አረመኔው ወገኖቻችንን አረደ
አረመኔው ወገኖቻችንን አረደ!!
አፈንዲ ሙተቂ
“ኢትዮጵያም እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች” የሚለውን ታዋቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ በብዙ ስፍራዎች ተለጥፎ አየዋለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የመንፈሳዊ መጽሔቶች የሽፋን ዘገባ ርዕስ ሆኖ ያጋጥመኛል፡፡ አንድ ሁለት ጊዜም የመጻሕፍት ርዕስ ሆኖ ያየሁት ይመስለኛል፡፡ እኔ ሙስሊም ነኝ፤ ነገር ግን ይህንን ጥቅስ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነበር የማውቀው፡፡ ሆኖም ጥቅሱ በመጽሐፉ ውስጥ የሚወክለውን እማሬያዊ ፍቺ እና በገቢርም ሊወክለው የሚችለውን አውዳዊ ፍቺ በትክክል አላውቅም፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ወንድሞቼ ቢያስረዱኝ ደስ ይለኛል፡፡ በሌላ በኩል ግን ጥቅሱን በውስጤ ይዤው በማደጌ የተለየ ስዕል ፈጥሮብኛል፡፡ ይህም ስዕል የተፈጠረብኝ ከቤታችን በቅርብ ርቀት (በሀምሳ ሜትር ላይ) ከሚገኘው “መጋላ ቆቦ” ከተሰኘ የጉልት ገበያ ላይ በየቀኑ ከማያቸው ክውኖች ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በዚህም መሰረት “ኢትዮጵያ” የልጆቿ አባት ሞቶባት ጨቅላዎቿን ለማሳደግ ስትል በየቀኑ በርበሬና ሽሮ አዘጋጅታ፣ እንጀራ ጋግራ፣ ዳቦ ደፍታ ለሽያጭ ወደ ጉልት ገበያ የምትወጣ አንዲት ባልቴት ትመሰላለች፡፡ ታዲያ ከእለታት በአንዱ ቀን የሆነ ጠብደል ወዛደር ቢጤ ሰው ከዚህች ባልቴት አራት እንጀራ ያህል ሊሸማምት ጎራ ይልና አስር ብር ይሳጣታል (አንዱ እንጀራ አንድ ብር የነበረበትን ዘመን አስታውሱ)፡፡ ባልቴቷ በቅድሚያ ገንዘቡን ተቀብላ ለአራት እንጀራ መግዣ የሚያስፈልገውን ያህል ከቆረጠችለት በኋላ መልሱን ትሰጠዋለች፡፡ ከዚያም አራት እንጀራ በፌስታል ቋጥራ ታስረክበዋለች፡፡
ሆኖም ሰውዬው እንጀራውን ተቀብሎ ሲያበቃ መንገዱን መቀጠሉን ትቶ ሴትዮዋን “መልስ ስጭኝ እንጂ” ይላታል፡፡ ባልቴቷ ግን “መልሱን አስቀድሜ ሰጥቼሃለሁ እኮ” በማለት ትመልሳለች፡፡ ዐይነ ደረቁ ሰውዬ “ሰጥቼሃለሁ! አከከከከከ…. ትቀልጃለች እንዴ…. ወይ ጉድ! በይ ቶሎ መልሱን ስጪኝ” ብሎ ያንባርቅባታል፡፡ ሴትዮዋ “እግዚአብሄርን! ሰጥቼሃለሁ የኔ ወንድም” በማለት ትምልለታለች፡፡ ይሁን እንጂ የሴትዮዋ ትህትና ሰውዬውን ወደ ህሊናው ሊመልሰው አልቻለም፡፡ ይልቅ ትዕቢቱ ከአፍንጫው ጫፍ ትወጣበትና ልቡን ታሞቀዋለች፡፡ ባልቴቷ “ኧረ በእግዚአብሄር!” እያለች ብትለምነው ሊሰማት ነው?…. የቀኝ እግሩን አንዴ አንስቶ እንጀራ ያመጣችበትን መሶብ ቢመታው በመሶብ ውስጥ የተነባበረው እንጀራ ሁሉ በአንዴ ተደፋ!! ሴትዮዋ በተፈጠረው ነገር ደንግጣ ክው አለች፡፡ ሰውዬው ግን በዚያ ብቻ ሳያበቃ የግራ እግሩን አነሳና ሽሮውን ድፍት አደረገው፡፡ ከዚያም “አንቺ ከይሲ!” ብሎ ከተፋባት በኋላ እየገላመጣት ወደ ማደሪያው ነጎደ፡፡ ይህ አጭበርባሪ ሰውዬ መልሱን አስቀድሞ ወስዶ ነው እንግዲህ ሴትዮዋን እንዲህ ጉድ ያደረጋት!!
ግርግሩን ያዩ ገበያተኞች በሴትዮዋ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ ግማሹ “ምጽጽጽ” እያለ ከንፈሩን መጠጠላት፡፡ የተቀረውም “ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሂጂና አመልክቺ” እያለ መከራት፡፡ ነገር ግን ባልቴቷ የምትናገርበት አቅም አልነበራትም፡፡ አንገቷን ቀና አድርጋ ሰማዩን በማየት እምባዋን እየዘራች ለአምላኳ አቤቱታዋን አቀረበች፡፡
ፈጣሪ ያቺን ደሃ ባልቴት አይሰማት ይሆን…..? ያለምንም ጥርጥር!! የፈለገውን ያህል ቢቆይም በእውነት መፍረዱ አይቀርም፡፡ አንድ የኦሮምኛ ተረትና ምሳሌ እንዲህ ይላል፡፡
Itti bokka malee roobni dhagaa hinjiisu (ዶፍ ቢወርድበት እንኳ ድንጋይ በዝናብ አይበሰብስም)
Numa turti malee Rabbi jazaa hindhiisu (ቢዘገይም እንኳ አምላክ መፍረዱ አይቀርም)
አዎን! “ኢትዮጵያ እጆቿን ትዘረጋለች” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ በውስጤ የሳልኩት ከላይ በገለጽኩት ሁናቴ ነው፡፡ ለኔ “ኢትዮጵያ” የተባለችው እመቤት ገንዘቧን ተጭበርብራ እንጀራዋና ሌሎች የጉልት ሸቀጦቿ በጉልበተኛ የተበተኑባት ምስኪን ባልቴት ዓይነት ሆና ትታየኛለች፡፡ ታዲያ ይህቺ ባልቴት የአንድ ዘመን ብቻ አይደለችም፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ በደለኞችን ወክላ ዕምባዋን እያዘራች ወደፈጣሪዋ የምትጮህ የሚስኪኖች ተምሳሌት ትሆናብኛለች!!
ከላይ የጻፍኩት የግል ፍካሬዬ በባልቴቷ ተምሳሌትነት የቀረበ ነው፡፡ የባልቴቷን ቦታ በህዝብ መተካቱ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ በዓለም ዙሪያ ያሉ ተበዳዮችን በመወከል በፈጣሪ ፊት ተደፍቶ የምንዱባንና የድኩማንን አቤቱታ ለፈጣሪ ማሰማት የሚችለው ህዝብ የትኛው ነው….? እኔ በበኩሌ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ባይ ነኝ፡፡ በየትኛውም እምነት ሆኖ ጸሎቱን ሲያደርስ በጣም የሚያምርበትና ከልቦናው የፈለቀ ሐቀኛ አቤቱታ ለፈጣሪ ማድረሱን የሚችል ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ያለ አይመስለኝም፡፡
ይህ ጸሎተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ የሰላም እንቅልፍ አልነበረውም፡፡ በየመን በሚካሄደው ጦርነት የተወጠሩ ወገኖቻችን ጉዳይ እንቅልፍ ሲነሳው ነበር፡፡ የየመኑ አበሳ ሳያባራ ከዚያ የባሰው መአት ከምድረ ደቡብ አፍሪቃ ተሰማ፡፡ “ለስራ አጥነታችንና ለችጋራችን መንስኤ የሆናችሁት እናንተ ናችሁ” የሚሉ ወጠምሻ የሰፈር ዱርዬዎች ገጀራና መዶሻ እየያዙ በስደት ወደዚያ የሄዱ ዜጎቻችንን ይወግሯቸው ገቡ፡፡ በዚህም የተነሳ ከሳምንቱ መግቢያ ጀምሮ ሰላም አልነበረንም፡፡ የወገኖቻችን ነገር ውጥር አድርጎ ይዞን እንደ እሳት እየለበለበን በቀጣይነት ስለሚወሰደው እርምጃ በማሰላሰል ላይ እያለን ነው እሁድ ሚያዚያ 11/2007 የመጣው፡፡
ጧት አራት ሰዓት ገደማ በሞባይል ስልኬ የአልጀዚራን ዌብ ሳይ በማገላበጥ ላይ ሳለሁ “ከ700 የማያንሱ የአፍሪቃ ስደተኞችን የያዘች መርከብ ከሊቢያ ተነስታ ጥቂት እንደተጓዘች ደብዛዋ ጠፋ፤ እስከ አሁን 28 ሰው ብቻ በህይወት ተገኝቷል” የሚል ዜና አነበብኩና ልቤ ተሰበረ፡፡ “ወይ ጌታዬ! የደቡብ አፍሪቃው አበሳ ሳያበቃ በዚህ ደገምከን እንዴ አምላኬ…? የባሰ አታመጣ እንጂ መቼስ ምን እናደርጋለን…?” ብዬ ከተንተባተብኩ በኋላ በዜናው ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ ማፈላለጉን ቀጠልኩ፡፡ ይህንንም ሳደርግ በዜናው ውስጥ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ስላልተጠቀሰ ብዙ ሰው በሚያየው የፌስቡክ አካውንቴ እና በዋናው ገጼ ላይ አስቀድሞ የመጣውን ዜና ከመለጠፍ ተቆጠብኩ፡፡ ነገር ግን ሌሎችም ጉዳዩን እንዲከታተሉት ለማድረግ ሲባል ወሬውን ማሳወቁ ጠቃሚ ስለመሰለኝ ብዙ ተከታይ በሌለው ሁለተኛው የፌስቡክ አካውንቴ ላይ የአልጀዚራን ርእሰ ወሬ ለጠፍኩ፡፡ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ገደማ “ያ የአፍሪቃዊያን ስደተኞች ወሬ እንዴት ሆነ” ብዬ የአል-ጀዚራን ድረ-ገጽ ስከፍት” በህልሜ እንኳ ጠብቄው የማላውቀው ልብ ሰባሪ ዜና ተለጥፎ ተገኘልኛ!!
“ISIL የሚባለው አክራሪ ቡድን በርካታ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያንን ጨፈጨፈ” ዝርዝሩን ስላነበባችሁት ወደዚያ አልገባም፡፡ ቢሆንም አረመኔው ቡድን ባደረሰው ጭፍጭፋ መሪር ሐዘን የደረሰባቸው ወገኖቻችንንና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪ ብርታቱን ይስጣችሁ/ይስጠን ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
——
(ከዚህ በላይ መቀጠል አልቻልኩም ወገኖቼ!! እስቲ ይንጋና ጉልበት ካገኘሁ አንዳንድ ነገሮች ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡ ስለዚህ የዛሬው ጽሑፌ ጎደሎ መስሎ ከታያችሁ ሌሎች ጓዶቻችን ባበረከቷቸው ጽሑፎች አካክሱት)፡፡
April 19, 2015
ከፌስ ቡክ የተገኘ