ከገቢያቸው በላይ ሀብት ባካበቱ አማሳኞች እና ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሰረጉ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
ዛሬ፣ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሔደው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ወቅት ከመላው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት የተውጣጡ ከኹለት ሺሕ ያላነሱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች÷በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት እና በግልባጭ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በሀገረ ስብከቱ ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ያሳወቁት አምስት ዐበይት እና በርካታ ንዑሳን ነጥቦችን ያካተተው አቤቱታ አንኳር ሐሳቦች፤
- ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር ሚልዮን በላይ ልጆቿን አጥታለች፤ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብቶቿን በአግባቡ እያስተዳደረች ለተልእኮዋ ማስፈጸሚያ ማዋል ሲገባት ከብክነት፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተዝረከረከ አሠራር ጋራ ተያይዛ መጠቀሷ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡
- ፓትርያርኩ ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን እንደሚያጠፉና እንደሚዋጉ፣ የቤተ ክርስቲያንንም የቀድሞ ልዕልናዋንና ክብርዋን እንዲሚያስመልሱ በተደጋጋሚ የገለጡ ቢኾንም እስከ አኹን ምንም የታየ ለውጥ ባለመኖሩ አማሳኞች እየተጠናከሩ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች በመዋቅር እየገቡ፣ ምዝበራ እና የአስተዳደር በደል እየተባባሰ ነው፡፡
- በፓትርያርኩ ውሳኔ ከልዩ ጽ/ቤት በተጻፉ ደብዳቤዎች፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቅርቡ የተካሔደው የሥራ አስኪያጆች ምደባ እና ሹመት ሕገጋተ ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁ እና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚጋፉ ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያኗ ህልውና ሲባል መዋቅርን ባልተከተለና ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባልጠበቀ መልኩ የሚፈጸሙ አካሔዶች የሚታረሙበት መንገድ እንዲቀየስ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
- ሙስና እና ኑፋቄን የሚያጋልጡ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች÷ ‹‹ሽብርተኞች ናቸው፤ መንግሥትን ለመገልበጥ አሲረዋል›› በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች በኑፋቄ እና በሙስና በተዘፈቁ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና ሠራተኞች መዋከባቸው እጅግ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ከመንፈሳዊ አባትም የሚጠበቅ ባለመኾኑ በእኒኽ ሓላፊዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፡፡
- በዝርፊያ የተሰማሩ እና በአግባቡ ሥራቸውን የማይሠሩ አንዳንድ የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች እና ተቆጣጣሪዎች ያላቸው ቤት፣ መኪና እና አኗኗር ከሚያገኙት ደመወዝ/ገቢ/ ጋራ የማይመጣጠን በመኾኑ በአቋራጭ ያለአግባብ የበለጸጉ መኾናቸውን በማያሻማ መልኩ የሚያረጋግጥ ነው፤ በዘረፉት ብርም ከግብር አበሮቻቸው ጋራ ቤተ ክርስቲያንን ሰላም እየነሱ ነው፡፡ ያለአግባብ የተያዘ ምንጩ የማይታወቅ ንብረት ማካበት በሕግ የሚያስጠይቅ በመኾኑ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በመንግሥት በኩል ማስረጃ ተጠናክሮ ለፍርድ እንዲቀርቡ በአንድነት እንጠይቃለን፡፡
- በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን መካከል አንዳንዶቹ ባልታወቀ ምክንያት እንዲመለሱ መደረጋቸውና ስም በመቀየር መልሰው ሥራ የተቀጠሩ መኖራቸው በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ ጉዳያቸው በእንጥልል የቀሩት ግለ ሰዎች እና ቡድኖች ከዚኽ ቀደም ባቀረብነው ማስረጃ መሠረት እንዲኹም በሌሎች ቀሳጮች ላይ በቀጣይነት በምናቀርበው ማስረጃ መሠረት ጉዳያቸው ታይቶ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰድ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
- የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመኾናቸው፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን እና ቃለ ዐዋዲን የሚፃረሩ አፈጻጸሞች እየገዘፉ ለመጡት ችግሮች ዋነኛ መንሥኤ በመኾናቸው፣ አቤቱታዎች ተጠራቅመው አቅጣጫቸውን ስተው ወደአልተፈለገ ደረጃ ከማምራታቸው በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በትኩረት ተመልክተው እልባት የሚሰጥ ውሳኔ ያሳልፉ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የጥያቄውን እና የአቤቱታውን ሙሉ ይዘት ይከታተሉ

