ከየመን 2,524 ዜጎች መመለሳቸውን መንግሥት አስታወቀ

የመን ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አደጋ ላይ የወደቁ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሆኑ በውል ባይታወቅም፣ ከአራት ሺሕ በላይ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በአስቸኳይ ለመመለስ ሰንዓ በሚገኘው ኤምባሲ መመዝገባቸው ተገለጸ፡፡
ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የገቡትን ጨምሮ 2,524 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉን መንግሥት አስታወቀ፡፡
በዕለቱ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ይገባሉ ተብሎ የተጠበቁት የየመን ተመላሾች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ሲደርሱ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ደከምከም ያሉና ሕፃናት የያዙ ተመላሾች ይበዙ ነበር፡፡
በዕለቱ ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 260 መሆኑን፣ ቀደም ሲል የገቡትን ጨምሮ እስካሁን 2,524 ስደተኞች ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ ዶ/ር ቴድሮስ በሥፍራው ለተገኙት ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የየመን መንግሥትን በምትደግፈው ሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማፂያን መካከል በተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት በተለይ የውጭ አገር ስደተኞች አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ምክንያት በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ፍርኃትንና ድንጋጤን ፈጥሮ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተመላሾች ተናግረዋል፡፡ ተመላሾቹ እንደሚሉት፣ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎችና በጠረፍ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡
መንግሥት በቀን ከ200 እስከ 400 ስደተኞች ወደ አገራቸው እየመለሰ መሆኑን፣ እስካሁን የተመዘገቡት ከ4,000 በላይ ዜጎች በሚቀጥሉት አራትና አምስት ቀናት ውስጥ ጠቅልለው ወደ አገራቸው እንደሚገቡ ዶ/ር ቴድሮስ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ተመላሾች ፊታቸውን ሲያዞሩ ከተመላሾቹ አንዱን ወጣት፣ ‹‹ተቸገራችሁ አይደል? ዘገየንባችሁ? ኤርፖርቱ እኮ ጥቃት ስለደረሰበት የእሱን ዕድሳት እየጠበቅን ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፤›› ሲሉት፣ ወጣቱም መልሶ፣ ‹‹ዶ/ር በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ በተቻላችሁ መጠን ደርሳችሁልናል፡፡ ረድታችሁናል፤›› በማለት መልሶላቸዋል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አስተያየት ነበራቸው፡፡
በየመን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሊቢያ በኢትዮጵያን ላይ የተፈጸመው ዓይነት ጉዳት እንዳለ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እስካሁን ይህ ነው የሚባል ጉዳት የደረሰበት ሰው የለም፡፡ ለደከሙትና ለታመሙት ቅድሚያ ሰጥተን ነው እያመጣን ያለነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከተመላሾች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት መኮንን ገበየሁ ሁኔታውን በተመለከተ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በሶማሊያ በኩል በባህር አድርጎ ነበር ወደ የመን የገባው፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እምብዛም አስቸጋሪ ነገር አልገጠመውም፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ግን፣ ‹‹ወደ አገሬ የምገባበት ቀን ናፍቆኝ ነበር፡፡ በጣም ነው የሚያስፈራው፤›› ብሏል፡፡ መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ኤምባሲ ሄደው መመዝገብ እንዳለባቸው የሰማው መኮንን፣ ተቀጥሮ ይሠራው የነበረውን አስተናጋጅነት ጥሎ መምጣቱን ይናገራል፡፡ እሱ ይኖር የነበረው በዋና ከተማ ሰንዓ ነበር፡፡ በጣም የሚያስጨንቀው በጠረፍ አካባቢዎች ስላሉት ኢትዮጵያውያን መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞች የተደረገለትን ትብብርም አመስግኗል፡፡
ፈይሰል አህመድም ከተመላሾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በጂቡቲ በኩል ነበር ወደ የመን የተሻገረው፡፡ ያለፈበትን አሰቃቂ ጉዞ ማስታወስ አይፈልግም፡፡ ‹‹ስደት ሲባል አስቸጋሪ ነው፡፡ የእኛ ዓይነቱ ስደት ሕገወጥ ነው፡፡ ሕጋዊ የሚባል ስደት የለም፤›› በማለት በስደት ሆኖ የደረሰበት የከፋ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል የመን እንደገባ ገጠር በመሄድ በአንድ እርሻ ውስጥ ተቀጥሮ ያርስ እንደነበር ይናገራል፡፡ ቀጥሎም እርሻውን ትቶ ወደ ከተማ በመግባት ተቀጥሮ የፅዳት ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ‹‹አሁን በጣም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ መብራት የለም፡፡ ውኃ የለም፡፡ ምግብ የምናበስለው በጋዝ ነበር፡፡ ጋዝ ደግሞ አይገኝም፡፡ ችግር ላይ ወድቀን ነበር፤›› ብሏል፡፡
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ስደተኞች የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው የገለጸው ፈይሰል፣ በኢትዮጵያዊያን ላይ በተለይ የሚደርስ አደጋ እንዳለ ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ ፈይሰል፣ ‹‹ሁለቱም ወገኖች አንደኛው የሌላኛው ደጋፊዎች ናችሁ እያሉ ያስፈራሩናል፡፡ ነገር ግን በተለየ ጥቃት አልፈጸሙብንም፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ የከፋ ነው፡፡ እላይህ ላይ ቤት ይፈርሳል፤›› ብሏል፡፡
የፈይሰል ሥጋት ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን በጠረፍ አካባቢዎች ስለሚሠሩና ጦርነቱም የከፋው እዚያ ስለሆነ ጉዳት እየደረሰባቸው ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ ‹‹እንዳንድ ጊዜም አልቃይዳ ናችሁ ይሉናል፤›› ብሏል፡፡ ‹‹እባክህን የተቀሩት ኢትዮጵያውያንን እንዳይገድሏቸው መንግሥት እንዲረዳቸው ንገርልን፤›› በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ከሊቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የማስወጣት ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን፣ በቅርቡ በሁለቱም አካባቢዎች (በትሪፖሊና በቤንጋዚ) የሚገኙት 100 ስደተኞችን ለማስመለስ መንግሥት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡