በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ ክስ መዝገብ ስር የሚገኙት ተከሳሾች ለብይን ተቀጠሩ

በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙትና ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው እነዘላለም ወርቅአገኘሁ ከረፋዱ 4፡30 ላይ ልደት በሚገኘው 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡

ችሎቱ ዛሬ ተሰይሞ የነበረው በተከሳሾቹ ላይ አቃቤ ህግ ባቀረበው የሰነድና የሰው ማስረጃ ላይ ብይን ለመስጠት እንደሆነ ያወሱት የመሃል ዳኛው ሸለመ በቀለ፣ አቃቤ ህግ ለአራተኛ ጊዜ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንዳቀረብ ጊዜ ይሰጠኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ችሎቱ ያልተቀበለው በመሆኑ ውድቅ መደረጉን ገልፀዋል። ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉት ተከሳሾች እንዲሁም የ9ኛ ተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ ለፍርድ ቤቱ የማመለክተው ነገር አለኝ በማለት ደምበኞቻቸው ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች የተገኙት ከህግ አግባብ ውጪ መሆናቸውንና ደምበኞቻቸው ከተያዙ በኋላ የቀረቡ መሆኑንና ይህም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 146 የተላለፈ መሆኑን ገልፀው አቃቤ ህግ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃም ሆነ የሰው ምስክር ከክሱ ጋር ያልተያዘዘ መሆኑን ተረጋግጧል በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። አቃቤ ህግ በበኩሉ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ የሰነድ ማስረጃዎቹም ሆነ የሰው ምስክሮቻችን ውድቅ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ተጨባጭ ማስረጃ እንዳላቀረቡ ገልፆ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችም ሆነ የሰው ምስክሮች ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን አስረድቷል። አያይዞም የቀረቡት ‹‹የሰነድ ማስረጃም ሆነ የሰው ምስክሮች የቀረበውን ክስ ያስረዳሉ አያስረዱም የሚለው ፍርድ ቤቱ የሚመዝነው መሆኑን ገልፆ፣ ፍርድ ቤቱ የጠበቃ ተማም አባቡልጉን መቃወሚያ ወድቅ እንዲያደርገውና በተሰሙት የሰው ምስክሮችና በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ተገቢውን ብይን እንዲሰጠን እናመለክታለን›› በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዛሬው ችሎት ውሎ ከመቅረፀ ድምፅ ተገልብጠው ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማመልከት ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ሰጥቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል በማሰብ የሚል ክስ የተመሰረተበት የአንድነት አባል የነበረው መሳይ ትኩ፣ በተመሳሳይ ሰአት ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ክስ መቃወሚያ ካለው ከጠበቃው ጋር በመሆን ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በዘላለም ወርቅ አገኘሁ የክስ መዝገብ ስር የሚገኙት የቀድሞ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ም/ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺና የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል አፈጉባኤ የነበረው አቶ የሺዋስ አሰፋ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዞን ሶስት እንደተዘዋወሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡