የኢትዮጵያ መንግስት ነኝ ባዩ ቡድን ዛሬ ማምሻውን ባስተላለፈው ዜና ማገባደጃ ላይ ሊቢያ ውስጥ የተገደሉት ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መንግስት በካይሮ ግብጽ ከሚገኘው ኢምባሲ ለማረጋገጥ እየሞከርኩ ነው አለ
የኢትዮጵያ መንግስት ነኝ ባዩ ቡድን የሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ዛሬ ማምሻውን ባስተላለፈው ዜና ማገባደጃ ላይ ሊቢያ ውስጥ የተገደሉት ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መንግስት በካይሮ ግብጽ ከሚገኘው ኢምባሲ ለማረጋገጥ እየሞከርኩ ነው አለ።
የዜና አንባቢው ፕሮግራሙን የከፈተው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አንድ ፋብሪካ ሲጎበኝ በሚያሳይ ቅንብር ነው። ከሁለት ወራት በፊት የግብጽ ክርስቲያኖች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም የ7 ቀናት የሀዘን ጊዜ የግብጽ መንግስት አውጆ እንደነበር ይታወሳል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሀፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እንደገለፁት አሸባሪዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙትን ይህን መሰል የጭካኔ ተግባር ኢትዮጵያ በፅኑ የምታወግዘውን ያህል ቀደም ሲል ጀምሮ ዜጎቿንም ከሽብርና አሸባሪዎች ጥቃት ለመታደግ የሚያስችላትን አስፈላጊውን ዝግጁነት ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት በአስተማማኝ ማረጋገጥ ችላለች ፡፡
በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 11፣2007 የተለያዩ አለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ባሰራጩት ዘገባ አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ግድያ የፈፀመባቸው ስደተኞች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ቢገልፁም በግብፅ ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዳልሰጠም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ቡድኑ ለህልፈት የዳረጋቸው ዜጎች ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም ባይሆኑም መንግስት በንፁሃን ላይ የሚፈፀም ይህን መሰል አፀያፊና ዘግናኝ የሽብር ድርጊት አጥብቆ ይኮንናል ብለዋል፡፡
በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ከሆነም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡በመሆኑም ከሊቢያ ወደ ሀገር ተመላሽ ፈላጊ ስደተኞች በግብፅ ካይሮ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ግኑኝነት እንዲፈጥሩም የኢትዮጵያ መንግስት አሳስቧል ሲል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሀፈት ቤት ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በላው መግለጫ አመልክቷል፡፡
