፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል

2004 eotc ssd gen assembly

  • ዓመታዊ ጉባኤው የሚካሔድበት ወቅት ‹‹የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን›› በሚል ተሠይሟል
  • በአ/አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ ላይ አቋም እንደሚይዝ ይጠበቃል
  • ዋና ሓላፊው፣ ‹‹የአ/አበባዎችን ጥያቄ እንዳትቀበሉ›› በሚል ያደረጉት እንቅስቃሴ ተነቅቶበታል
  • የሀ/ስብከቱ ሥ/አስኪያጅ ለአንድነቱ ልኡካን የውክልና ደብዳቤ ባለመጻፍ በዓላማ ተባብረዋቸዋል

በዓለ ጰራቅሊጦስን ተንተርሶ በየዓመቱ የሚካሔደው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ፣ አራተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ይጀምራል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ከዛሬ ግንቦት ፳፩ እስከ ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ለሦስት ቀናት በሚካሔደው ሀገር አቀፉ የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ ከ52 አህጉረ ስብከት የተወከሉ ከ500 በላይ ልኡካን ይሳተፉበታል፡፡

እንደ መንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ኹሉ፣ አስፈላጊነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ታምኖበት በጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም. በጸደቀው የውስጥ መመሪያ የተፈቀደው ዓመታዊው ሀገር አቀፍ አጠቃላይ የሰንበት ት/ቤቶች ጉባኤ÷ ኹሉንም ሰንበት ት/ቤቶች እኩል አድርጎ በአገልግሎት ለማሳተፍ እና ለመምራት በወጣው ስትራተጅያዊ ዕቅድ መመራታቸውን ለመከታተል፤ ወጥ የአገልግሎት ሥርዐት እንዲኖር ለማድረግ፣ ልምድ እና ተሞክሮን ለመለዋወጥ እንዲኹም ለጋራ ችግሮች መፍትሔ የሚቀየስበት የመመካከርያ ጉባኤ ነው፡፡

የሀገር አቀፍ አንድነቱ የመጨረሻ የሥራ አካል እና በማደራጃ መምሪያ የሚመራው ጠቅላላ ጉባኤው በዘንድሮው ዓመታዊ ስብሰባው፣ በማደራጃ መምሪያው እና በሥራ አመራር ጉባኤው ተመክሮበት በአምስት ዓመቱ ስትራተጅያዊ ዕቅድ ማህቀፍ የተከናወነውን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም እና የበጀት አጠቃቀም ሪፖርት ይገመግማል፤ በቀጣይ ተግባራት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

ስለ ሰንበት ት/ቤቶች የአስተዳደር ወጥነት እና የፋይናንስ ሥርዐት ዝርጋታ እንዲኹም በጸደቀው የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ አፈጻጸም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ምን ዐይነት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል በሚሉ አርእስተ ጉዳዮች ላይ በማደራጃ መምሪያው የተዘጋጁ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ለስብሰባው በወጣው መርሐ ግብር ተመልክቷል፡፡