በደሙ ተፃፈ፤ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ

በጭካኔ ጥበብ ተንኮል የተካኑ፤
ስብዕናን ያጡ ለውነት የመከኑ፤
በሐሰት ተጠምቀው በውሸት የፀደቁ፤
በሌላው መከራ ሳቁ ተሳለቁ::

ሊጥሉት ሞክረው አልወድቅም ቢላቸው፤
ቀጥቅጠው ገደሉት በፈሪ ዱላቸው።
በድቅድቅ ጨለማ ተስፋ በታጣበት፤
የነፃነት ትግል በደበዘዘበት፤
ሣሙኤል አወቀ እንደሻማ በርቷል፤
ለወገኑ ክብር በሕይወቱ ከፍሏል።

ፈለጉን ተከተል አደራ ብሎሃል፤
ደሙ ከአጥናፍ አጥናፍ ይጣራል ይጮሃል፤
እምቢ በል ወገኔ ተነሣ ይልሃል፤
ፀጥ ያለው ነጎድጓድ፤ የታመቀው ቁጣ፤
የዝምታው መብረቅ፤ ገንፈሎ እንዲወጣ፤
አብረህ ተነሳ፤ ይቅር ማመንታቱ፤
ስዓቱ አሁን ነው ህዳሴ አብዮቱ።

የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈልቶ ሲገነፍል፤
እንዳላየህ አይተህ፤ አልፈህ ዝም ስትል፤
ታሪክ ይጠይቃል የት ነበርክ ይልሃል።
ግፉዓን ሲጮሁ፤ ፍትሕን ተጠምተው፤
አንደበት የሆኑ ድምጽ ለሌላቸው፤
እንደነ ሣሙኤል ደፍረው የጀገኑ፤
በጨቅላ ዕድሜያቸው እንደጉም ሲተኑ፤
እንዴት ያስችለናል ሰምቶ ዝም ማለቱ፤
በወንበዴ መንግስት ሲቀጩ ሲሞቱ።

ሣሙኤል በደሙ ታሪኩን ጽፎታል፤
የነፃነት ቀንዲል አሻራውን ትቷል፡
የጀግናው መሰዋት እንዳይቀር በክንቱ፤
ይብቃ ብለህ ተነስ የዝግታ ሞቱ
ይብቃ ብለህ ተነስ ውርደቱ ስደቱ።

በጨካኞች በትር ሕይወቱ ላለፈው፤ ለወጣት ሣሙኤል መታስብያ ትሁንልኝ።