የ2007ቱ ሀገራዊ ምርጫ አካሄዱና አፈጻጸሙም ነጻና ፍትሀዊ ስላልሆነ ውጤቱን ሸንጎ አይቀበለውም።

ገና ከጅምሩ፣ የተቃዋሚ ፓርቲወችን በመበታተን፣ መሪዎችንና አባላቶቻቸውን በማሰር፣ በማሳደድና በማዋከብ፤ ነጻ የሃሳብ ልውውጥ እንዳይኖርና አማራጭ ሃሳቦች ለህዝብ እንዳይደርሱ ነጻ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞችንና ጦማራውያንን በግፍ ወደ እስር ቤት በመወርወርና የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ፤ ከአገዛዙ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በጭቆና መሣርያነት የሚያገለግለውን የምርጫ ቦርድ በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማፈራረስ የጀመረው ምርጫ ተብየ በትናንቱ እለት ተካሂዷል።

በዚህ ምርጫ ተብየ፣ የተስተዋለው ድባብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፈናፈኛ በሚነሳ ሁኔታ እግር ከወርች አስሮ በተለያየ አሻጥር ቀፍድዶ እንዳይንቀሳቀሱ የሆነበት አካሄድ በግልጽ ሲታይ በአኳያው ደግሞ የገዠው ፓርቲ የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት ገደብ በለለው ሁኔታ ለራሱ ጠቀሜታ እንደፈለገ ሲያውላቸው ተስተውሏል።

በሃገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልክ ገዠው ፓርቲ በብቸኛነት ተወዳዳሪም፣ አወዳዳሪም፣ ታዛቢም የሆነበትና የገዝው ወያኔ/ኢህአዴግ ካድሬዎች በምርጫ ጣቢያዎች በመገኝት ድምጹን ለመስጠት የተሰለፈን ህዝብ አንድ ባንድ የገዠውን ቡድን እንዲመርጡ በማሰፋራራት፣ አልፎ ተርፎም “እዚህ ላይ ምልክት አድርጉ” በማለት ከገዥው ቡድን ውጭ ማንንም እንዳይመርጡ በማድረግ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደዋሉ ተስተውሏል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር “ማን እንዳሸነፈ መናገር የሚችለው ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው” ብሎ እንዳላለ ሁሉ የድምጽ መስጠቱ ሂደት እንደተጠናቀቀ ብዙም ሳይቆይ የራሱን ትእዛዝ ጥሰው የገዥው ቡድን ደጋፊ የሆኑ መገናኛ ብዙሀን (ለምሳሌ አይጋ ፎረም የተሰኝው ድረገጽ) “አዲሰ አባበን ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግ አሽንፏል፣ የመድረክ መሪዎች የሆኑት ፕሮፊሰር በየነ ጴጥሮስ እና ዶክተር መረራ ጉዲና ተሸንፈዋል፣ ኢህአዴግ በመላው ሀገሪቱ አሽንፏል”…. ወዘተ የሚል ዜና አሰራጭተዋል።
እጅግ የሚያሰገርመው ደግሞ፣ ኢህአዴግ አሽንፏል፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራር አባላትም ተሸንፈዋል የተባለው፣ ድምጽ ተቆጥሮ ሳያልቅ መሆኑ ነው።

ይህ ታዲያ የሚያሳየው የተሰጠው ድምጽ ዋጋ እንዳልነበረው እና በያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ማን እንደሚያሸንፍ በወያኔ/ ኢህአዴግ እና ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈጸም ባቋቋመው ምርጫ ቦርድ ቀድሞ እንደተወሰነ ነው።
ባጠቃላይ ፣ ቅድመ ምርጫ የነበረው አካሄድ፣ በምርጫ መዳረሻ የተከሰቱት የመብት ረገጣዎች እና በምርጫው ቀን የተከሰተው ሁሉ ፣ ምርጫው በምንም መልኩ ፍትሃዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበረ በትክክል የሚያሳዩ ነበሩ። በአጠቃላይ ፣ ምርጫ ተብየው በምንም መልኩ አንድን ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማለት የሚያሰችሉ መመዘኛዎችን አላሟላም።

ይህ ሁኔታ በሀገራዊ ደረጃ ለአምስተኛ ጊዜ መደገሙ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አሳዛኝና እጅግ ታላቅ ቁጣን የሚቀሰቅስ ተግባር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) የዚህን የተጭበረበረ ምርጫ አካሄድና ውጤት ሙሉ በሙሉ አይቀበለውም። የተፈጸመውን የመብት ረገጣም ያወግዛል።

የህዝብን መብት እየረገጡ ተደላድሎ በስልጣን ለመቀጠል ማሰብ ከታሪክም ከአካባቢ ሁኔታም አለመማር ነው።ህዝብ መብቱ ሲረገጥ አንገቱን ደፍቶ መገዛቱን ይቀጥላል ብሎ መገመት ደግሞ ከተራ ትምክህት የሚመነጭ ቅዠት ብቻ ነው። ወያኔ/ኢህአዴግ እና ተባባሪው የምርጫ ቦርድ ይህ የህዝብ መብት መጣስ ሊያስከትለው ለሚችለው ማንኛውም አደጋ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ከወዲሁ ልናሰምርበት እንወዳለን።
ለኢትዮጵያ ህዝብ እና የህዝባችንን መብት ለማስከበር ለተንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሁሉ ያለንን አክብሮት እየገለጽን የተነጠቅነውን መብታችንን፣ የታፈነውን ድምጻችንን፣ የተገፈፍነውን የዜግነት ክብራችንን ለማስከበር፣ የጋር ትግሉን በአዲስ ስሜት፣ በህ ብረት፤ አስፈላጊውን መስዋዕት በመክፈል ቆርጠን አንድንቀጥል ጥሪያችንን እናሰማለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ