ነገ ህዝቡ በመስቀል አደባባይ በነቂስ ይወጣል
በነገው እለት በመስቀል አደባባይ የሚደረገው ሰልፍ ላይ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይወጣል ተብሎ ይገመታል። ከአዲስ አበባ እና አካባቢው ያለ ህዝብ በነቂስ እንደሚወጣ የሚደርሱን መረጃዎች ይተቁማሉ። ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ ሰማያዊ ፓርቲ እና አንድነት ፓርቲንን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግፈውታል። አላማው በኢትዮጵያውያን ላይ አይሲስ የፈጸመውን ግድያ ለመቃወም ነው ተብሏል።
በዛሬው እለት የታፈነው የአኢትዮጵያ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ሲያሰማ ውሏል። ሀዘኑንና ቁጭቱን ለመግለጽ የወጣውን የአዲስ አበባ ህዝብ የህወሃት ፌዴራል ፖሊስ ሲቀጠቅጠው እና የንጹሃኑን ደም ሲያፈስ እንደዋለም በምስል የተደገፉ መረጃዎች ደርሰውናል። በርካታ ሰልፈኞችም በጭነት መኪና እየተጫኑ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል። በሃዘን ላይ ሃዘን። በሃዘን የተጎዳ ወገኑን እየቀጠቀጠ ደም የሚያፈስ ስርዓት ከደቡብ አፍሪካው ዙሉ እና ከሊቢያው አይሲስ ታድያ በምን ይለያል?
በየሃገሩ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ሰቆቃ ገዢው ፓርቲ ያሳየውን ቸልተኛነት ለመቃወም ነበር ዛሬ ህዝቡ ነቅሎ አደባባይ የወጣው። ዱላው ያልበገረው ህዝብ፣
“ኢህአዴግ ሌባ ሌባ፣ ኢህአዴግ ሌባ ሌባ!”
“ይለያል ዘንድሮ የኢህአዴግ ኑሮ! ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ!.”
እያለ መፈክር ሲያሰማ ውሏል።
ከነገው ሰልፍ በተጨማሪ ሃሙስ እለት የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ የሚጠይቅ ወረቀትም እየተበተነ ነው። ይህ የአድማ ጥሪ በአሁኑ ሰዓት በከተማ ውስም መነጋገሪያ ሆኗል።
ወያኔዎቹ ግን አሁንም እያሾፉበት ይመስላል።
ኢትዮጵያዊው ፒኖኪዮ እየተባለ የሚጠራው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል።
‘አንዳንድ ወገኖች ደቡብ አፍሪቃ ላሉት ወገኖች እየሰጠን ያለውን ድጋፍ ሳስረዳ ስድብ መስሏቸው “ወያኔ አሉኝ”። ከጥቂት አመታት በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ በረከት ስምዖን ያለውን አስታወሱኝ “ሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን። ወያኔነት ልማት፣ ኩራትና ዴሞክራሲ ነው።”
ወያኔነት ልማት ሳይሆን ድህነት፣ ኩራት ሳይሆን ውርደት መሆኑን ለህዝቡ በደንብ አድርገው እያሳያዩት ነው። ያውም እየደጋገሙ። ለነገሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድህኖም ባለፈው የተናገሩት ነጭ ውሸት እንደተቀመጠ ነውና አፍ አለኝ ብለው በአደባባይ ባይናገሩ ይሻላል። ማፈርና መሸማቅ ይገባቸው ነበር። በማንም ዘመን ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ተዋርዶ አያውቅም። በማንም ዘመነ-መንግስትህዝቡ እንደዚህ በገፍ አልተሰደደም። ከገሃነም ከማይሻለው ህወሃት ስርዓት የተሻለ ሆኖ ያገኘው በበረሃ መውደቅ መሆኑን እያየን ነው። ይህ ደግሞ አሁን ድረስ በሙት መንፈስ የሚገዛው የባለራእዩ መሪያቸው ውጤት ነው።
ህዝቡ ሀዘኑን እንኳን እንዳይገልጽ የሚከለክል ዲሞክራሲ ያኮራኛል የሚል ሰው ጤናው ያጠራጥራል።
ቴድሮስ ቀጠሉ “እኔ ወያኔ ነኝ! ሁላችንም ወያኔ ነን! ይህን ችግር የሚፈታውም ወያኔነት ነው! በትክክለኛ የእድገትና የልማት አቅጣጫ ነው ያለነው።”
እንዲህማ እየቀለዱ አይዘልቁም። የታፈነ እና ተስፋ የሌለው ህዝብ እንደ ሱናሚ መነሳቱ አይቀሬ ነው።