ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የአፍሪካ የሰላም ማዕከል በአዲስ አበባ ተገነባ

ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የአፍሪካ የሰላም ማዕከል በአዲስ አበባ ተገነባ

ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ እንዲሰጥ ታስቦ በአዲስ አበባ የተገነባውና ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የሰላም ማዕከል፣ ሰኔ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመርቆ ተከፈተ፡፡ 

ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መርቀው የከፈቱት ይኼ የደኅንነት ተቋም፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ግጭትን ለመፍታት ለሚደረጉ የሰላም ማስከበር ጥረቶች አስፈላጊ የሥልጠናና የጥናት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተገነባ ነው፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፣ የተሳካ ሰላም የማስከበር ሥራዎች ለማከናወን ማዕከሉ ትልቁ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ማዕከሉን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹የሰላም ማዕከሉ ወታደራዊና የሰላም አስከባሪ ተቋማት ዓላማቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲወጡ የምርምርና የሥልጠና አገልግሎት በመስጠት የሰላም ማስከበር ሥራዎች ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንፃር ላደረገው አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ለመከላከያ ሚኒስቴር የቸሩት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ የአገሪቱ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ኢትዮጵያ በአካባቢው የሰላምና የፀጥታ ተምሳሌት መሆን በመቻሏ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ 

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ሰላምን በማስከበር ሥራዎች የማይተካ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ገልጸው፣ ማዕከሉ ይህንን ጥረት በዕውቀትና በምርምር ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተገነባው ይኼው የሰላም ማዕከል ግጭትን ለመከላከል፣ ዕርቅ ለመፍጠርና ሰላም ለማስከበር ለአካባቢውና ለመላው አፍሪካ ጥቅም ይውል ዘንድ፣ በተለይ ከአፍሪካ ኅብረትና ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በትብብር እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስን ጨምሮ፣ በርካታ የመከላከያና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡