ምርጫ በሐድያ ዞን

በደቡብ ክልል የሚገኙ 123 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፎ ለመያዝ ምርጫ ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል አንዷ፣ በሀድያ ዞን በምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የምትገኘው የሾኔ ከተማ ነች፡፡
ምሥራቅ ባደዋቾ በ30 ቀበሌዎችና በ72 የምርጫ ጣቢያዎች ሲከፋፈል፣ በዚሁ ዞን የምትገኘው ሾኔ ከተማ ደግሞ በስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ በሾኔ ለዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ የተመዘገቡት መራጮች ደግሞ 61,101 ናቸው፡፡
በከተማዋ የሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎችም ጤና ኬላ፣ ፀረ ኤድስ 1 እና 2፣ ታተም፣ መናኸሪያና ማክማማ የተሰኙ ናቸው፡፡
የወቅቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበርና በተቃውሞ ፖለቲካ ጐራው ዘለግ ያለ ዕድሜ ያስቆጠሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ በዚሁ ዞን በሚገኘው አንደኛ ሀሙበርሴ በተባለ የምርጫ ክልል አካባቢ ተወልደው ያደጉና በሥፍራውም ለሦስት ጊዜያት ያህል ምርጫውን አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው፣ በሥፍራው የሚደረገውን ውድድር ለመዘገብ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በከተማው እንዲከትሙ አድርጐ ነበር፡፡
ፕሮፌሰሩ በ1987 ዓ.ም.፣ 1992 ዓ.ም. እና እንዲሁም በ1997 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫዎች በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ደግሞ በገዥው ፓርቲ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ተወካይ አቶ ዮሴፍ ዳኤሞ ተሸንፈው ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩንና የገዥው ፓርቲ ተወካይ የሆኑትን አቶ ዮሴፍን ለመወዳደር ደግሞ የሰማያዊና የቅንጅት ፓርቲዎች ተወካዮቹ የሆኑት አቶ መብራቱ ተካና አቶ ያሬድ ደበበ ተመዝግበዋል፡፡
በዚሁ ከተማ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ፕሮፌሰር በየነ ድምፃቸውን የሚሰጡበት የምርጫ ጣቢያ ማክማማ የሚባል ሲሆን፣ በድምፅ መስጫው ዕለት ግን ፕሮፌሰሩ በሥፍራው ተገኝተው ድምፅ አልሰጡም፡፡ በአንፃሩ በፀረ ኤድስ አንድ የምርጫ ክልል ድምፅ የሚሰጡት አቶ ዮሴፍ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ቀደም ብለው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ያልመጣሁት ምርጫው ሥነ ሥርዓቱ ተጥሶ ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ስለተረዳሁ ወደዚያ ለማድረግ ያሰብኩትን ጉዞ በመተው፣ እዚሁ ማዕከል ሆኖ ሁኔታዎችን መከታተል የተሻለ ይሆናል በሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዞኑ ከምርጫው ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ደግሞ የምሥራቅ ባደዋቾ መድረክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ ኤልያስ ሀደሮን ማነጋገርና መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ምርጫ በሾኔ
የሾኔ ከተማ በምርጫው ዋዜማ በጣም ቅዝቅዝ ያለ እንቅስቃሴ የሚታይባት ነበረች፡፡ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦችን በመጠየቅ ሪፖርተር መረዳት እንደቻለው፣ ከተማዋ ለወትሮው ሞቅ ያለች ነበረች፡፡ የምርጫ ዋዜማው ግን ከተማዋን ቀዝቀዝ እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡
ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ደግሞ የከተማዋና የነዋሪዎቿ እንቅስቃሴ እጅጉን የተገደበ ነበር፡፡ ለወትሮው በክልል ከተሞች ወዲህና ወዲያ የሚሉት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጆች) ቢሆኑም እንኳን፣ አልፎ አልፎ ውርውር ከማለትና ከጥቂት ሞተሮች እንቅስቃሴ በስተቀር ከተማዋ ፀጥ ረጭ ብላ ከእንቅስቃሴ ነፃ ሆና ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የምርጫው ዕለት
በዕለቱ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የምርጫውን ሒደት በንቃት እየታዘቡ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ የአብዛኛዎቹ ምላሽ ችግር እንዳላገጠማቸው የሚገልጽ ነበር፡፡
ከዚህ በተለየ ግን የወረዳው የመድረክ ሊቀመንበር የምርጫው ዕለት ቀትር ሊሆን ሲቃረብ በተለያዩ ቦታዎች የመድረክ ተወካዮች ከምርጫ ጣቢያዎች ተባረዋል የሚል ቅሬታዎችን፣ ወደ ምርጫ ጣቢያውና ወደ መገናኛ ብዙኃን እየደወሉ ያሳውቁ ነበር፡፡
ቡልጊታ በተባለው የምርጫ ጣቢያ የመድረክ ተወካይ ከምርጫ ጣቢያው እንዲወጣ ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር፡፡ የቡልጊታ 02 የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተረፈ ዴንሴሞ ግን የተባለውን በመቃወም የመድረክን ክስ አጣጥለዋል፡፡
በተመሳሳይ እንዲሁ መድረክን የወከሉት አቶ ዓለሙ ኦርዶሎ በጣቢያው ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ከመግለጽ ባለፈ፣ ‹‹አንድ ግለሰብ በርከት ያሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን የምርጫ ኮሮጆ ውስጥ ሲከት አይቻለሁ፤›› በማለት በሥፍራው ለተገኙ የጋዜጠኞች ቡድን ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚ አሁንም ክሱ ከእውነታ የራቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሒደቱ በሥነ ሥርዓት ለመካሄዱ አባሪ የሚሆኑ አቶ ዓለሙ የፈረሙባቸውን የቃለ ጉባዔ ሰነዶችን በማሳየት የተባለው ሀሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በሥፍራው የነበሩ የሰማያዊና የቅንጅት ፓርቲ ተወካዮችም አቶ ዓለሙ ያቀረቡትን ክስ አለመመልከታቸውን በመግለጽ፣ ከተወካዩ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
ሲቄ 02 የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ያዕቆብ ዮሴፍ በበኩላቸው፣ ‹‹መድረክ ያቀረባቸው ክሶችና ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ችግር አለባቸው በተባሉ አካባቢዎች በአካል በመገኘትና የሌሎች ፓርቲዎችን ተወካዮች በማናገር እንዳረጋገጥነው የቀረበው ቅሬታ ተጨባጭነት የሌለውና አሉባልታ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ ከመድረክ ተወካይ በኩል ይቀርብ ከነበረ ቅሬታ በስተቀር ሌሎቹ ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ያቀረቡ ፓርቲዎች ያነሱት ቅሬታ አልነበረም፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ከቀትር በፊት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ መራጮች ድምፅ ሰጥተው ሄደዋል፡፡