መምህር ዘበነ ለማ በውሸት ላይ ወሸት በቅጥፈት ላይ ቅጥፈት ጨመረ
ከታዛቢ
“…..እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው……” ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቁጥር 32 ይህንን ጥቅስ ለማስቀደም የመረጥኩበት ምክንያት እ.አ.አ. ሜይ 10 ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ “ናሽናል ሞል” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሊቢያ ሰማዕት ለሆኑትና በደቡብ አፍሪካ ለተገደሉት ኢትዮጵያዊያን በርካታ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት ካህናትና ምዕመና፣ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ተወካዮች፣ የእስልምና ሐይማኖት ተካታዮችና ሌሎችም የማህበረሰብ አባላት በተገኙበት እጅግ ደማቅና የተዋጣለት የጸሎትና የመታሰቢያ ስነሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል። በዚህ ዝግጅት ላይ የሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የአውስትራሊያና ካናዳ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ መቃሪዮስ፣ የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አስተዳዳሪ ቀሲስ ዶክተር አማረ ካሳዬ፣የካንሳስ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌና ሌሎችም አንጋፋ ካህናት ተገኝተው ነበር።
ይህ ዝግጅት ከታቀደበት ጊዜ አንስቶ ተሳታፊ የነበሩትና በኋላ ግን የተንሸራተቱት መምህር ዘበነ ለማና መምህር ተስፋዬ መቆያ ከወያኔ ጋር ያጋጨናል የሚል ምክንያት በመስጠት እንዳልተሳተፉ ይታወቃል። ይህንን አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ በቀጥታ በሚተላለፈው 1120 ኤ.ኤም ራዲዮ “ደምጸ ተዋህዶ” መርሃ ግብር ላይ አንድ ተቆርቋሪ ምዕመን ስልክ በመደወል ለመምህር ዘበነ ለማ ”… በዋሽንግተን ሞኑመንት ላይ በተደረገው ዝግጅት አንተና መምህር ተስፋዬ መቆያ ከወያኔ ያጋጨናል በማለት እንዳልተሳተፉችሁ ይነገራል ይህ እውነት ነው ወይ?…” በማለት ላቀረቡለት ጥያቄ “አልተጠራሁም፤አልሰማሁም” በማለት የክህደት ቃሉን ሰጥቷል። ይህም በሬዲዮ የተላለፈ የክህደት ቃል በርካታ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ምዕመናንን በማነጋገርና በማወያየት ላይ ነው። እኔም መምህር ዘበነ ለማ መዋሸት ልማዱ እንደሆነና ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ለማስታወስ ያህል ይህችን አጭር ማስታወሻ አዘጋጅቼ ልኬያለሁ።
እኔ የማስታውሳቸው የመምህር ዘበነ ወሸቶች የሚከተሉት ናቸው።
1. “አቡነ ጳውሎስ ሰርጌ ላይ ሳልጠራቸው ነው የመጡት”
2. “የአቡነ ጴጥሮስ መስቀል እጄ ላይ ይገኛል”
3. “ ክህነት ለመቀበል እየሩሳሌም በሄድኩበት ጊዜ በወቅቱ የእየሩሳሌም ገዳም አስተዳዳሪ የነበሩት አቡነ ማትያስ ከደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጋር ባላቸው ቂም ምክንያት ሥነ ሥርዓቱ እንዳይካሄድልኝ በመከልከላቸው ምክንያት በገዳሙ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለግሉ የነበሩት አቡነ አብሳዲ በግላቸው ደብቀው ክህነቱን ሰጥተውኛል።
4. “ታደሰ ሲሳይ ምንኩስና ስለተቀበለ ክህነቱን መቀጠል ይችላል”
እንደዚህ ዓይነት አወናባጆችንና እንደ ጣቃ ጨርቅ የሚቀደዱ ካህናትና ሰባኪዎችን ቤተክርስቲያናችን እስከ መቼ ተሸክማ እንደምትኖርና መቼስ ምዕመናን እንደዚህ ዓይነቶንች በቃችሁ ለማለት ወኔው እንደሚኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ምዕመናን ለሐይማኖታቸው ኃላፊነት እንደማይወስዱና ግድ የለሽ መሆናቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ አንደበታቸው ጤፍ የሚቆላ የዘመናችን ጩልሌዎች የሚገታቸው ከሌለ በስተቀር ከያዙት እኩይ ተግባር የሚመለሱበት ሁኔታ የለም። ምዕመናን ቢያንስ በነጻነት በሚኖሩበት በዚህ አሜሪካን አገር ውስጥ እንኳ ቤተክርስቲያናቸውን የሚንከባከቡበትና ከቀጣፊዎች የሚያጸዱበት ጊዜ ቅርብ እንጅ እሩቅ እንዳይሆን ቸልተኝነቱን ትተው ለሐይማኖታቸው በቀናኢነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ። በቤተክርስቲያን አውደ ምሕረት ላይ ቆመው ተዋቡ ቃላትን የሚያሰሙን ነገር ግን ችግራችንን እንዳንፈታ የሚያደነዝዙንና የሚያዘናጉን የውሸት ሰባኪያንና አስመሳይ ጥቅመኞችን ልናስወግዳቸው ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ በሊቢያ የተሰዉት ወገኖቻችን በደማቸው ቀለም ጽፈው ያስተማሩን ለሐይማኖት ጽናት የሚከፈለው መስዋዕትነት እስከ ሞት ድረስ መሆኑን ነው። እኛ በሰላም አገር እየኖርን ቢያንስ አይናችን የሚያየውንና ጆሮአችን የሚሰማውን የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ጩኽት ማስተጋባት ይኖርብናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንም “እውነቱን እውነት በሉ፣ ሀሰቱንም ሀሰት በሉ ነው።በመጨረሻም በጥቅስ እንደጀመርኩ በጥቅስ እጨርሳለሁ “…..ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው…።” ምሳሌ ምዕራፍ 12 ቁጥር 22።