ምርጫ በሐዋሳ

ምርጫ በሐዋሳ

ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ የደቡብ ክልል መዲና ሐዋሳ መንገዶች ከወትሮው ቀዝቀዝ ብለው ነበር፡፡ በመዝናኛዎች የነበረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር፡፡

ፒያሳ የሚገኘው ሐውልት ፏፏቴ ግን ተከፍቶ ነበር፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ትልልቅ ድንኳኖች ለድምፅ መስጫ ጣቢያነት ተጥለውም ነበር፡፡ 

በምርጫው ዕለት ብዙዎች ድምፅ ወደሚሰጡባቸው ጣቢያዎች ያመሩት ማልደው ነበር፡፡ በየድምፅ መስጫ ድንኳኖች ደጃፍ ላይ ሰዎች ተሠልፈው ይታይ ነበር፡፡ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን ወክለው ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍና የ27 ዓመቱ አካል ጉዳተኛ በቃሉ አሰፋ፣ ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ገደማ ነበር ከታቦር ክፍለ ከተማ ሒጠታ ቀበሌ ወሜ ድምፅ መስጫ የተገኙት፡፡ ባገኘው የመምረጥ ዕድል ‹‹የመጠቀም ግዴታ አለብኝ›› የሚለው በቃሉ ምርጫው እንደ ከንቲባው አቶ ዮሴፍ ሁሉ ለእሱም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡ 

ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ቀበሌ ቁ 4፣ ሐይቅ ዳር ጉዱማሌ ምርጫ ጣቢያ 3፣ መናኸሪያ ፒያሳ ቁጥር ሦስትና በታቦር ክፍለ ከተማ የድምፅ መስጫዎች ጨፌ ተጎዝጉዞ ቡና እየተፈላ በዓል በዓል ይመስል ነበር፡፡ ከበር የተሠለፉ ሰዎችን ስሜት መገመት ግን ከባድ ነው፡፡ ሠልፍ ላይ ጎን ለጎን ተሠልፈው ደቂቃዎችን ቢያሳልፉም ብዙዎች ሲነጋገሩ አይታይም፡፡ በዝምታ ተራቸው ደርሶ ወደ ድንኳን ውስጥ መግባትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ በብዙዎቹ ድምፅ መስጫዎች ስለድምፅ አሰጣጥ በመሀል በመሀል ገለጻ ሲሰጥ ተስተውሏል፡፡

በሲዳማና በሐዋሳ 1,437,697 ሰዎች ካርድ እንደወሰዱና 1,327,082 (624,72  ሴቶችና 702,361 ወንዶች) ድምፃቸውን እንደሰጡ በምርጫው ማግሥት የሲዳማና የሐዋሳ ከተማ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዱካሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በሐዋሳ 151 ድምፅ መስጫዎች የነበሩ ሲሆን፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማግሥቱ ቀኑን ሙሉ ምርጫው ቀጥሎ ነበር፡፡ 

ምርጫ እዚህ ታዛቢ እዚያ 

ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ነበር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸው እየታሰሩና በተለያዩ መንገዶች ጫና እየደረሰባቸው እንደነበር ቅሬታ ማሰማት የጀመሩት፡፡ አንድነት ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት አቶ ሲዳ ኃይሌ፣ ‹‹የስም ፊደል ስህተት አለ›› በሚል ሁለት ታዛቢዎቻቸው መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት አቶ ተስፋ ማርያም ጉቻ ደግሞ፣ ከሐዋሳ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና እሳቸው በሚወዳደሩበት የቦሪቻ ምርጫ ጣቢያ 16 ወይም ሦስት አራተኛ የሚሆኑ ታዛቢዎቻቸው፣ በሐዋሳ ምርጫ ጣቢያ መድረክን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት ዶ/ር አየለ አሊቶም ቦሪቻ ላይ በርካታ ታዛቢዎቻቸው መታሰራቸውንና መደብደባቸውን ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸው ለመታሰራቸውና ደረሰባቸው ለሚሉት እንግልት በምክንያትነት ካስቀመጧቸው መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆነው መገኘታቸው በራሱ፣ ታዛቢ የሚሆኑባቸው ቦታዎች ላይ የተመዘገቡ ባለመሆናቸው ታዛቢነታቸው አግባብነት የለውም መባልና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የሲዳማና የሐዋሳ ምርጫ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ የታሰሩ ታዛቢዎች መኖራቸውን ባይክዱም፣ ታሰሩ በተባሉት ታዛቢዎች ቁጥርና ለእስራታቸው በተሰጠው ምክንያት አይስማሙም፡፡ ቢሆንም ግን የታሰሩበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋገሩ እንደነበርና እንዲፈቱ ትዕዛዝ ያስተላለፉላቸው ታዛቢዎችም እንደነበሩ፣ በምርጫው ዕለት እኩለ ቀን ላይ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ታዛቢዎቹ ስንት ሰዓት ላይ ተፈቱ? ከተፈቱ በኋላስ በቀሪው ጊዜ ከታዛቢነት ኃላፊነታቸው እንዲገኙ ተፈቅዶላቸዋል? እነሱስ ከእስራቱ በኋላ ታዛቢ ለመሆን ፈቅደዋል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ምሽት ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በአንዳንዶቹ ምንም እንኳ የሕዝብ ተወካዮች ቢኖሩም፣ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ያልነበረበትም አጋጥሟል፡፡ አንድ ወይም ሁለት የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ብቻ የተገኙባቸውም እንዲሁ፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ከነበሩበት (ጉድማሌ ቁ 3) ድምፅ መስጫም ሪፖርተር ተገኝቶ ነበር፡፡ 

በመናኸሪያ ፒያሳ ቁጥር 3 ድምፅ መስጫ ድምፅ በመቆጠር ላይ ሳለ ሪፖርተር ያገኘውና አስተያየቱን የጠየቀው በጣቢያው ወጣቶችን ወክሎ ታዛቢ የነበረው የ12ኛ ክፍል ተማሪ፣ ሥልጠና ሲወስዱ አስተያየት እንዳይሰጡ ስለተነገራቸው ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በዚያው ጣቢያ ድምፅ በመቆጠር ላይ ሳለ ምንም እንኳ መንገዱን በድንጋዮች ለመዝጋት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ አንድ ሞተር ድንኳኑን ጥሶ በመግባቱ አራት ሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የምርጫ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ምርጫ በዩኒቨርሲቲ 

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አራት ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት፣ ከዚህ ውስጥም 3,678 ያህሉ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ከምርጫ አስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነው ተስፋዬ ጥሩነህ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ እሱ እንደገለጸው፣ በዩኒቨርሲቲው ስድስት ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ነበሩ፡፡ በእያንዳንዱ ጣቢያ 700 ተማሪዎች ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ብዙ ድምፅ ሰጪ የሌለባቸው እንደ አፋርና ትግራይ ክልሎች እንዲጣመሩ ተደርጎ ነበር፡፡ በዕለቱ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ተሟልተው ቀርበው ስላልነበር፣ በማግሥቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ ምርጫው እንዲቀጥል መደረጉን ሰኞ ጠዋት በዩኒቨርሲቲው ተገኝቶ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

በምርጫ ጣቢያዎቹ ረዥም ሠልፎች ታይተዋል፡፡ ጣቢያዎቹ የነበሩበት የዩኒቨርሲቲው አካባቢ በእንቅስቃሴ የተሞላ ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርካታ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ተማሪዎች እንዲመርጡ መደረጉ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ብቻም ሳይሆን፣ በዚህ ምርጫ የግቢያቸውን ፍትኅዊነት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ይህ እውነት ዴሞክራሲ ስለመስፈኑ ያረጋግጥንበት ነው፤›› ያለው ከምዕራብ ሐረርጌ ገለምሶ የመጣው የአንደኛ ዓመት ጋዜጠኝነት ተማሪ ዮናስ ወንድሙ ነው፡፡ ከአርባጉና ወረዳ የመጣችው ሰላማዊት ፀጋዬ (ሲዳምኛ ቋንቋ ተማሪ) የዮናስን አስተያየት የምትጋራና የምርጫ አስተባባሪም ነበረች፡፡ 

የሌሎች ተማሪዎችም ሐሳብ ተመሳሳይ ነው፡፡ ምርጫው የዴሞክራሲየዊ ሥርዓት መገለጫ እንደሆነና ለሕዝብ ሰላምና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሪፖርተር በግቢው በነበረው የአንድ ሰዓት ቆይታ ተዘዋውሮ አስተያየት ሲጠይቅ ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው ተማሪዎች አላገኘም፡፡ ምንም እንኳ ተማሪዎቹ ምን ያህል ዩኒቨርሲቲውን ይወክላሉ የሚለው ጥያቄ ቢነሳበትም፣ የተገኙት አስተያየቶች ተመሳሳይ መሆን የሚናገረው ነገር ይኖራል፡፡ 

በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለያዩ ሥርዓቶች የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ስለሕዝብ ጥቅም፣ ነፃነትና ሌላም ሌላም በመጠየቅ የታገሉ መሆናቸውን በማስታወስ፣ በኢሕአዴግ ሥርዓት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተማሪዎች የተለያዩ ሐሳቦች (የሚቃረኑም ሊሆኑ ይችላሉ) የሚንፀባረቁባቸው መሆን እያቆሙ ነው የሚለው ከዚህ ቀደምም በበርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጭምር ይገለጽ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ስለዛሬው ብቻም ሳይሆን ስለቀጣዩ የአገሪቱ ፖለቲካ ብዙ የሚናገረው ሊኖር ይችላል የሚለው ብዙዎችን ያነጋግራል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ምክንያቶች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኢሕአዴግ አባል መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ 

የምርጫው ማግሥት 

በምርጫው ማግሥት ጠዋት በነበረው ቅኝት በአንዳንዶቹ ጣቢያዎች ውጤት ሲለጠፍ በሌሎች ደግሞ አልተለጠፈም ነበር፡፡ የምርጫ አስፈጻሚ ከቤት ከእንቅልፉ ተቀስቅሶ እንደዋዛ አጣጥፎ የያዛቸውን ሁለት የውጤት ወረቀቶች ሲለጥፍ በአንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያ ተስተውሏል፡፡ አንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ ከፕላስቲክ ጠርሙስ ኮላ በእንጨት እየተሟጠጠ ውጤት ለመለጠፍ ሲሞከር፣ በቦታው የነበሩ ሰዎች የምርጫው በጀት ይህን ታሳቢ አላደረገም? በሚል ቀልድ በሥፍራው የነበሩትን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡