ሰበር ዜና – ከብር 4 ሚልዮን በላይ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የመዘበሩት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ሒሳብ ሹም እና ገንዘብ ያዥ ቃሊቲ ወረዱ!

Addis Ababa Lideta LeMariam Church

  • ለደብሩ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና ለየሰንበት ት/ቤቱ ታላቅ ድል፤ በየአጥቢያው ለተጋጋለው የፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ ታላቅ የምሥራች፤ የንቅናቄውን ኃይሎች በነፍስ ግድያ ዛቻዎች ጭምር ለማዳከም ለሚሯሯጡት አማሳኞች ከባድ ድንጋጤ እና መርዶ ኾኗል !!!

Lideta LeMariam Church

  • በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ረፋድ ባሳለፈው የቅጣት ውሳኔ፣ የደብሩ ዋና ሒሳብ ሹም ዲያቆን ተስፋዬ በቀለ እና የደብሩ ዋና ገንዘብ ያዥ ወ/ሮ አብረኸት ተክሉ በሰነድ ማጭበርበር በፈጸሙት የእምነት ማጉደል ወንጀል እያንዳንዳቸው በኹለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ፈርዶባቸዋል፡፡ መዝባሪዎቹ ውሳኔው ከተላለፈበት ካለፈው ዓርብ ረፋድ ጀምሮ ቀጨኔ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ቆይተው የቅጣት ጊዜአቸውን ለመፈጸም በዛሬው ዕለት ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት መውረዳቸው ታውቋል፡፡
  • በተመሳሳይ መዝገብ የኹለት ዓመት የእስር ገደብ እና የአምስት ሺሕ ብር ቅጣት ከተላለፈባቸው ተከሣሾች መካከል በተለያየ ጊዜ የደብሩ ጸሐፊ የነበሩት መ/ር ኃይለ ማርያም ኣብርሃ(ለአጭር ጊዜ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ) እና መ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ዕዝራ እንዲኹም የደብሩ ዋና ተቆጣጣሪ ዲያቆን ሀብቶም አረጋዊ ይገኙበታል፡፡ ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ሕግ፣ ‹‹ቅጣቱ አንሷል፤ አስተማሪ አይኾንም›› በሚል ከብዶ እንዲወሰን ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተመልክቷል፡፡
  • በአኹኑ ወቅት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሐፊ ኾነው የሚሠሩት መ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ዕዝራከየካቲት እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. ባሉት ሰባት ወራት ብቻ ገዳሟ ለተመዘበረችው ከብር 1.5 ሚልዮን በላይ ገንዘብ ከሒሳብ ሹሙ፣ ከገንዘብ ያዡ፣ ከቁጥጥሩ እና ከቀድሞው አስተዳዳሪ ጋር ተጠያቂ እንደኾነ ሰበካ ጉባኤው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በአድራሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በግልባጭ ለበላይ ጠባቂው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለፓትርያርኩ ሊቀ ጳጳስ ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

*          *          *

  • የወቅቱ የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ እና የሰበካ ጉባኤ ማዳራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ÷ ከሐምሌ1/2004 – ኅዳር 20/2005 ዓ.ም. ያለው የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን የገቢ እና የወጪ ሒሳብ አጣርተው እንዲያቀርቡ በ2005 ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በታዘዙበት ወቅት በሰነድ ማጭበርበር የተፈጸመውን ከፍተኛ የገንዘብ ዘረፋ ለማድበስበስ እያንዳንዳቸው ብር 50‚000 ተቀብለዋል፡፡ ‹‹እንዴት እኩል ይሰጠኛል›› በሚል በዋና ሒሳብ ሹሙ እና በዋና ገንዘብ ያዡዋ ላይ ቂም የያዙት የጥንቆላ እስረኛው፣ የፐርሰንት ፈሰስ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እና የአበል ክፍያዎች ቀበኛው ሊቀ ጠበብት ኤልያስም ሒሳብ ሹሙ እና ገንዘብ ያዡዋ እንዲከሠሡ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
  • በአማሳኝ አለቆች እና በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የጥቅም ትስስር፤ ከመጪው ሰኔ 30 ቀን ጀምሮ በየአድባራቱ የኦዲት ምርመራ ለማካሔድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት ያለተጠያቂነት የሚፈጸመው የአጥቢያ ሠራተኞች ዝውውር እንደቀጠለ ነው፤ በትላንትናው ዕለት ያለአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና በዋና ሥራ አስኪያጁና ጥቂት ተባባሪዎቻቸው ውሳኔ በአምስት አጥቢያዎች መካከል የተደረገው የሒሳብ ሹሞች ዝውውር÷ በብልሹ አሠራር ላይ ጥያቄ ያቀረቡ የተጠቁበት፤ በምትኩ ለቀጣይ ዘረፋ ኹኔታዎች እየተመቻቹ እንዳሉ የሚጠቁም እንደኾነ እየተገለጸ ነው፡፡

*          *          *

  • ‹‹ቃለ ዐዋዲው÷ የደብሩ ሒሳብ ሹም በየወሩ፣ ቁጥጥሩ ደግሞ በየሦስት ወሩ ለሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢያዝም ድንጋጌውን በደብራችን ለመተግበር አስቸጋሪ ኾኖ ቆይቷል፤
  • ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኅዳር 28/2003 ዓ.ም. ለአጥቢያችን በተጻፈ ደብዳቤ የ10 ዓመት ያልተከፈለ 20% ዕዳ ብር 4‚181‚189.76 ስላለባችኹ እስከ ታኅሣሥ 30/2003 ዓ.ም. ገቢ እንድታደርጉ የሚል ደብዳቤ ደርሶን ነበር፡፡ …ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት በቀየሱት የጥፋት እና የብክነት ስትራተጂ ከሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ከሚገኘው ገቢ ላይ ለሀገረ ስብከቱ ሊከፈል የሚገባው የ20% ድርሻ እየተቀነሰ ሰነድ ሳይነካው በአየር ላይ ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዲላክ በቃል በማዘዛቸው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተበልቷል
  • …በየወሩ በከፍተኛ መጠን የሚገባና ለብክነት የተጋለጠ የገንዘብ ምንጭ ቢኖር የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ ገንዘብ ነው፤ የቆጠራው ሥርዐት ምን እንደሚመስል ለመመልከት፣ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ካሉም ለማሻሻል እና የቁጥጥር ሥርዐቱን አጠናክረን ለመቀጠል የሰበካ ጉባኤው አባላት በሙሉ በመገኘታችን በወቅቱ የነበረው አስተዳደር፣ ለምን ተሰብስባችኹ ትገባላችኹ? ይህን እንድታገጉ ማን ፈቀደላችኹ? በሚል በጣም ተቆጣ፤ አባላቱን በማስፈራራት በቆጠራ ላይ እንዳይገኙ ጥረት ቢያደርግም ሰበካ ጉባኤው ጉዳዩን አጠናክሮ ቀጠለበት፤
  • …በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሚያንቀሳቅስ ቤተ ክርስቲያን የዚኽ ዓይነት ብልሹ የሒሳብ አሠራር በዘመናችን የለም፤ የሞዴል 64 ሰነዶች እየተደለዙ ከፍተኛ የማጭበርበር ተግባር ተፈጽሟል፤ 17 የሞዴል 64 ቅጠሎች በሓላፊዎቹ ተዘርፈዋል፤ ከሐምሌ1/2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሒሳብ ምርመራው እስከተካሔደበት ድረስ የተወራረደ ሒሳብ የለም፤ ከሙዳይ ምጽዋት ተቆጥሮ በሞዴል 64 የገባ ብዙ መቶ ሺሕ ብር ተሰርዞ እና ተደልዞ መጭበርበሩን /በ2003 ዓ.ም. ከብር 591‚965.25 ባንክ አለመግባቱን/ ከባንክ ባስመጣነው የገቢ እና የወጪ ማስረጃ /Bank statement/ አረጋግጠናል፤
  • የሕንፃው ክፍሎች የኪራይ ክፍያ ወቅቱንና የአካባቢውን የገበያ ኹኔታ ያገናዘበ ሳይኾን ለተከራዩ የሚያደላና ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው፤ ማኅበረ ምእመናን፣ ማኅበረ ካህናት እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ገንዘባቸውን እያዋጡ ያሠሩትን የቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውጤት ለማየት ባለመቻላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ ኮሌጁ በሰበካ ጉባኤው እንዲተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው መተዳደርያ ደንብ ተጥሶ ደብሩ የማያዝበትና የማይጠቀምበት፣ ባለቤቱ በውል ያልታወቀ ተቋም በመኾኑ የገቢና ወጪ ሒሳቡን ለመቆጣጠር አልተቻለም፤ በ2003 እና በ2004 ዓ.ም. ለደብሩ የሚገባውን ፈሰስ አልከፈለም
  • በአጠቃላይ ከሐምሌ 1/2002 – ሰኔ 30/2005 ዓ.ም. ባሉት ሦስት የበጀት ዓመታት በውጭ ኦዲተር በተደረገ የሒሳብ ምርመራ ከብር 4‚606‚301.50(አራት ሚልዮን ስድስት መቶ ስድስት ሺሕ ሦስት መቶ አንድ ብር ከኃምሳ ሳንቲም) የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘብ በዋና ሒሳብ ሹሙ፣ በዋና ገንዘብ ያዡዋ እና በዋና ተቆጣጣሪው ተመዝብሯል፡፡››

/ከሚያዝያ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ተመርጦ በሥራ ላይ የነበረው ሰበካ ጉባኤ በነሐሴ 2005 ዓ.ም. ለማኅበረ ካህናት፣ ለማኅበረ ምእመናን እና ለየሰንበት ት/ቤቱ ካቀረበው ሪፖርት/

  • ‹‹የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር በሰጡት መግለጫ÷ የደብሩ ሒሳብ በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው መሠረት የጊዜ ሰሌዳውን ጠብቆ በአግባቡ እንዲመረመር ሰበካ ጉባኤው ለሚመለከተው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለሟቋረጥ አቤቱታ ሲያቀርብ ቢቆይም ሰሚ ዦሮ በማጣት ወይም ዦሮ ዳባ ልበስ ተብሎ በመቆየቱ የተገለጸው ከፍተኛ ገንዘብ ምዝበራ በደብሩ ሊፈጸም የቻለ መኾኑን አሥምረውበታል፡፡
  • …ከካህናቱ እና ከምእመናኑ ከቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መካከል፡- ሒሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥ፣ ቁጥጥር በማን እንደሚላኩ እናውቃለን፡፡ ከዚኽ ከደብራችን የሥራ ብቃት ያላቸው ልጆች እያሉን ከላይ መመደባቸው ያሳዝናል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተጠያቂዎች መኾናቸውን ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊያውቀው ይገባል፡፡…ለዚኽ ኹሉ ጥፋት ዋና መነሻ ከዚያው የሚላኩት ኦዲተሮች ናቸው፡፡ እነርሱ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በእነርሱ ላይ የምንወስደው ርምጃ ምንድን ነው? የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡››

/የዜና ቤተ ክርስቲያን የነሐሴ ፳፻፭ ዓ.ም. ዘገባ/