?”…. ፈተና እገባና ከመሞት በኋላስ፣ ”ምን ይሆን እውነቱ?….መልሱ ያጥረኝና መልሼ እተዋለሁ…. ”ያልተጻፈ መጻፍ….” እኔ አልቻልኩምና።
****ገፅ – 3 ላይ*****
ሌላው ፍልስፍና አዘል ግጥሙንም “ሰማዩ ያለቅሳል” በማለት ዝናብ የሰማይ የብሶት መግለጫ ዕንባ ነው ይለናል:: በሌላ መነጽር ያስቃኘናል ደራሲው።
ሰማዩ ያለቅሳል! ሆድማ ሲብሰው መከፋት ሲያምሰው፤ ይከስላል ይጠቁራል ጭጋግ ይላበሳል። በሐዘን በእንጉርጉሮ በእዬዬ በእሮሮ፤ በሲቃ በዋይታ በሞገድ ብልጭታ፤ ገመናውን ገልጦ እህ ብሎ አምጦ፤ ሰማዩ ያለቅሳል እንባውን ያፈሳል። ታዲያ ምን ይደርጋል አዳም ፍርደ ገምድል ዝናብ ነው ይለዋል።
******ገፅ – 42 ላይ*****
የአገር ክዳቱ የአብራኳ ክፋይ ልጆቿ ውጤት መሆኑን “ምነዋ ኢትዮጵያ ?” በሚለው ግጥሙ ላይ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። የውስጥም የውጭም ጠላት ለምን በዛብሽ አገሬ ከሚል መጠይቃዊ የሆነ ገሃድ የምናየውን እውነታ ያሳየናል። ለሆዳቸው ያደሩ ልሂቃን ዝምታ፣ የፈፀሙትን ደባ፣ ክህደት፣…. በአራት ገፅ ረዥም ግጥሙ ይዘረዝርልናል። ከስንኞቹ ቆንጥሬ ልጋብዛችሁማ! ምነዋ ኢትዮጵያ…? እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ እንደ ኤሳው ሆኑ ቡክርናቸውን ሸጡ በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ። እንደ ባሕር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት ምነዋ ኢትዮጵያ… በዛብሽ ጠላት?…
*******ገፅ – 78 ላይ*******
ፀሃፊው ተስፋ ያደርጋል:: መልሶም ተስፋ ሲቆርጥ ደግሞ እናገኘዋለን። ውስጣዊ ጭንቀቱን የተነፈሰበትን ነፍሴን ልጋብዛችሁ።
ነፍሴ! አልጠግብ – አይቼ አልሞላ – ሰምቼ፤ አልቅሼ – አላለቅስ እንባ ከዐይኔ አይፈስ፤ ስቄ ሳቅ – አልስቅ አልል ፍልቅልቅ፤ እያለኝ ስቅ…. ስቅ… ነፍሴ አላት ጭንቅ።
****ገፅ – 30 ላይ*****
አብዛሃኞቹ ግጥሞቹ ስለ አገር፣ ስደት፣ ተስፋ፣ የሕይወት የመኖር ሕላዌ ፍልስፍና ቢበዛበትም የፍቅር ስንኞችም ለማጣፈጫነት ተካተውበታል።
ውብ! አየሽ የኔ ውብ! አየሽ የ’ኔ ርግብ!…. ለአንቺ እንጂ…ለአንቺ ፍቅር፤ ለኔ ለሆንሽው ብቸኛ ዓለም ለመሞት ተፈጥሬ፣ ለመሞት የምኖር እኮ አይመስለኝም።… እናማ… የኔ ርዕይ በር እናማ… የእምነቴ ማኅደር፤ እስከ ወዲያ – ወዲያኛው አለውህ በይኝ እኔን በእኔ ነቴ ብቻ ውደጂኝ ገላሽን ሳይሆን ልብሽን ከፍተሽ ስጭኝ።… ያኔ ነው ንጹሕ ውበቱ ዘላለማዊይ ኅብር ጽናቱ የፍቅር ህያው ሕይወትነቱ።
****ገፅ – 47 ላይ***
ለማን ይሆን የተቀኘላት? ምስጥር አርጎት አልፎታል።
የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ክብር እንደሚገባውና ማግኘትና ማጣት የስብዕና መመዘኛ ሊሆኑ እንደማይገባው ሲያስተምረንና ”ሃብታም ድሃን የፈጠረ ይመስለዋል!” የሚለውን አገራዊ ብሂል ያብራራበትና፣ በሥልጣናቸው ተመክተው እራሳቸውን እየካቡ የግፍ ፅዋቸው ሞልቶ የፈሰሰውን ባለጊዜዎች ፍንትው አድርጎ ያሳየናል።
መዝን ስብእናህን!
በዓለም ስለናኘ ዝናና ክብርህ ምድር ጠበበችህ የማያልፍ መስሎህ። ”ቱጃር” ስለተባልክ ”አለህ ብዙ ንብረት” ትንሽ መስሎ ታየህ ሌላው ሁሉ ፍጥረት። ባለሥልጣን ሆነህ በኃይልህ ተመካህ እንደጥላ እንደሚያልፍ ማን ሰው በነገረህ። እንኳ’ ሥልጣን ክብር – ገንዘብና ዝናህ አንድ ቀን ታልፋለች – መተኪያ የሌላት ውዷ እንኳ ሕይወትህ። አትደልል ራስክን ልብህ እያወቀው ይዘገያል እንጂ ህልፈት የማይቀር ነው። የትም ቦታ ብትደርስ ምንም ምን ብትሆን ማግኘት ይሁን ማጣት ደስታ ይሁን ሐዘን፤ የማያልፍ የለም ሁሉም ያልፋል ብለህ መዝን ስብዕናህን ”በኮንትራት” ኑሮህ።
******ገፅ – 54 ላይ*******
ደራሲ ፊልጶስ የችግሮች መደራረብ ውስጣዊ ቁጭቱ ሆድ አስብሶት ብቻውን በርሃ ውስጥ ቁጭ ብሎ ያነባበትን እናገኛለን።
ወንድ ልጅ ያለቅሳል! እንባ ከዓይኑ ወቶ ባይንፎለፎል፣ በጉንጩ ላይ ባይወርድ የብሶቱ ሲቃ ከሱ አልፎ ሄዶ፣ ሌላ ሐዘን ባይወልድ፤ እ! ብሎ አምጦ፣ እስትንፋሱን ውጦ፣ ነክሶ ጥርሱን በጥርስ ወንድ ልጅ ያነባል! ገላ አጥንቱን ጨምቆ፣ ልቡም እስኪያለቅስ።
*******ገፅ – 49 ላይ********
ይህ ግጥም በሃሳብ ደረጃ ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ”ወንድ ልጅ ያለቅሳል” ከሚለው ግጥም ጋር ይቀራረባል።
የወቅቱን የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በገሃድ የሚያስቃኘን የወደድኩለት ድንቅ ሥራው “አሳልፎ ሰጠሽ “ የሚለው እጅግ ስደምመኛል። ጳጳሳት፣ ሸሆች፣ ፓስተሮች፣ ሊሂቃን፣ የኪነጥበብ ባለሙያው፣ ባለሃብቱ ወዘተ… ሁሉም ”ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” እነደሚባለው የሰነፎች ተረት አገር ለመቀራመት ተሰልፈው ሲሞዳሞዱ እና ከላይ ፈጣሪ በዝምታ ሲያያቸው ለምን? ይላል ደራሲው።
አሳልፎ ሰጠሽ…. ‘ጌኛ’…. ባለዛር – ቦለቲከኛ…. ….ይሸረሙጥሻል። ጳጳስ… ይወሽምሻል ሸህ… ‘ይቀምጥሻል። ፓስተር… ይዳራሻል። ምንደኛ…. ‘ካርቴል’- ቱጃረኛ.. ….ይቆምርሻል። ከርሰኛ…. ‘ሊ’ቅ ባይ ኪነተኛ’… ….ይዘሙትሻል። ዘመነኛ…. ወጣት ቀናተኛ ይሻፍድሻል።……. የኖህን መርከብ እንኳን ‘እ’ንዳይልክልሽ አንድ ሰው…አጣና አሳልፎ ሰጠሽ!
******ገፅ – 37 ላይ*******