ትኩረት የሚሹት ሁለቱ የሰማዕቱ የብርሃኑ ልጆች

በግፈኛው አይሲስ ከተሠዉት ወንድሞች መካከል ብርሃኑ ጌታነህ የተባለው በአዲስ አበባ አቧሬ አካባቢ ይኖር የነበረው ወንድም ይገኝበታል፡፡ ብርሃኑ ከሀገሩ የወጣው ከአራት ወራት በፊት ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበረ፡፡ ቤተሰቦቹ እንደሚናገሩት ወደ ሱዳን ሲሄድ ለባለቤቱ የ3 ወር የቤት ኪራይ ከፍሎ ነበር የሄደው፡፡ ሁለቱ ልጆቹ የስምንትና የአራት ዓመት እድሜ ያላቸው ሲሆኑ ቤተሰቡ በችግር ላይ እንደሚገኝ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው መሐመድ ካሣ ማክሰኞ ምሸት ወደ አሜሪካ ልበር ስል ነግሮኝ ነበር፡፡ እስካሁን መርዶ የተረዱት የሰማዕታቱ ቤተሰቦች ወላጆች፣ እኅቶች ወይም ወንድሞች ሲሆኑ ብርሃኑ ግን ባለቤቱና ገና ክፉና ደግ ያልለዩት ሁለቱ ልጆቹ ናቸው የተረዱት፡፡

ፎቶ፡- ያሬድ ሹመቴ

ከሰማዕታቱ ቤተሰቦች መካከል ይበልጥ ትኩረት የሚፈልጉት እነዚህ ምንም የማያውቁ ሕጻናትና እናታቸው ናቸው፡፡ መማር፣ ተምሮም ማደግ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መኖሪያ ቤትና የትምህርት ቤት ክፍያ ይፈልጋሉ፡፡ እናታቸውንም በሥራ ማሠማራት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም የክፉዎቹ ሥራ ውጤት እንዳይኖረው እነዚህን ሁለት ሕጻናትና እናታቸው እንርዳ፡፡ ቤታቸው አቧሬ አድዋ ድልድይ አካባቢ ነው፡፡  

ጉዳዩን በሚገባ ለመረዳትና ርዳታውን ለማስተባበር መሐመድ ካሣን ብታነጋግሩት ያግዛችኋል፡፡ ስልኩ 0911602795 ነው፡፡
ዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ዋሽንግተን ዲሲ