አመራር አልባ የኾነው የአ/አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ሕግ አፍራሽ ይኹንታ በተሰጠው የሥራ አስኪያጁ ሕገ ወጥ የሓላፊዎች ዝውውር እና እግድ እየታመሰ ነው፤ ከጠቅ/ቤተ ክህነቱ ጋር ያለው ግንኙነት ተስተጓጉሏል
- ያለሊቀ ጳጳሱ ዕውቅናና ፈቃድ በአምስት ሓላፊዎች ላይ እግድ እና ዝውውር ተፈጽሟል
- አካሔዱ በሊቀ ጳጳሱ ሕገ ወጥ ነው በሚል ታግዷል፤ የሊቀ ጳጳሱ እግድ በፓትርያርኩ ተሽሯል
- የተጠናከረው የሰንበት ት/ቤቶች ፀረ ኑፋቄ እና ፀረ ሙስና መነሣሣት በመንሥኤነት ተጠቅሷል
- ‹‹ያለአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ እና ያለጥናት የአንድ አካባቢ ሰዎችን በመምረጥ የተፈጸመ ነው፡፡›› /ዋና ሓላፊዎቹ/
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በፓትርያርኩ ብቸኛ ምርጫ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች መሾማቸውን ተከትሎ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጋራ የተጀመረው ውዝግብ፣ ከሓላፊዎች ሕገ ወጥ ዝውውር እና የእግድ ርምጃ ጋራ በተያያዘ በመባባሱ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደራዊ አንድነት እና ሰላም አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ፡፡
የሥራ አስኪጆቹን ምርጫ እና ሹመት መነሻ በማድረግ ካለፈው መጋቢት አንሥቶ ተፈጥሮ የቆየው የፓትርያርኩ እና የረዳት ሊቀ ጳጳሱ አለመግባባት ዳግም ወደ ዐደባባይ የወጣው፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በአምስት የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች ላይ ሕገ ወጥ ዝውውር በማድረጋቸው እና በዛሬው ዕለት ደግሞ አንድ ሓላፊን ከሥራ እና ከደመወዝ በማገዳቸው እንደኾነ ተገልጧል፡፡
ዝውውሩ የተፈጸመው ዋና ሓላፊዎቹን በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዋና ክፍሎች መካከል በማሸጋሸግ፣ ወደ ክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች ከደረጃ ዝቅ አድርጎ በመመደብ እንዲኹም ‹‹ለውጡን ተቃውመዋል፤ አሠራሩን አስተጓጉለዋል›› የተባሉ የአስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊውን ከሥራ እና ከደመወዝ በማገድ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በዋና ሥራ አስኪያጁ የተደረገው የዋና ክፍል ሓላፊዎቹ ሕገ ወጥ እና ያልተመከረበት ዝውውር፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው›› የሚለውን የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ድንጋጌ በሰበብነት በመጠቀም ከጅምሩም የሚታወቀውን የፓትርያርኩን ይኹንታና ፈቃድ ማግኘቱን ዛሬ ከቀትር በኋላ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በወጣ ደብዳቤ ተገልጧል፡፡
ፓትርያርኩ፣ በዋና ሥራ አስኪያጁ ለተደረገው የሓላፊዎቹ ዝውውር ዛሬ በይፋ እንደሰጡበት ከመታወቁ አስቀድሞ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የሕግ ድንጋጌ ውጭ የተፈጸመ መኾኑን በመግለጽ ታግዶ እንደነበር ታውቋል፡፡

በሀገረ ስብከቱም ኾነ በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሚደረጉ የሠራተኞች ዝውውር፣ ዕድገት እና ቅጥር ያለሊቀ ጳጳሱ ዕውቅና እና ፈቃድ መፈጸም እንደማይቻል በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ በግልጽ መደንገጉን ረዳት ሊቀ ጳጳሱ በእግድ ደብዳቤአቸው ጠቅሰዋል፡፡ ይኹንና ዝውውሩ እና ሽግሽጉ ከዚኽ መሠረታዊ የሕግ ድንጋጌ ውጭ መፈጸሙን ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አስገንዝበዋል፡፡
አፈጻጸሙ አግባብነት የሌለው ብቻ ሳይኾን ሠራተኞች ባሉበት ቦታ ላይ ተረጋግተው የመሥራት መብታቸውን የሚያሳጣ በመኾኑ በሀገረ ስብከቱ እና በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የተደረገውን ዝውውር እና ሽግሽግ እንዳይፈጸም መሻራቸውን እና ማገዳቸውን ባለፈው ዓርብ ለሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈ ቅዱስ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ባሉበት ውይይት ተካሒዶ፣ የዝውውሩ እና የሽግሽጉ ጉዳይ ተጠንቶ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስም ሓላፊዎቹ ባሉበት ቦታ ላይ ኾነው ሥራቸውን እንዲቀጥሉም አሳስበዋል፡፡
ዝውውሩ፣ ‹‹በማናውቀው ጥፋት ከደረጃችን ዝቅ የተደረግንበት እና ሳንጠየቅ በግብታዊነት የተፈጸመ ነው›› ያሉ አምስት የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከትላንት በስቲያ ፓትርያርኩ ዘንድ ቀርበው አካሔዱ እንዲታረም ጠይቀው እንደነበር ታውቋል፡፡
የሠራተኞችን መብት፣ ደረጃ እና ሞራል ጠብቆ ማዘዋወር፣ ብርቱውን ማነቃቃት እና ደካማውን ማረም አግባብ ቢኾንም የአንድ አካባቢ ብቻ ሰዎችን በመምረጥ ያለጥናት እና ያለበቂ ምክንያት የተፈጸመው ከደረጃ ዝቅ የሚያደርግ ዝውውር ሠራተኞች በሥራ መደባቸው የሥራ ዋስትና እንዳይኖራቸው የሚያደርግ እንደኾነ ሓላፊዎቹ ገልጸዋል፤ ከክርስቶስ፣ ከሐዋርያት እና ከአበው አስተምህሮ ውጭ፣ ‹‹የአንድ አካባቢ ሰዎች ናቸው›› በማለት በዘር እና በብሔር ስሜት ተነድቶ የተወሰደ ርምጃ በመኾኑም ያልተለመደ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እና ፓትርያርኩ ለቆሙለት ዓላማም አፍራሽ መኾኑን በማሳሰብ ከፓትርያርኩ ፍትሐዊነትን እና ሚዛናዊነትን የተጎናጸፈ አባታዊ አመራር እና ውሳኔ እንዲሰጣቸውም ተማፅነው ነበር፡፡