እግዜር ያተረፋት ነፍስ ምስክርነት

አሁን ከማልታ ባገኘሁት መረጃ በቀደም ከተሠዉት ወንድሞቻችን ጋር የነበረ ፣በእግዚአብሔር ቸርነት አምልጦ ትሪፖሊ የገባ ወንድም አግኝቼ ነበር፡፡
 

እርሱ እንደነገረኝ በአጅዛቢያና ቤንጋዚ መንገድ ላይ የአይሲስ አራጆች የሊቢያ መንግሥት ወታደሮችን ዩኒፎርም  ለብሰው በዚያ የሚያልፉትን ለመያዝ ይጠብቃሉ፡፡ በአካባቢው ወደ ትሪፖሊ የሚጓዙ መንገደኞችን ሲያገኙ ይይዛሉ፡፡ ሱዳኖችንና ሶማልያውያንን ሙስሊሞች ናቸው ብለው ስለሚያስቡ ወዲያው እንዲሄዱ ይለቋቸዋል፡፡ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያንን ግን ለብቻ ይይዛሉ፡፡ ከዚያም ሙስሊሞችን ለብቻ ክርስቲኖችን ለብቻ ያሰልፏቸዋል፡፡ በመቀጠልም ክርስቲያኖችን በኮንቴይነር ውስጥ ከትተው ወዳልታወቀ ሥፍራ ይወስዷቸዋል፡፡ ሙስሊሞችን ደግሞ ይለቋቸዋል፡፡

በቀደም ዕለት አይሲስ በባሕር ዳርቻ የሠዋቸው ክርስቲያኖች በሰውነታቸው ላይ የመስቀል ምልክት የነበረባቸውን መርጦ ነው፡፡ እነርሱን በተለየ ኮንቴይነር አስቀምጧቸው ነበር፡፡ ይኼንን መረጃ የነገረኝ ሰው ሊገደሉ ተመርጠው ከተለዩት ወገን ነበረ፡፡ ሌሎች በኮንቴይነር ያስቀመጣቸው ክርስቲያኖችም አሉ፡፡ ምናልባት ከዚህ የከፋ ዜና እንሰማ ይሆናል፡፡ አምላክ ይጠብቀን፡፡ አሁንም የአይሲስ አራጆች የመንግሥት ወታደሮችን ልብስ ለብሰው ሌሎች ስደተኞችን እየያዙ ነው፡፡

ይኼ መረጃንውን ያደረሰኝ ሰው ሊያመልጥ የቻለው ሌሎች ክርስቲያኖችን በጨለማ ወደ ኮንቴይነሩ ለማስገባት ኮንቴይነሩን በከፈቱበት ጊዜ ነው፡፡ የተወሰኑ ተያዦች አምልጠው ነበር፡፡ አንዳንዶች ተያዙ፡፡ ሦስቱ ግን አመለጡ፡፡ ሁለቱ የት እንደደረሱ አያውቅም፤ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ቸርነት አምልጦ ትሪፖሊ ገብቷል፡፡
እባካችሁ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ሰሞኑን ለመጓዝ የተነሡት ቢያንስ ለጊዜው ይታገሡ፡፡ ሱዳን ያሉትም ከሱዳን አይውጡ፡፡ መንገዱ በአይሲስ አራጆች ተይዟል፡፡ ለማታለልም የመንግሥት ወታደሮችን ልብስ ለብሰው ድንበር ጠባቂ ይመስላሉ፡፡
እግዚአብሔር በእጃቸው የተያዙትን እንዲታደግ እንጸልይ፡፡