የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አጎዋን ለአሥር ዓመት አራዘመ

አፍሪካ ከእስያ አገሮች ትልቅ ፉክክር ይጠብቃታል  

የአሜሪካና የአፍሪካ የእርስ በርስ የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበት ላለፉት 15 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል፣ ለተጨማሪ አሥር ዓመታት ማራዘሙን የአሜሪካ ኮንግረስ ይፋ አደረገ፡፡ 

ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ወይም ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት – አጎዋ›› ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በአምባሳደር ማይክል ፍሮማንና አምባሳደር ሱዛን ራይስ በኩል ቀርቦለት ሲመክር የከረመው ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት፣ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት እንዲራዘም ይፋ ያደረገው አጎዋ እንደከዚህ በፊቱ ሳይሆን በእስያ አገሮች ዘንድ ፈተና እንደሚገጥመው እየተነገረለት ነው፡፡ አምባሳደር ፍሮማን የአሜሪካ የንግድ ዘርፍ ተወካይ ሲሆኑ፣ የቀድሞዋ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ሱዛን ራይስ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ናቸው፡፡ በአምባሳደሮቹ የቀረበው የአጎዋ ረቂቅ ሕግ ለአሥር ዓመታት የሚራዘም ከሆነ ከ30 በላይ ለሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች ትልቅ እፎይታ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኮንግሬሱ ተቀባይነት አግኝቶ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በፊርማቸው እንዲያፀድቁት መርቶታል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ2009 ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጋና ተገኝተው አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትስስር የማጠናከር አስፈላጊነት ሲገልጹ፣ ‹‹ለልጆቻችን ማውረስ የምንፈልገውን ዓለም በመቅረፅ ረገድ አፍሪካ የአሜሪካ አጋር ነች፡፡ አጋርነታችንም በጋራ ኃላፊነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፤›› ብለው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የአፍሪካና የአሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ የዕድገትና የገበያ ዕድል የሚያበቃበት ጊዜ ማለትም የመጪው ዓመት መስከረም ወር ደርሶ ከመጠናቀቁ በፊት፣ የጊዜ ገደቡ እንዲራዘም ኮንግረሱን መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡ በዚህ መሠረት አጎዋ እንዲራዘም መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ ማሻሻያዎች ተደርገውበት የበለጠ ውጤታማ የሚሆንበት መንገድ እንዲመቻች ሲጠየቅ እንደቆየ አይዘነጋም፡፡

ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገትና የገበያ ዕድል ለመፍጠር በሚል መነሻ እ.ኤ.አ. በ2000 ሕግ ሆኖ የፀደቀው አጎዋ፣ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል እያደገ ስለመምጣቱ ለሚነገርለት አጋርነት መጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጉን በማስረጃ ደፍገው የሚያቀርቡት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ብቻ አይደሉም፡፡ አፍሪካውያንም ይጠቀሳሉ፡፡ በአፍሪካ ወሳኝ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች እንዲከናወኑ፣ የተለያዩ የአኅጉሪቱ ቀጣናዎች የኢኮኖሚ ጥምረት እንዲፈጥሩ፣ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለሚያደርገው የካፒታልና የኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹነትን በመፍጠር በኩል ሚናው አሌ እንደማይባል የሚገልጹ አሉ፡፡  

በአልባሳት ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት በተገኘ መረጃ መሠረት ከነዳጅ መስክ ውጭ ያለው የወጪ ንግድ፣ መርሐ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በቀጥታ ወደ 350,000 ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ በተዘዋዋሪም ሌሎች በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩትን በማገዝ ዘርፉን በሦስት እጥፍ አሳድጎታል፡፡ 

የአፍሪካን ልማት ከመደገፍ ባሻገር አጎዋ ለአሜሪካ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችንም አስገኝቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ወዳሉት አገሮች የምትልካቸው ሸቀጦች መጠን ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክቱ ክስተቶች በአፍሪካ እየታዩ ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እያደገ መጥቶ ከሩብ ቢሊዮን በላይ እንደሚደርስ የኢኮኖሚ ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በአሜሪካ የተመረቱ ሸቀጦችን የመሸመት አቅማቸው በማደጉ፣ የሸቀጦች ወጪ ንግድ መጠን በሦስት እጥፍ ሊጨምር ችሏል፡፡ በአፍሪካ የሚገኙ የንግድ ተቋማት የአሜሪካ ግብዓቶች፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና አጋርነት አስፈልጓቸዋል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ የምታደርገው የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ በአፍሪካም ሆነ በአሜሪካ ለሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩም በላይ፣ ገቢያቸው እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

አሜሪካ በአጎዋ በኩል ከአፍሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ልውውጥ እንዳፋጠነ የሚነገርለት ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ግን ተጠቃሚ ሳይሆኑበት እንደቀረ ይታወቃል፡፡ በግብርና ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች አኳያ ተጠቃሚ መሆን ከሚገባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንደነበረች ይታመናል፡፡ ቢሆንም በአጎዋ በኩል አገሪቱ ከቀረጥና ከኮታ ነፃ ወደ አሜሪካ የላከቻቸው ምርቶች መጠን እጅግ ዝቅተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ በአጎዋ በኩል ከላከቻቸው ምርቶች በአማካይ በዓመት ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ ከፍተኛ የንግድ ባለሙያና በኢትዮጵያ የአሜሪካ የውጭ ንግድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታንያ ኮል እንዳስታወቁት፣ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በአጎዋ በኩል ከምትልካቸው ምርቶች ቦይንግ አውሮፕላንን ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ ግን ከ225.6 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ ገቢ አላገኘችም፡፡ በመሆኑም ምርቶችን በገፍ ማምረትም ሆነ ወደ አሜሪካ መላክ ፈተና ሆኖ ይገኛል፡፡ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አጎዋ በመራዘሙ ግን እየተስፋፉ ያሉት የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የገበያ ዕድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ አሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል ለእስያ አገሮች ‹‹ትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ›› በተሰኘው ማዕቀፍ ውስጥ ተመሳሳይ የነፃ ገበያ ዕድል መስጠቷ ግን በርካታ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾችን ሥጋት ውስጥ የጣለና የአፍሪካን የተወዳዳሪነት አቅም የሚፈታተን ተብሎለታል፡፡ የሥጋቱ ምክንያት ደግሞ በእስያ አገሮች ውስጥ የማምረቻ ወጪዎች ከአፍሪካ ይልቅ ዝቅተኛ መሆናቸው ነው፡፡