2 Comments on “ለሰማዕታቱ ደም የፍትሕ ጭኽት ድምፅ፤ በዲሲና አካባቢው ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ”

  1. አያልቅበት አለቀበት
    Published on Friday, 08 May 2015 10:11 | Written by Super User | Print | Email | Hits:

    http://ethiochristian.net/

    የክርስቶስ በመሆናቸው ምክንያት “አይሰስ” ብሎ ራሱን በሚጠራ ወንጀለኛ ድርጅት፤ በግፍ በስለትና በጥይት በአሰቃቂ ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን በመገደላቸው ሃገር ከፍተኛ ሃዘን ውርደት እና ቁጭት ውስጥ የከተተ ድርጊት ሆኖአል፡፡ ይህንን መሪር ሃዘን ወደመጽናናት ለመመለስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከፍተኛውን ድርሻ ወስዳ እንደአባት እንደሃገር አንደመሪ ሁሉንም አይነት ሃላፊነት ተወጥታለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊያን በአስገዳጅ ሆንታ በክርስቶስ ስም ህይወታቸውን ያለፈውን የሁሉም እናት በምትሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰማዕት አድርጋ ስለተቀበለቻቸው ፤ ቁጭትን የሚየረግብ መጽናናት ለወላጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው መንፈሳዊ እረፍትን ሰጥታለች፡፡

    እስከሁን በፍጥነት ማንነታቸው የታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ ውጪ የሚገኘትን ሰዎች ለክርስቶስ ብለው ህይወታቸው የተሰዋውን ሀሉ የራሱዋ ሰማዕት አድርጋ የምትቀበልበት መንፈሳዊ ማዕቀፍ ቤተክርስቲያኒቱ ቀድሞም የነበራት መሆኑ ወንጌላዊያን ክርስቲያኖችን ግር ሊያሰኝ እንደሚችል ቢገመትም፤ ቤተክርስቲያኒቱ ከዚህ ቀደምም ገድላቸውን የምታከብርላቸው አውሮፓዊ ሰማእታት እንደነበርዋት ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ይህንንም በቤተክርስቲያኒቱ ፍትሃ መንፈሳዊ 20 ቁጥር755-756 ላይ ያልተጠመቀ ሰው በልቡ አይዘን ስለክርስቶስ የተቀበለው መከራ የተመረጠ ጥምቀት ይሆንለታልና የሞቱን ምሳሌ በተቀበለ ጊዜ በጌታ አምሳል ሞቶአልና ሁለት ልብ አይሁን እነርሱ ቢገድሉት እርሱም ቢገደል ይጸድቃል በደሙ ተጠምቋልና ተብሎ በተገለጸው በቅዱሳን አበው ድንጋጌ መሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰማዕት አድርጋ እንደምትቀበላቸው ሲኖዶሱ ይገልጸል …ይላል አንድ ያነበብኩት የቤተክህነት መግለጫ፡፡ ይህ አንቀጽ የወንጌላዊያኑ በሊቢያ ምድር የኢትዮጵያ ሰማእት ውስጥ የተቀላቀሉትን ለጊዜው የታወቁት ወንድማችን አያልቅበት ስንታየሁና ወንድማችን ብርሃኑ ጌታነህን በሁለት ዋና ዋና ምክንያት ታሪካቸውን በዚህ ጽሁፍ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡

    የመጀመሪያው ሰይጣን እንኩዋን የክርስቶስ በመሆናቸው ሊለያቸው ያልቻለውን የክርስቲያኖችን አንድነት ተረድቶ ሲገድላቸው …የትኛውም አይነት ስነመለኮት መረዳትና ልዩነት ቢኖርም በአንድነት ለክርስቶስ መስዋእት በመሆን ያሳዩ በመሆናቸው የልዩነት ግድግዳ ሳይፈጠር …እነዚህን ወጣቶች ከሌሎች ሰማእታት ሁሉንም ሰማእታት ለማክበር ወንጌላዊያንን የሚያቀርቡ ድልድዮች አድርገን የምናይበት እድል የሚፈጥር ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ሰዎች ማንነታቸው የታወቀው በስተመጨረሻ በመሆኑ ምክንያት በማጽናናት አሁንም እንድትተባበሩአቸው ለመማጸንም ጭምር ሲሆን በዚህ ፅሁፍ ታሪካቸው የታወቀውን ሰዎች አብሬ እዳስሳለሁ….፡፡

    “በባልቻ ስም ምንም አይነት ልገሳ ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለንም” …አቶ ተስፋዬ የባልቻ የቤተሰቡ የመጀመሪያ ወንድም ተናገሩ፡፡ ቀጥለውም…ባልቻ ልጅ አልወለደም እናቱም አባቱም በህይወት የሉም…ሁላችንም በገዛ እጆቻችን እየሰራን ገቢዎችን መፍጠር እንችላለን፡፡ ይልቅስ እኔ ሃዘን የተቀመጥኩት ለእነዚህ አስርና ሃያ ወጣቶች አይደለም፡፡ የማስበው ሃገር ነው፡፡ …ሰው በእምነቱ ምክንያት የሚገደልበትን አለም በምን መልኩ መታገስ ይቻላል…ይህን አይነት ግድያን አናስቆምም ወይ …እስከመቼ እንገደላለን…ለምን ..ለምን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በምንም ምክንያት የነዚህ ወጣቶች ሞት ፓለቲካዊ መልክ ማንም እንዲፈጥርብን አንሻም የምንናገረው ስለሰው ልጅ ብቻ ነው ስለክርስትናችን ብቻ ነው ለማጥቃት ባልወጣንበት የምንገደለው እስከመቼ ነው የሚል ነበር…

    እህቱ እየሩሳሌም …ስለባልቻ የማይቆጫት ና የማትናገረው ነገር የላትም …አቅም አልባነትን ጋሻዋ የሆነው ወንድሟ በበረሃ ውስጥ ተያያዥነት ያለጥፋቱ ሲገደል አይታለች ….ባልቻ እንዴት እጅህ ታሰረ ..እንዴት ወደ ኋላ ታሰርህ ጨርቆስ በዚህ አታውቅህም አለች፡፡ ባልቻ ለቤተሰቦቹ ልጅ ሳይወልድ አንድ ቦታ ታሪኩ ተቋቷል የክርስቶስ ስም ስለተጠራበት ክርስቲያን ኢትዮጵያን የሚወክልኖ በጠላቶቻችን እጅ ህይወቱ አልፋል ሁላችንም እዚያ አንገታችን እንዳልተቆረጠ በማንም ሰው ላይ ያላደረግነውን እንደተደረገብን እናያለን …አንቺ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ….ቀንሽን ጠብቂ …

    የእያሱ ይኩነአምላክ ወንድም ስዩም ይኩነአምላክ …በዚያች ጠባብ ቤት ውስጥ ..ሆኖ የሚናገረውን አጥቶአል፡፡ ወንድሙ ኑሮን ለማሸነፍ ያደረገውን ብርቱ ትግል ይገልጻል ፡፡ ኳታር ሄዶ መኪናውን የትራፊክ ፓሊስ ነጥቆት አስሮት ወደ ሃገር እንደመለሰው አይቶአል፡፡ ለምረቃ የሚዘጋጀውን ወንድሙን ልብስ ሊያለብሰው ወዲህ ወዲያ እያለ ነበር ከዚያ የአይጥ ጎሬ ከመሰለ መንደር ቤተሰቡን የማውጣት ህልም ነበረው…ደካማ እናቱ አህዛን ና በህይወት እያሉ ቤታቸውን መቀየር ይፈልጋል ታናሽ ወንድሙን ለማስተማር አስመርቆ ወንድሜ ለዚህ አደረሰኝ በሚለው የታላቅ ሃላፊነት ለመወጣት ሲታገል ጉዞው በአጭር ተቀጭቶአል፡፡ አንድ ነገር እርግጠኛ ነው የቤተሰቡ አባት ለመሆን ሲታገል በአረመኔዎች እጅ ወድቆ ያለረዳት መከራውን ሲጋተው አይቶአል፡፡

    ጨርቆስ ኢትዮጵያን ወክላ በገባችበት ሃዘን ውስጥ ያልገባ ማንም ኢትዮጵያዊ አልነበረም ፡፡ ለወትሮው በአፍቃሪነት የማይታወቁት ፌደራል ፓሊሶች እንኩዋን(የለቅሶውን ቦታ በተከለለ ቦታ ብቻ ለማድረግ ከቆሙበት ሆነው ) እንዲህ ብለው ሲያለቅሱ አይቻቸዋለሁ….”ምናለ የሚደረስበት በሆነና ተዋግተናቸው እኛን ገድለው ልጆቻችንን በገደሉብን” አሉ በቦታወ ያለሁት እኔ ይህንን ጨመርኩበት እኛ የተሸከምነ ው መሳሪያ እነርሱኑ ልጆቻችንን ነው የመታው ከልጆቻችን ውጪ ጠላቶቻችን መቼ ነው የሚመታው የሚል ተጨማሪ የጸጸት ድምጽ አለበት፡፡ ባስ ሲል በጥይት አልያም በአሳሪ ህጎች ወይም ድህነታችን ውስጥ ታምቀን እንድንቀር ወይም ከዚህ መፈናፈኛ ከሌለው እውነተኛ ተስፋ በማይሰጥ ጥቂቶችን የሚያበለጽግ አሰራር ውስጥ..በአንድ ጊዜ ወይም ቀስ በቀስ ተገድለናል፡፡ ገጣሚው ጌትነት እንዳለው ሙዋችም ገዳይም እኛው ነን ፡፡

    አቶ ጫኔ ልጃቸው እባክህ ልጄ አትሂድብኝ ሲሉ ለምነውት ነበር፡፡ ነገር ግን የእኔን ኑሮ እያየ በመሳቀቁ ምክንያት ..ብዙም እውቅና ከሌለው ኮሌጅ ተመርቆ ገቢ ለቤተሰቡነና ለራሱ መፍጠር ባለመቻሉ በሚጨነቅበት ጊዜ አቶ ጫኔ 600 ብር ከሚከፈላቸው የጥበቃ ስራቸው የተደራጁ የጥበቃ ማህበራት ስራቸውን ስለቀሙአቸው ወደ ቤት መዋል የተገደዱ ሲሆን ልጃቸው ኢየሩስ ስትናገር አባታችን እናታችን ከሞተች ጀምሮ አባትም እናትም ሆኖ በጭንቀት እንዲኖር ተገዶአል አለች፡፡ አቶ ጫኔ አእምሮ ጭንቀት ይዞአቸው ከአማኑኤል ሆስፒታል መድሃኒት እየወሰዱ ነው እንግዲህ አዲሱ አስጨናቂ ጉዳይ የመጣው የሳቸውን ጭንቀት ለመቀነስ ሞት ወይም አውሮፓ ልጃቸውን ለመላክ…እዳገብተው ብዙ ብር አውጥተዋል፡ ፡ በበለጠ ጭንቀት ሃገርን በሚያስጨንቅ ጭንቀት ተደምድሞአል፡፡ በእግዚአብሔርና በትውልድ መካከል በአይኖቻችን ፊት የራሳችንን የወደፊት ሞት ሊያሳይ በሚችል ሁኔታ ታሪካቸው ተደምድሞአል፡፡

    ብሩክ ካሳ ከሁሉም ትንሹ ” ሌሎቹን እንዳስኬደ ለመሄድ የሚያበቃ መሰረታዊ ችግር የለበትም” ሲሉ የሰፈሩ እኩዮቹ ሲናገሩ አድምጫለሁ….ሌሎቹ መሄድ ነበረባቸው ከመሄድ ውጪ ሁሉንም ነገሮች ስላዩ እንኩዋን ሄዱ ባይሞቱብን ግን ጥሩ ነበር ሲል ወጣቱ ሙሴ ስለወጣቶቹ መሄድ በእርግጠኝነት ተናግሮአል፡፡ ብሩክ ግን ከእድሜ እኩዮቹ ጋር የሚካፈለውን በልጽጎ መታየትን በማለምና አሁን ባለበት ሁኔታ የቱንም ያህል ቢቆይ ምንም አይነት ለውጥ አንደማያመጣ በመገመት መሄድ እንደነበረበት አምኖ ሄዶ ህይወቱን ሰውቶአል፡፡ በክርስቶስ ስም በመሞቱ ምክንያት ክርስቶስ በክብር እንደሚቀበለው በማመን እናቱ ተስፋዋን ሰንቃለች፡፡

    በቀለ ታጠቁ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ከስልጢ ዞን እህቱ ኢየሩሳሌም ስትናገር እንደተደመጠው ያንን ወጣት ማጣት አንገቱ ሲቀላ ማየት አሰቃቂ ነበር፡፡ የመቻቻሉ ሰባኪ የሚችለው አጥቶ ሞቷል፡፡ …አሁንም የጨርቆስ ጎረቤቶቹ መሄድ ነበረበት ሲሉ የሚከራከሩለት ነው፡፡ የሚቃወሙት መሞቱን ብቻ ነው፡፡ መሞት ወይም በአግባቡ መኖር የሁልጊዜም ምርጫ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ይላሉ፡፡ ለስብከተ ወንጌል መጥተው ያስተማሩት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘማሪና የወንጌል ሰባኪ ጌታ ኢየሱስ አጠገብ ለመሰቀል ጥያቄ ሲያቀርቡ አብ የወሰነው ነው የሚሰቀለው በማለት ይህንን የክብር ሞት ለመሞት የተመረጡ በመሆናቸው …ጸሎታችን በክብር እንሙት ሆኖ በክብር ለሞቱት ኢትዮጵያ ወጥታ ላለቀሰችላቸው ቤተክርስቲያናችን ..እኛ ሰባኪዎች ብንመኘው የማናገኘውን እነዚህ ወጣቶች ሲያገኙት ደስ ሊላችሁ ይገባል…ብዙ ሰዎች ማንም ሳያውቅላቸው ሞተዋል…ነገር ግን አይሰስ እራሱ ድርጊቱን ቀርጾ ማዋረዱን ለመግለጽ ያህል ስለላከልን …ለእኛ ክብር ናቸው ብለን መልሰንለታል፡፡ ለክርስቶስ መሞት ክብር ነውና…

    የባሪያዋ ልጅ ….አያልቅበት

    አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ ትላለች ወ/ሮ አለሚቱ በላይነህ ፡፡ ያው እንደ ብዙዎች ሁለት በሶስት ሜትር በሆነ ቤት ውስጥ ነው የምትኖረው፡፡ ልጄ አያልቅበትን ለ25 አመት ተመላላሽ የቤት ሰራተኛ ሆኜ በጭንቀት እየኖርን ጌታን ስናመልክ ኖረናል፡፡ የዘወትር ጭንቀቱ የቤታችንን አኑዋኑዋር ለመቀየር መታገል ሲሆን አስረኛ ክፍል ወደ ቴክኒክ ትምህርት መማር ሲኖርበት ተጨማሪ ወጪ አንቺን ከማስወጣ አሁን ገቢ መፍጠር አለብኝ ብሎ ከዚህ ወደ ዚያ ገንዘብ ሊገኝበት የሚችሉትን ስራዎች ሁሉ ሲሰራ ኖሮአል፡፡ ህልማችን አንድ ነው የራሳችን ቤት ኖሮን በሰው ቤት ተቃጥዬ የማገኘውን ገንዘብ ለኪራይ ቤት ከመክፈል ማዳን ነበር፡፡ አያልቅበት ወደ ሱዳን ለመሄድ እቅድ ባወጣ ጊዜ ለምኜዋለሁ… ጌታ ፊት ጸልየናል እርሱ ችግራችንን ያውቃል ፡፡ የኛ እረፍት ደግሞ መንግሰተ ሰማይ ነው” በማለት ሳስረዳው ፤ ልጄ ግን “እማ የቻልነውን ሁሉ ያህል ታግለናል ጸልያናል ስለዚህ እኔ አሁን አንቺን ከሰው ቤት ሰራተኝነት ማውጣት ይኖርብኛል፡፡ እንደሰው መኖር አለብን፤ ያንን የኮንደሚኒየም ቤት እንኩዋን መክፈል ብችል የትም ድረስ መሄድ ይኖርብኛል ሲል ገልጾልኛል ፡፡ ይሄን የማይሞላ ኑሮ ለመለወጥ ሲል ህይወቱን ከፍሎበታል ተስፋችነን አጨልሞታል፡፡

    ጌታ ግን …በእርግጥ እግዚአብሔር የልጄን ጉዳይ አሳይቶኝ ነበር …”ያየሁት ልጄ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ ነበር … ልክ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ ሲሄድ እንደሚታየው ስዕለ ልጄ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ አየሁ ለካ ሊሞት ነው፡፡ እኔ ልጄ ሱዳን እንዳለ ባውቅም የልጄን አልጋ ከምኖርበት ከካዛንቺስ ለማውጣትና ቤቱን በመቀየር ህልሙን ልፈታው ፈለግሁኝ ..ወዲያው ቤቴን ቀየርኩትና አሁን ወደ ምታየኝ ቤት ገርጂ ተከራይቼ ገባሁ ፡፡ አልጋውን እኔ ተሸክሜለት ሄድኩኝ… ይሁን እንጂ ተንበርክኮ መጸለይ አቃተኝ በመንገድ እንባዬ ዝም ብሎ ይፈሳል ለካ ሊሞት ነው፡፡ ልጄ ፎቶውን አይተኸዋል አይደል? እንዴት እንዳቀረቀረ ..ሁልጊዜም ሲጨንቀው አንገቱን አቀርቅሮ ይጸልያል…አያልቅበት በዚያን ጊዜ ጌታሆይ ነብሴን ተቀበል ሲል እየጸለየ ነው፡፡ ልጄ ሁልጊዜ እንዲህ እንደሚያደርግ አውቃለሁ ..

    ወደ ሊቢያ እንደሚሄድ ታውቂ ነበር ?

    ሱዳን እንደሚቆይ እንጂ ሊቢያ እንደሚሄድ ግን አላወቅሁም በእርግጥ ብር ልኮልኝ ነበር የኮንደሚኒየም ክፍያ አላላኩ ትንሽ ወር ሳይልክ እንደሚቆይ ያሳይ ነበር፡፡

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለጅሽን ሰማዕት በማድረጉዋ ምን ይሰማሻል ? ልብ ሆኖብኝ እንጂ ሞቱ አኩሪ ነው ቤተክርስቲያንም ይህንን በማድረጉዋ ደስ ብሎኛል የክርስትና ስሙን ፈልጌ ወደ ቋቋመው ልዩ ቢሮ እወስደዋለሁ፡፡ ብርሃኑና ልጄ አብረን ቤተሰብ ሆነን ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ጌታን ስናመልክ ነበር እንግዲህ የሁለቱንም ልጆች ጉዳይ ይዘን እንሄዳለን…

    ብርሃኑ ጌታሁን ባለቤት ቡርቱካን ጌቱ ሁለት ልጆቹ ኢየሩሳሌም 8 እድሜና ዮናታን 5

    ባለቤትሽ ከቤት ከወጣ ምን ያሀል ጊዜ ሆነው

    አራት ወራት

    ወዴት እንደሄደ የምታውቂው ነገር አለ ?

    ባለቤቴ ከቤት የወጣው ድሬደዋ ንግድ ስራ ፍለጋ መሆኑን ነው፡፡ በትንሽ ጊዜ ስልኩ ስለተቋረጠብኝ በዚህ ጊዜ አደጋ የደረሰበት መስሎኝ ለፖሊስ አመለከትኩኝ ባለቤቴ ጠፍቶብኛል ብዬ…እነርሱም እድሜው ከአስራስምንት አመት በላይ ስለሆነ በፈለገው ጊዜ ራሱን ይደውላል ብለው አበረታቱኝ፡፡ ከወር በሁዋላ ባለቤቴ ሱዳን ከአያልቅበት ጋር መገናኘቱን ሰማሁ ፡፡ ልቤ አረፈ ፡፡ አያልቅበት ሱዳን ውስጥ ሁለት አመት በላይ ቆይቶ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከባለቤቴ ጋር ብዙ ስላሳለፉ፤ ከድሮም ጀምሮ በወንጌል ብርሃን ቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ ስለኖሩ፤ ቤታችንም እንደቤቱ የእናቱ ቤት እንደቤቴ ስለሆነ ተረጋጋሁ ከዚያማ ሊቢያ ላይ ሰዎች ተገደሉ ሲባል በየለቅሶ ቤቱ ሲሄድ ሳለቅስ ቆየሁኝ የራሴን ጉድ ሳላይ፡፡

    እንዴት አወቅሽ ?

    አያልቅበት ሞተ የሚል ወሬ ሰማሁ…ወገቤ ተቆረጠ፡፡ እንደማይለያዩ አውቃለሁ፡፡ ኢንተርኔት ካፌ ሁድኩና ያንን መከረኛ ቪዲዮ አየሁት ባለቤቴ በጥይት ከተገደሉት የመጀመሪያው መሆኑን አየሁ…እዛው ነብሴ ፍስስ ብላ ራሴን ሳትሁ፡፡ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ብቻ ከፍሎልኝ ነው የሄደው አሁን ይቅርታ አድርጌለታለሁ ጉዞውን ሚስጥር ማድረግ ፈልጎ ነበረ በርከት አድርጎ ቢሰጠኝ ኖሮ እጠረጥር ነበር፡፡ አላሰኬደውም ነበር

    ኑሮ ይከብዳችሁ ነበር ?

    የምንኖረው በወንጌል ብርሃን ቤተክርስቲያን ደጃፍ ለይ ጥቅስ በመሸጥ ነው የምንተዳደረው፡፡ በዚህ አይነት ሁለት ልጆች አስተምሮ የቤት ኪራይ ከፍሎ መኖር አይቻልም ፡፡ ስለዚህ ለልጆቹ የወደፊት እድል ሲል የከፈለው ዋጋ ነው ፡፡

    ይህንን ሶስት ወር እንዴት አሳለፍሽ?

    ሁለተኛው ወር ላይ ቤት ኪራይ የምከፍለው ስለሌለኝ የባለቤቴ ጉዋደኞች የአራት መቶ ብር ስራ ሰጡኝ፡፡ ትምህርት ወጪና ቤት ኪራይ ምን ሊሆን እንደሚቻል እንግዲህ ገምቱት፡፡

    እግዚአብሔር ይርዳሽ ሁሉም የክርስቶስ ሰማዕታትን እግዚአብሔር አይጥላችሁም የእግዚአብሔር ህዝብም አይጥላችሁም፡፡

    እሺ እኔ እንደምታየኝ ወጣት ነኝ፡፡ ሰርቼ መኖር እችላለሁ ልጆቼ ግን ምንም አይነት መከራቸውን ላየው አልፈልግም አደራ

    እነግራለሁ ፡፡ በመጨረሻው ከራቱ ከታወቁት ቤተሰቦች ውስጥ የሙዋቾቹ ሶስት እህቶች ስማቸው ኢየሩሳም ሲሆን የአራተኛው የብርሃኑ ልጅ ኢየሩሳሌም ትባላለች 8 ዓመትዋ ነው፡፡

    አንድ መልዕክት ልንገራችሁ ..ሁላችሁም እንደምታውቁት የእግዚአብሔር እጀ ለማዳን ተዘርግቶአል ነው የሚባለው ….ነገር ግን እግዚአብሔር አሁን እንዲህ አለ … “እጄ ለጥፋት ተዘርግቶአል፡፡ ይህ ጊዜ ለእናንተ እራሳችሁን ከኔ ጋር የምታስታርቁበት ይሁናችሁ!”

    ……..www.ethiochristian.net……. Bell of Freedom Church (BF)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*