ሰበር ዜና፤ የኤርትራ አገዛዝ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተረጋገጠ
የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crime against humanity) ተብሎ ሊጠራ በሚችል ሁኔታ በረቀቀ መንገድ እጅግ አስከፊ የሆነ ፍርሃት በህዝባቸው ላይ የጫኑ መሆኑ ትናንት ጄኔባ ላይ ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) አጣሪዎች ሪፖርት አመልክቷል። በዚህም መሠረት በሽዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን አገራቸውን እየለቀቁ በመሰደድ ላይ መሆናቸውንና ይህም በሜድትራኒያን ባሕር ላይ ላለው የስደተኞች ቀውስ ዋናው መንስዔ መሆኑ የተ.መ.ድ. አጣሪዎች አረጋግጠዋል።አጣሪዎቹ እንዳብራሩት በመጠኑና በስፋቱ ኤርትራ ውስጥ እንዳለው ዓይነት የሰብዓዊ መብት መጣስ በሌሎች አገሮች ውስጥ እንዳላጋጠማቸው ጠቁመው፣ ኤርትራ ውስጥ በሰዎች ላይ ሰቆቃ መፈጸምና ማሰቃየት፣ ከህግ ውጭ ግድያ መፈጸም፣ የግዳጅ የጉልበት ሥራ ማሰራት፣ በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸም በስፋት እንደሚከሰት አስታውቀዋል ። ለነዚህም ወንጀሎች በሙሉ ተጠያቂው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የስለላ መዋቅራቸው መሆኑም ተገልጿል። የተ.መ.ድ. ከአሁን በፊት በኤርትራ ውስጥ ስለሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዚህ መልክ ጠንካራ ሪፖርት ሲያወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው።