የደቀ መዛሙርት ምረቃ ሳምንት ነው – አህጉረ ስብከት እና ኮሌጆች በደቀ መዛሙርት ምልመላ፣ ቅበላ እና የትምህርት ዝግጅት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔዎች ያስከብሩ!

  • ‹‹ደቀ መዛሙርቱ ከየአህጉረ ስብከቱ ተመርጠው ሲላኩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መኾናቸው እና የሃይማኖታቸው ጥንካሬ ታይቶ እንዲመለመሉ አህጉረ ስብከት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡››
  • ‹‹ወደ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎች እና የሚያስተምሩ መምህራን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀታቸው እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እየታየ ወደ ኮሌጁ ገብተው እንዲማሩ እና እንዲያስተምሩ  ይደረግ፡፡››

/የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የጥቅምት ፳፻፬ ዓ.ም. ውሳኔ/

  • ‹‹የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛየትምህርት ተቋማት እና ማሠልጠኛዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያደርጉት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ኾኖ ወደ ኮሌጆች የሚገቡ ደቀ መዛሙርት በምልመላ፣ በቅበላ እና በትምህርት ዝግጅት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ በታከለበት ኹኔታ እንዲሠሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይደርስ ዘንድ ተግተን እንሠራለን፡፡››

    /የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የ፳፻፯ ዓ.ም. የአቋም መግለጫ/

Logos of the three EOTC theological colleges
ትምህርተ ሃይማኖት ዘኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ድኅነትን ያስገኛል፤ በረከትንም ያሰጣል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ለወደፊቱም የሚኖረውን እውነተኛ አስተምህሮዋን ጠብቃ ካኖረችበት መንገድ አንዱ የትምህርት መስጫ ተቋማትን መመሥረቷ ነው፡፡

የበርካታ የአብነት ት/ቤቶች እና የካህናት ማሠልጠኛዎች ባለቤት የኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ነባሩን አስተምህሮዋን በዘመናዊ አቀራረብ አስፋፍታ እና አጠናክራ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሦስት መንፈሳዊ ኮሌጆችንም ለማቋቋም ችላለች፡፡

ለሦስቱ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዛሬ ቅዳሜ ሰኔ ፳ ቀን ጀምሮ ያለው አንድ ሳምንት የምረቃ ሳምንት ነው፡፡

EOTC St.Trinity College Logoከዛሬ 53 ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እንደ አንዱ ኾኖ መንፈሳዊውን ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጥበት የመጀመሪያው መካነ ጥበብ – የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ – በተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲያስተምራቸው የቆዩትን 322 ደቀ መዛሙርት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ያስመርቃል፡፡

በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በሚከናወነው የምረቃ መርሐ ግብር÷ በመደበኛ የድኅረ ምረቃ ሲስተማቲክ ቴዎሎጂ 10፣ በቀን መደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ 43፣ በማታ ተከታታይ የመጀመሪያ ዲግሪ 71፣ በማታ ተከታታይ ዲፕሎማ 107፣ በግእዝ ቋንቋ ዲፕሎማ 7 እና በርቀት ትምህርት ሰርተፊኬት 84 ደቀ መዛሙርት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ይመረቃሉ፡፡

St.Paul collegeየብሉያት እና የሐዲሳት ትርጓሜ ቤት እንዲኹም የአንደኛ ደረጃ ዘመናዊ የአዳሪ ትምህርት ቤት ኾኖ በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. የተቋቋመው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መምህራን ማሠልጠኛ፣ ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ተሸጋግሮ የሰሚነሪ(የአራት ዓመት ኮርስ) የጀመረው በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. ሲኾን ወደ ኮሌጅነት ያደገው ደግሞ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ነው፡፡

ኮሌጁ በዘንድሮው ዓመት 218 ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ ያቀርባል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ኀሙስ፣ ሰኔ ፳፭ ቀን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ የሚመረቁት ደቀ መዛሙርት፡- በቀኑ መደበኛ እና ተመላላሽ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ 16፣ በብሉይ ኪዳን አንድ፣ በቀን መደበኛ እና ተመላላሽ የሰሚናር ዲፕሎማ 21፣ በማታ ተከታታይ የሰሚናር ዲፕሎማ 180 ናቸው፡፡

St Fremnatos Abba Selama Collegeየመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የተቋቋመው በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ወደ ኮሌጅ ደረጃ አድጎ በመደበኛ የዲግሪ መርሐ ግብር ማስተማር የጀመረው በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ነው፡፡ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. የተከታታይ ትምህርት መርሐ ግብር በመዘርጋት በማታው ክፍለ ጊዜ ማሠልጠን ጀምሯል፡፡

በቴዎሎጂ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ለሦስተኛ ጊዜ 16 ደቀ መዛሙርትን በማሠልጠን ላይ የሚገኘው ኮሌጁ፣ በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፯ ቀን 30 ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ የሚያበቃ ሲኾን ከእኒኽም 7ቱ በዲግሪ፣ 12ቱ በዲፕሎማ እና የቀሩት በድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡