በማኅበረ ቅዱሳን: ሰማዕትነት ለክርስትና በሚል ርእስ ነገ ውይይት ይካሔዳል

on martyrdomበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናት እና ምርምር ማእከል÷ ‹‹ሰማዕትነት ለክርስትና› በሚል ርእስ ነገ፣ ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 – 11፡00 ሰዓት በማኅበሩ የዋናው ማእከል ጽ/ቤት አዳራሽ ጥናታዊ ውይይት ያካሒዳል፡፡

የጥናታዊ ውይይት መርሐ ግብሩ፣ በየኹለት ወሩ (በዓመት ስድስት ጊዜ) በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ የሚዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የውይይት መድረክ አካል ቢኾንም የሊቢያ ኦርቶዶክሳውያን ሰማዕታትን በማሰብ እና የኦርቶዶክሳዊ ጽናት ምሳሌነታቸውን በመከተል ከትውልዱ ምን እንደሚጠበቅ አትኩሮ የሚካሔድ መኾኑ በዓይነቱ ልዩ እንደሚያደርገው ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

Yared Shumete picture of Kirkos mourningከነገው ጥናት አቅራቢዎች አንዱ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የኾኑት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ሲኾኑ በቂርቆስ የሊቢያ ሰማዕታት ቤተ ሰዎች መካከል በመገኘት በሰጡት የማጽናኛ ትምህርት÷ ሃይማኖታችንን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም በሚል የተሠዉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ‹‹የተግባር መምህሮቻችን›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ አክለውም ክርስትና ‹‹የመከራ ሃይማኖት›› መኾኑን የተናገሩት መመህሩ ‹‹መከራ የበለጠ ሊያስተሳስረን ይገባል›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

Medlote Tsidik, Dn Yaregal New Bookሌላው የጥናቱ አቅራቢ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የኾኑት ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ሲኾኑ በነገረ ሃይማኖት እና በዕቅበተ እምነት ላይ በአተኮሩ የጽሑፍ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን እና የቀደምት አበው ሊቃውንት ትምህርትን ሚዛን በማድረግ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላውያን ለሚያሰራጩት የስሕተት ትምህርት ምላሽ የሰጡበትን ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸውን ‹‹መድሎተ ጽድቅ›› በሚል ርእስ በዚኹ በሚያዝያ ወር ፳፻፯ ዓ.ም. ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ቤተ እምነቶች በዋናነት የሚለያት የመዳን ትምህርቷ መኾኑን የሚገልጹት ዲያቆን ያረጋል፣ የክርስትና ሃይማኖት የመዳን ሃይማኖት በመኾኑ የመዳን ትምህርት ከትምህርቶች ኹሉ ዋናውና የመጀመሪያው መኾኑን በመጽሐፋቸው አበክረው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መዳን በእምነት ብቻ››፣ ‹‹ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ አያስፈልግም››፣ ‹‹ካመንን በኋላ ኃጢአት ሠርተን ብንገኝ እንኳ አንኰነንም››… የሚለውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የፈጠራ ትምህርት ከተቀረጸበት ርእዮተዓለማዊ አስተሳሰቡ ጋራ ያፈለሱት ጸሐፊው፣ አንድ ሰው ለመዳን በእምነት ላይ ኾኖ ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ መሥራት እና መጋደል እንዳለበት፣ ተጋድሎው እና ክርስቲያናዊ ምግባሩም በእምነት የተቀበለውንና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በመሳተፍ የራሱ ያደረገውን የመዳን ጸጋ ጠብቆ እና አጽንቶ ወደ ሕይወት ለመግባት እንደሚያበቃው በስፋት አስረድተዋል፡፡

ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ቸርነት የተሰጠውን የመዳን ጸጋ በእምነት ሲቀበል፣ በመቀጠልም ይህን የመዳን ጸጋ በአማናዊ መንገድ የሚያገኝባቸውንና የራሱ የሚያደርግባቸውን ምስጢራት(ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቅዱስ ቁርባን) ሲፈጽም ነው፡፡ ከዚያም ይህን የተቀበለውን የመዳን ጸጋ ለመጠበቅና ወደ ሕይወት ለመግባት መጽናት እና መጋደል፣ እንደዚኹም ክርስቲያናዊ መልካም ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ኹል ጊዜ በመስቀል ላይ በመኾኑ ከብዙ ተጋድሎ ብዙዎችን ስትማርክ እንደኖረች ዲያቆን ያረጋል ያብራራሉ፡፡ የተጋድሎ መንገዱም ብዙ ነው፡፡