የሆላንድ ካር ባለቤት ያቀረቡት ዕቅድ ተቃውሞ አስነሳ

– የኩባንያው ንብረት መዘረፉ ይነገራል
የከሰረው የሆላንድ ካር ኩባንያ ባለቤት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ከሦስት ዓመት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ አገር ቤት በመመለስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ኩባንያቸውን ለመታደግ ያስችላል ብለው ያቀረቡት ዕቅድ ከድርጅቱ ደንበኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡
ኢንጂነር ታደሰ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ የከሰረው ኩባንያቸው በሐራጅ ቢሸጥ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ገልጸው፣ ይልቁንም ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕቅድ ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነር ታደሰ ሞጆ በሚገኘው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙትን ያልተገጣጠሙ መኪኖች ገጣጥሞ የቅድሚያ ክፍያ ለከፈሉ ደንበኞች በማስረከብ፣ በቀጣይም ኩባንያው ያለበትን የባንክና የመንግሥት ዕዳ ለመክፈል ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ዕቅዳቸውን ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘቱ የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን፣ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ስድስት ሚሊዮን ብር ይዘው መምጣታቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
ኢንጂነር ታደሰ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኩባንያው ደንበኞች አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከኩባንያው መኪና ለመግዛት ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው መኪኖቻቸውን ሳይረከቡ የቀሩ ግለሰቦች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የከሰረው የሆላንድ ካር ገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ፍሬሕይወት ወልደሃና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንጂነር ታደሰ ከመኪና ገዢዎች ጋር ሳይመክሩ ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሜዲካል ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ባለሀብቱ ያቀረቡት ዕቅድ አዲስ አለመሆኑን፣ ለኪሳራ አጣሪ ዳኛና ለገንዘብ ጠያቂዎች ኮሚቴ ቀርቦ ተጨባጭ ማስተማመኛ የሌለው በመሆኑ ውድቅ የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹በዕቅዱ መሠረት ኢንጂነር ታደሰ ስድስት ሚሊዮን ብር ይዤ መጥቻለሁ ነው የሚሉት፡፡ ኩባንያው ያለበት ዕዳ በትክክል መናገር ባይቻልም፣ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ስድስት ሚሊዮንና 80 ሚሊዮን ብር በጣም የተራራቁ ናቸው፤›› ያሉት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ‹‹ይህንን ዕቅድ መኪና ገዢዎችን (የኩባንያው ደንበኞችን) ሰብስበው ቢያወያዩ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ካለው ሁኔታ ግለሰቡ በተጨባጭ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ደንበኞች የደረሰባቸውን ችግር ለመፍታት ያደረጉት ጥረት የለም፡፡ ከዘመን ባንክ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ከደንበኞች ጋር ያደረጉት ውይይት የለም፤›› ብለዋል፡፡
ደንበኞች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ሲከታተሉ ብዙ ውጣ ውረድ እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ የኩባንያው ባለቤት አገር ጥለው በመኮብለላቸውና ኩባንያው በመዘጋቱ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሒደት ውስጥ ኪሳራ መታወጁን፣ የኪሳራ አጣሪ ዳኛና ንብረት ጠባቂ መሾሙን አስረድተዋል፡፡ ገንዘባቸውን ከፍለው ንብረታቸውን ያልተረከቡ ግለሰቦች እንደገና ገንዘብ በማዋጣት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ወደመቋጫው ላይ ሲደረስ፣ ባለሀብቱ ከስደት ተመልሰው የሰጡት መግለጫ ውዥንብር እንደፈጠረም አመልክተዋል፡፡
‹‹መንግሥት ከለላ አድርጎልኝ መጣሁ ቢሉም በትክክል ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ አቅም ይዘው እንዳልመጡ ድርጅቱ ያለበት ዕዳና ያለው ንብረት በግልጽ ያሳያል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መኪኖችን አስረክባለሁ ሲሉ ለዚህ የሰጡት ምንም መተማመኛ የለም፡፡ ከዚህም አልፎ ደንበኞች ለዳኝነት፣ ለጠበቃ፣ ለንብረት ጥበቃና ለመሳሰሉት ተያያዥ ወጪዎች ያወጡትን ተጨማሪ ገንዘብም ሆነ የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ኢንጂነር ታደሰ የጠቀሱት ምንም ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የኩባንያው ደንበኞች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተው የተፈረደላቸው አሉ፡፡ በሒደት ላይ ያሉ አሉ፡፡ ይግባኝ የጠየቁ አሉ፡፡ ተወስኖላቸው የፍርድ አፈጻጸም የሚጠብቁ አሉ፡፡ በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ የደንበኞች ፍላጎት ግልጽ ነው፡፡ ገንዘባቸውን ማግኘት ነው፡፡ የተወሰኑት መኪናቸውን ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛው ግን የከፈለውን ገንዘብ ከነኪሳራው ማግኘት ይፈልጋል፤›› ያሉት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡት ዕቅድ በኮሚቴያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ አስረድተዋል፡፡
‹‹ይዘውት የመጡት ሐሳብ ንብረታችንን እንደምናገኝ ማስተማመኛ ስለሌለው አልተቀበልነውም፡፡ በፍርድ ቤት ሒደት እንጨርሳለን፡፡ ዳር የደረሰ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ኢንጂነር ታደሰ ኮሚቴውን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ደንበኞችን ማነጋገር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ደንበኞች ምን ይላሉ ብለው ማዳመጥ አለባቸው፡፡ አጠቃላይ ስብሰባ ተጠርቶ ከደንበኞች ጋር መወያየት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
የሆላንድ ካር ንብረት የአገር ሀብት እንደሆነና ንብረት ለመሸጥ ብዙም ፍላጎት እንደሌለ የሚናገሩት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ አዋጭ የሆነና ለሁሉም ወገን የሚጠቅም ዕቅድ ይዞ መቅረብ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከሆላንድ ካር መኪና ገዝተው ያልተረከቡ ሰዎች ከ200 በላይ ናቸው፡፡ ለኩባንያው ብድር የሰጠው ዘመን ባንክ 34 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈልጋል፡፡ የጉምሩክ ቀረጥና ግብር ዕዳ እንዲሁም የኩባንያ ሠራተኞች የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ኢንጂነር ታደሰ የኩባንያቸው ንብረት 180 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትና ኩባንያው ያለበት ዕዳ 63 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኪሳራ አጣሪ ቡድኑ ይህን አልተቀበለም፡፡ የኪሳራ መርማሪ ዳኛ አቶ አሰፋ ዓሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተመሰከረለት የዋጋ ገማች የተመነው የሆላንድ ካር ንብረት 83,058,533 ብር ነው፡፡ ኩባንያው ላይ የቀረበው የዕዳ ጥያቄ 160 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ፣ ከዚያ ውስጥ አጣሪ ቡድኑ መርምሮ በመረጃ ያረጋገጠው 74 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አሰፋ ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡትን ዕቅድ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡ ባለሀብቱ በአካል መጥተው እንዳላናገሯቸው አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥ ከአንድ ወር በፊት የአገሪቱ የንግድ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የስምምነት ሐሳብ (Composition Proposal) በጠበቆቻቸው አማካይነት ማቅረባቸውን አልሸሸጉም፡፡
‹‹የኪሳራ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ፣ ዕዳ ከተጣራ በኋላ ባለቤቱ ድርጅቱን እንደገና ላንቀሳቅሰው እችላለሁ፣ በሐራጅ ቢሸጥ እንጎዳለን፣ ባለቤቶቹ ገንዘብ ጠያቂዎቹ ይጎዳሉ፣ ኩባንያውን አንቀሳቅሼ የእነርሱንም ዕዳ እከፍላለሁ የሚል ዕቅድ አቅርበው ነበር፡፡ ገንዘብ ጠያቂዎች ከተስማሙ (የማይስማሙ ከሆነ እንኳ ፍርድ ቤት ካፀደቀው) መልሰው ሊሠሩ ይችላሉ የሚል የሕግ መብት ስላለ፣ ያንን መብታቸውን ለመጠቀም የስምምነት ሐሳብ ከአንድ ወር በፊት ልከው ነበር፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ በስምምነት ሐሳቡ ላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ነቅሰው አውጥተዋል፡፡
‹‹ስድስት ሚሊዮን ብር አገኘሁ ይላል፡፡ ይህ ገንዘብ ያሠራል አያሠራም የሚለውን ለመወሰን አንችልም፣ ሙያችንም አይደለም፡፡ በሕግ የሚጠየቅ ለገንዘብ ጠያቂዎች ዋስትና ተቀማጭ መደረግ አለበት ይላል፡፡ በተጨባጭ ይህን አላደረጉም፡፡ ለማድረግ ስለመቻላቸውና ፈቃደኛ ስለመሆናቸው የገለጹት ነገር የለም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ዕቅዱን እንደማንቀበል በጽሑፍ በጠበቆቻቸው በኩል ምላሽ ሰጥተናል፤›› ብለዋል፡፡
በፍርድ ሒደት ብዙ ርቀት ሄደው፣ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ንብረት ተቆጥሮ እንዲጠበቅ አድርገው፣ ከብዙ ትግል በኋላ ወደ ጨረታ ሒደት በገቡበት ወቅት ኢንጂነር ታደሰ በድንገት ከተሰወሩበት ብቅ ብለው መንግሥት ከለላ ሰጥቶኝ መጥቻለሁ በማለት የሰጡት መግለጫ፣ ሁሉንም ወገኖች ግራ ያጋባና የጨረታ ሒደቱንም እንዳጨናገፈ አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ገንዘባቸውን ከፍለው መኪናቸውን ሳይረከቡ የቀሩ ግለሰቦች ባዋጡት ሁለት በመቶ ገንዘብ ቢሮ ተከራይተው ባቋቋሙት ተቋም ሥራቸውን እንደሚያካሂዱ የገለጹት አቶ አሰፋ፣ ግለሰቦቹ በፊት የተቀሙት ገንዘብ ሳያንስ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን፣ ይህን ገንዘብ በጥንቃቄ ሥራ ላይ በማዋል ተቋሙ የኩባንያው ደንበኞች ያጡትን ንብረታቸውን ለማስመለስ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ዘመን ባንክ አለኝ የሚለውን ገንዘብ ለማስመለስ በመያዣነት የያዘውን የኩባንያውን ንብረት (ፋብሪካ፣ መጋዘንና ሕንፃ) ለመሸጥ ሲነሳ እስከ ሰበር በደረሰ የፍርድ ቤት ክርክር ማስቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ አለኝ የሚለውን መብቱን በፍርድ ቤት ያሉ ክርክሮች ሲያልቁ ከተወሰነለት ገንዘቡን እንዲወስድ ተስማምተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞችም በፍርድ ቤት አስወስነው የድርጅቱን መኪኖች ለማሸጥ ሲሞክሩ ማሳገዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን 330 ንብረትና ገንዘብ ጠያቂዎች ያሉ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካከል 242 ያህሉ መኪና ገዢዎች 74 ደግሞ የኩባንያው ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኪሳራ መርማሪውና ንብረት ጠባቂው ከዘመን ባንክ ጋር ተባብሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ተረድተው የኩባንያውን ንብረት በጨረታ ለመሸጥ በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያውን አስነግረዋል፡፡ ለማስታወቂያ ብቻ ከ109 ሺሕ ብር በላይ ማውጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አሰፋ፣ ስምንት ድርጅቶች የጨረታ ሰነድ መግዛታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የኩባንያው ንብረቶች በአጠቃላይ በ83,058,533 ብር የመነሻ ዋጋ ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡
የጨረታ ሰነዱን የገዙት ኩባንያዎች ሞጆ የሚገኘውን የድርጅቱን ፋብሪካና ሌሎች ንብረቶች እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ ጨረታው ሊዘጋ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ኢንጂነር ታደሰ በድንገት የሰጡት መግለጫ ገዢዎችን እንዳራቀ አቶ አሰፋ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በጨረታው መዝጊያ ዕለት ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢንጂነር ታደሰ ጠበቃ የኩባንያው ንብረት እንዳይሸጥ የሚከላከል የፍርድ ቤት ማገጃ ለእነ አቶ አሰፋ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የጨረታው ሒደት ተቋርጧል፡፡
‹‹በሕግ ተቀባይነት ያለው አሠራር የሚመስለን ዋስትና የመስጠት አቅም ካላቸው፣ ገንዘብ ጠያቂዎችን በኮሚቴያቸው አማካይነት አነጋግረውና ተስማምተው ያንን ስምምነት በፍርድ ቤት አፅድቀው ወደ ሕጋዊ አሠራር መግባት ነው፡፡ አሁን የሰጡት መግለጫ ግራ መጋባት ፈጥሮ ሥራውም ቆሟል፡፡ ይህ የበለጠ ችግር፣ የበለጠ ጥፋት እንዲደርስ ያደርጋል እንጂ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፤›› ያሉት አቶ አሰፋ፣ በቀጣይ ምን እንደሚሆን መናገር እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡
የኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኢንጅነር ታደሰ፣ ያቀረቡት ዕቅድ በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደራድረው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸው ወደ አገር ቤት እንደተመለሱ አስታውሰዋል፡፡
‹‹የቀረበው ዕቅድ ዋስትና አይሰጥም ለተባለው ንብረቱ የሚገኘው በእጃቸው ነው፡፡ በእጃቸው ላለ ንብረት እኔ እንዴት ዋስትና ልሰጥ እችላለሁ? እኔኮ መኪኖቹን ስጡኝና ገጣጥሜ ሸጬ ልስጣችሁ አላልኩም፡፡ እኔ ያልኩት የመንግሥትም ተወካዮች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እኔ ባመጣሁት ገንዘብ የቴክኒክ ጉዳዮችን ላመቻችና መኪኖቹን ገጣጥመን፣ እሴት ጨምረን ይሸጡና ደንበኞች መኪኖቻቸውን ይረከቡ፡፡ በቀጣይም ሌሎች ባለዕዳዎች ገንዘባቸው ይከፈላቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢንጅነር ታደሰ በአካል መጥቶ አላናገረንም ለሚለው አቤቱታ በሰጡት ምላሽ፣ ከመጡበት ቀን ጀምሮ የኩባንያው ንብረቶች እንዳይሸጡ ለማሳገድ ሩጫ ላይ ስለነበሩ የሚመለከታቸውን ደንበኞች በጊዜ እጥረት ምክንያት እንዳላወያዩ አምነዋል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ተወካዮች ባሉበት በቅርብ ቀን ከደንበኞች ኮሚቴ፣ ከመርማሪ ዳኛና ከንብረት ጠባቂ ጋር ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞጆ ከሚገኘው የሆላንድ ካር መኪና መገጣጠሚያ 610 የመኪና ጎማዎች ከነቸርኬያቸው በቅርቡ መዘረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ፍሬሕይወት እንደማንኛውም ሰው መረጃውን እንደሰሙ ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አሰፋ በበኩላቸው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለና ለፍርድ ቤት የቀረበ በመሆኑ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡
ኢንጅነር ታደሰ በበኩላቸው በሁኔታው ማዘናቸውን ለሪፖርተር ገልጸው፣ ‹‹610 የመኪና ጐማ ከነቸርኬው ሲዘረፍ ንብረት ጠባቂዎች የት ናቸው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ኢንጅነር ታደሰ፣ ‹‹610 ጐማ ለማጓጓዝ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህ ታቅዶና በቂ ዝግጅት ተደርጐ የተፈጸመ ወንጀል ነው፡፡ ንብረት ጠባቂዎች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ ንብረቱን ፈርመው የተረከቡ ሰዎች ያስጠይቃቸዋል፡፡ 610 ጐማ ማለት የ110 መኪኖች ጐማዎች ተሰርቀዋል ማለት ነው፡፡ ምን ንብረት እንዳለና ምን ንብረት እንደተሰረቀ አይታወቅም፡፡ የንብረቱ ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም እርስ በርስ መወነጃጀሉ ቀርቶ በውይይት ችግሮችን ፈቶ ለሁሉም ወገን የሚጠቅም የመፍትሔ ሐሳብ ላይ መድረስ እንደሚበጅ፣ መንግሥትም ያስቀመጠው አቅጣጫ ይህንኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡