የሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ሙስና እና የፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ የሚስፋፋበት እና የሚጠናከርበት ስልት ተቀየሰ፤ አማሳኞች ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች በዩኒፎርም ሰልፍ መውጣት እያስጠቃን ነው›› አሉ
- በሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተጠራ ጉባኤ፣ የአንድ ወር እንቅስቃሴውን ገምግሟል
- ንቅናቄውን ከመሪ ዕቅዱ ቁልፍ ጉዳዮች ጋር አስተሳስሮ የሚመራ ራሱን የቻለ አካል ተቋቁሟል
- ከማኅበረ ካህናት እና ምእመናን፣ የማኅበረሰብ ተቋማት እና የፀረ ሙስና አካላት ጋር ይሠራል
- ዓላማውን ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ በማስተዋወቅ በስፋት ማነሣሣትና ማንቀሳቀስ ተግባሩ ነው
- የዕቅበተ እምነት የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ንቅናቄው በገዳማውያን አበው ጸሎት ይታገዛል
* * *
- ከ160 በላይ የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ኹሉም አመራሮች በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተካሔደው የግማሽ ቀን ውይይት፣ የአንድነቱ አመራር ባቀረበው የአንድ ወር የእንቅስቃሴው ሪፖርት ላይ የተመሠረተ ግምገማ እና ቀጣይ ስልቶችን የቀየሰ ውይይት ተካሒዷል፡፡
- የአንድነቱ አመራር በሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ስትራተጅያዊ ዕቅድ አፈጻጸሞች ላይ እንዲያተኩር የተወሰነ ሲኾን ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለፍትሕ መስፈን በንቅናቄ መልክ የተጀመረውን ተጋድሎ ከስትራተጅው ቁልፍ ጉዳዮች ጋር አስተባብሮ የሚመራ እና ከሰባቱም የክፍላተ ከተማ አንድነት ጉባኤያት የተውጣጣ 35 አባላት ያሉበት አካል ተቋቁሟል፡፡
- ለንቅናቄው በሚያስፈልጉ ሞያተኞች እና በካር አገልጋዮች የተሟላው ኮር አካል ከማኅበረ ካህናት፣ ከማኅበረ ምእመናን፣ እንደ ዕድር ካሉ የማኅበረሰብ እና እንደ ፀረ ሙስና እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ካሉ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲኾን የንቅናቄውን ዓላማዎች ከአባላት ወላጆች (ቤተሰብ) እስከ ኅብረተሰብ በማስተዋወቅ አገልጋዩንና ምእመኑን በስፋት ማንቀሳቀስ፤ አማሳኞችን እያጋለጡ ለፍርድ ማቅረብ እና መናፍቃንን እየመነጠሩ በቀኖናዊ ውሳኔ እንዲለዩ ማድረግ ዋነኛ ተግባሩ ነው፡፡
- ‹‹ሰንበት ት/ቤቶች ለሚያነሷቸው በተለይም የአለቆች ይነሡልን ጥያቄ ምላሽ መስጠት መሸነፍ ነው›› የሚሉት ቀንደኛ አማሳኞች እነ ኃይሌ ኣብርሃ፣ ዘካርያስ ሐዲስ፣ ተስፋ ፍሥሓ እና ነአኵቶ ለአብ አያሌው፣ ‹‹የሰንበት ት/ቤቶች በዩኒፎርም ለሰልፍ እና ለስብሰባ መውጣት እያስጠቃን ነው›› ብለዋል፡፡
- የሰንበት ት/ቤቶቹን መለያ ልብስ (ዩኒፎርም) ነጥቆ ወደ ግምጃ ቤት በመክተት፣ በሌላቸው ሞራላዊ ልዕልና ‹‹ገንዘባቸውን እና ንብረታቸውን ኦዲት ያስደረጉ›› በሚል በእጅጉ የፈሩትን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ እና የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴ አቅሞቻቸውን የሚያዳክሙ አሠራሮች ከአንዳንድ የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ጋር እየዶለቱ ነው፡፡
