ዕጣ የወጣባቸው ኮንደሚኒየሞች ምን ደረጃ ላይ ናቸው? ደላሎችና የቤት ገበያው Current status of recently awarded condominium homes, agents and the real state market

በ   [ሰንደቅ]

አስረኛው ዙር የኮንደሚኒየም ዕጣ ከወጣ ሳምንታት ተቆጠሩ። ቀደም ባሉት ጊዜያት በኮንደሚኒየም ቤቶች ላይ ዕጣ ከወጣ በኋላ ቤቶቹን ለባለእድለኞች በማስተላለፉ በኩል እሰከ ሁለት ዓመት የሚፈጅበት ሁኔታ ነበር። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ሲጠቀስ የነበረው ቤቶቹ ዕጣ ይወጣባቸው የነበረው ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ሳይሆን የግንባታቸው ሰማንያ በመቶ ብቻ ከደረሱ በኋላ ስለነበርና ቀሪውን ሃያ በመቶው ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የግንባታ ሳይቶቹ የመብራት፣ የውሃና መንገድን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች በቅንጅት መከናወን አለመቻላቸውም አንዱ ለርክክቡ መዘግየት ምክንያት ተደርጎ ሲጠቀስ የቆየ ጉዳይ ነው።

     የቤት ዕጣ እድለኞች ከቅድመ ክፍያ በኋላ ቀሪውን 80 በመቶ የባንክ እዳ ለመክፈል የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ (Grace Period) የሚሰጣቸው ሲሆን እስከዛሬ ባለው ሁኔታ እድለኞች በዚህ የእፎይታ ጊዜ ሲጠቀሙ አልታየም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ቤቶቹን በማጠናቀቁ ሂደት ላይ የሚፈጀው ጊዜ የእፎይታ ጊዜውን ሳይቀር የሚወስድ መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ ዕድለኞች ለሚኖሩበት ኪራይ ቤት ከመክፈል ባለፈ ቁልፉን ላልተረከቡት የኮንደሚኒየም ቤት የባንክ ዕዳ ክፍያ ለመጀመር የሚገደዱበት ሁኔታ ነበር። በዚህኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች ግን ቀደም ያለውን አሰራር በመለወጥ ከጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ውጪ ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው ያለቁ ቤቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎችንም በመስራት በሁለት ወራት ውስጥ ቁልፍ ለባለእድለኞች የሚሰጥበት ሁኔታም እንደሚኖር ቀደም ባሉት ጊዜያት ተመልክቷል።

     ይህን ሁኔታ በተመለከተ ቤቶቹ በእርግጥ ምን አይነት የማጠናቀቂያ ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመመልከት በየካ አባዶ ፕሮጀክት 13 እና ፕሮጀክት 14 ያሉ ኮንደሚኒየም ቤቶችን ተመልክተናል። ወደ የካ አባዶ ኮንደሚኒየም ቤቶች የሚወስዱ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ከመንገደኞቹ መካከል አንደኛው በመገናኛ ሲ ኤም ሲ ሃያት መስመር አቅጣጫ ሃያት አደባባይ ላይ ወደ ግራ በመዞር ሶስት ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝን ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ በመገናኛ ኮተቤ ባሉት ሁለት መስመሮችም ወደ ሳይቱ መድረስ ይቻላል። አሁን በስራ ላይ ካሉት መንገዶችም በተጨማሪ በእንግሊዝ ኢምባሲ በኩል ወደ ሳይቱ የሚወስድ ሌላ መንገድም በግንባታ ላይ ነው። ሳይቱ በኮተቤ መስመር በካራና በለገጣፎ መካከል ይገኛል። በትራንስፖርት በኩል ከዚያው አካባቢ የሚዞሩ ታክሲዎች እንደዚሁም ወደ ለገጣፎ የሚሄዱና የሚመለሱ የአውቶቡስና የታክሲ የትራንስፖርት አቅርቦቶች መኖራቸውን ተመልክተናል።

     በግንባታ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሃያት አደባባይ ላይ የሚያልቅ ሲሆን በየካ አባዶ አቅጣጫ መስፋፋት የሚችልበት እድል አለ። ከሀያት አደባባይ በየካ አባዶ ወደ ለገጣፎ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ መሀል ለመሀል ሁለት መንታ የባቡር መስመር ሊያዘረጋ በሚያስችል መልኩ ክፍት የሆነ ኮሪደር አለው። ይህም አሁን ያለውን የባቡር መስመር በቀጣይ ወደ አካባቢው መስፋፋት እንደሚችል አመላካች ነው።

     በሳይቱ በነበረን ቆይታ የቤቶቹ የግንባታ ማጠናቀቂያ ምን እንደሚመስል ለመመልከት ሞክረናል። ቤቶቹ አብዛኛው ግንባታቸው ተጠናቋል። የአንዳንዶቹ ብሎኮች መወጣጫ ደረጃ በስሚንቶ ብቻ ተገርፎ ገና የወለል ንጣፍ እንደሚቀረው ተመልክተናል። የደረጃ መወጣጫ ብረቶቹ በአንዳንዶቹ ብሎኮች የተገጠሙ ሲሆን በሌሎቹ ደግሞ ገና ናቸው። ከጥቂቶቹ በስተቀር የብዙዎቹ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶች ገና ሲራሚክስ መልበስ አልጀመሩም። የኤሌክትሪክ ስራው ተጠናቆ የሶኬትና የመብራት አሌክትሪክ ሽቦዎች በየቦታው ተንጠልጥለዋል። እያንዳንዱ ቤት የመብራት ቆጣሪ የገባለት ሲሆን ቆጣሪዎቹ የተተከሉት ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ ነው። ሁሉም ቆጣሪዎች ባለካርድ ናቸው። የአሌክትሪክ መስመር ለግንባታ ሥራ ሲያገለግል የነበረው ጊዚያዊ የኤሌክትሪክ መስመር ነው። በአካባቢው ያገኘናቸው ሠራተኞች ለቤቶቹ የሚያገለግለው ዋና የኤሌክትሪክ መስመር ተስቦ ገና ያልተገናኘ መሆኑን ገልፀውልናል።

     ውሃን በተመለከተ መስመሩ በሳይቱ የተዘረጋ ሲሆን ገና ያልተለቀቀ መሆኑን መረዳት ችለናል። በአካባቢው በስራ ላይ ያሉት ሰራተኞች ለውሃ አገልግሎት የሚውሉ መስመሮች በሳይቱ ሙሉ በሙሉ የተገጠመ መሆኑን ገልፀው፤ መስመሮቹን ለመፈተሸም ውሃ እየተለቀቀ የመስመር ፍተሻ ስራ መካሄድ ጀምሯል። ይህም ስራ ተጠናቆ ብዙም ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ውሃው ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

     መስኮቶቹ በማይካ ፍሬም መስታወት የተሰሩ ናቸው። እያንዳንዱ ቤት የውስጥ ለውስጥ ክፍሉ የተከፋፈለው በአግሮ ሰቶን ወይም ማግኒዢም ቦርድ ነው። ለኮንደሚኒየም ቤት ነዋሪዎቹ የሚያገለግሉ እርድ ማከናወኛን የመሰሉ የጋራ መጠቀሚያ ቤቶች ገና በጅምር ግንባታ ላይ ናቸው። የፍሳሽና የጎርፍ ውሃ ማስወገጃ ቱቦዎች ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።

     የግንባታ አካባቢን የማፅዳት ስራ (Ground Clerance) ገና አልተከናወነም። አፈር በየቦታው ተከምሯል። የተራረፉና ለተጨማሪ ስራ የሚያገለግሉ የግንባታ ግብአቶች በየቦታው ፈሰው ይታያሉ። አንዳንድ የኮንደሚኒየም ክፍሎች የሲሚንቶና የሌሎች የግንባታ ግብአቶች መጋዘንም ሆነው የሚያገለግሉበት ሁኔታ መኖሩንም ተመልክተናል። ብሎኮቹ ቀለም የተቀቡ ሲሆን መተላለፊያ በረንዳዎቹና የመወጣጫዎቹ ውስጠኛ ክፍሎች ግን ከሲሚንቶ ልስን ባለፈ ምንም አይነት ቀለም አልተቀቡም። ሁሉም ቤቶች የብረት በሮች ተገጥሞላቸዋል። በሮቹ ከወገብ በላይ መስታዎት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ገና አልተገጠመላቸውም። የየክፍሎቹ የውስጥ ለውስጥ በር መዝጊያ አልባ ነው።

የቤቶቹ አይነት 

     በሳይቱ ያሉት የኮንደሚኒየም ብሎኮች ባለ አራትና ባለስምንት ፎቆች ናቸው። ባለአራት ፎቆቹ ብሎኮች ሙሉ በሙሉ የደረጃ መወጣጫ ሲሆኑ ባለ ስምንት ፎቆቹ ደግሞ የደረጃ እንደዚሁም የሊፍት አገልግሎትንም ጭምር ያካተቱ ናቸው። ቀደም ያሉት አንዳንድ ኮንደሚኒየም ብሎኮች የውጨኛው ግድግዳ የውሀ ቀለም የተቀቡ በመሆናቸው ዝናብ ሲዘንብ ቀለማቸው እየለቀቀ ህንፃዎቹ ያለእድሜያቸው ያረጁ የሚመስል ገፅታን ተላብሰው የሚታዩበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን በየካ አባዶ ሁለቱም ሳይቶች ያሉት የኮንደሚኒየም ቤቶች ውጪኛ የህንፃ ክፍል የተቀባው ውሀ በማይገባውና በአየር ንብረት መለዋወጥ በቀላሉ በማይለቀው ኳርትዝ የቀለም አይነት ነው። የአብዛኞቹ ብሎኮች ቀለም ደማቅ ቡኒ ነው።

     የቤቶቹ ስፋት ወጥነት አይታይበትም። አንድ ብሎክ ያለው ባለሁለት መኝታ ቤት ከሌላኛው ብሎክ ተመሳሳይ ባለሁለት ክፍል አንድ አይነት ስፋት ላይኖረው ይችላል። አንዳንዶቹ መኝታ ቤቶች ጠበብ ብለው ወጥቤቱ ወይንም ሳሎኑ ሰፋ ሊል ይችላል። በአንዳንድ ብሎኮች ደግሞ ከሌሎች በተሻለ በአንፃራዊነት ሰፋ ያሉ የመኝታ ክፍሎች ጠበብ ያለ የሳሎን ክፍል ያለበት ሁኔታም አለ። ስቱዲዮና ባለአንድ ክፍሎች ከሌሎች ጋር የሚጋሩት አንድ መተላለፊያ የጋራ በረንዳ ብቻ ነው ያላቸው። ባለሁለትና ሶስት ክፍሎቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አንድ የጋራ በረንዳ እንደዚሁም በጀርባ በአንደኛው መኝታ ቤት በኩል የየራሳቸው በረንዳ (Balcony) እንዲኖራቸው ተደርጓል። የቤቶቹን ስፋት በተመለከተ በቤቶች ኤጀንሲ በኩል የተለቀቁ መረጃዎች እንዳሉ የሚታወስ ነው። ባአለአንድ ክፍል በአማካኝ ከ48 እሰከ 51 ካሬ ሜትር ስፋት ያለቸው መሆኑ ቀደም ሲል በተሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ተመልክቷል። ይህ የስፋት መጠን ግድግዳው ያረፈበትን፣ወሽመጥ የኮሪደር ቦታዎችን እንደዚሁም የጋራ መተላለፊያ በረንዳዎችን ጭምር የሚያካትት በመሆኑ ቤቶቹ ውስጥ ለውስጥ ሲለኩ በአማካኝ አላቸው ከተባለው የስፋት መጠን ያነሱ ናቸው። ይህም በመሆኑ የቤቶቹ የውስጥ ለውስጥ ስፋት ወደ 38 ካሬ አካባቢ ዝቅ ያለ ነው። ወደ 36 ካሬ ሜትር አጠቃላይ ስፋት ያላቸውን ባለአንድ መኝታ ክፍሎችንም ተመልክተናል። የባሁለት ክፍል ቤቶች የተቀመጠላቸው አማካኝ የስፋት መጠን 72 ካሬ ሜትር አካባቢ ሲሆን በውስጥ ለውስጥ ልኬት የስፋታቸው መጠን በአማካኝ ከ 63 እስከ 65 ካሬ ሜትር የሚደርስ መሆኑን ተመልክተናል።

 

ደላሎችና የቤት ገበያው

    

     ቤት ማግኘት የበርካቶች ህልምና ምኞት ነው። ሆኖም በተለይ ቅድመ ክፍያውን በመክፈሉ ረገድ የበርካቶች ፈተና ሆኗል። ለዚህ ችግር መፍትሄ አለን የሚሉ ደላሎችን በአካባቢው አግኝተናል። ቤት እንደደረሰው አውቆ ወደ ሳይቱ ጎራ የሚል ሰው በየመግቢያው ላይ መጀመሪያ የሚያጋጥሙት ደላሎች ናቸው። ደላሎቹ ቢዝነስ ካርዶችን አሳትመው ቤት ደርሷቸው ቤታቸውን ለማየት ለሚመጡ ሰዎች በስፋት ያድላሉ። ደላሎቹ ቤቶቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያከራዩ መሆናቸውን፣የሽያጭ ስራንም መስራት እንደሚችሉና ቅድመ ክፍያንም መክፈል ለማይችሉ ከግለሰቦቹ ጋር በመደራደር የተለያዩ መፍትሄዎችን እንደሚያዘጋጁ ገልፀውልናል።

     የቤቶቹ 80 በመቶ ባለቤት ባንክ ነው። አንድ ግለሰብ ዕጣ ከወጣለት በኋላ ቤቶቹን ለመረከብ የሃያ በመቶ ቅድመ ክፍያ ነው የሚጠበቅበት። በባለቤትነት ድርሻ ረገድ በዚህ ደረጃ የመንግስት ድርሻ የጎላ ቢሆንም ባለ ሀያ በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ግለሰብ ቤቱን እንደተረከበ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ የሚያስተላልፍበት ሁኔታ አለ። አንዳንዶቹ ሽያጮች የሚከናወኑት ገና ቅድመ ክፍያው ሳይከናወን ነው።

     ቀደም ባሉት ጊዜያት “ቅድመ ክፍያ የመክፈል አቅም የለኝም” ያለ ሰው ቤቶቹን ቀርቦ የማይረከብ ሲሆን፤ አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። የቤቱ ዕጣ ወጥቶላቸው ቅድመ ክፍያ የሌላቸው ሰዎች በደላሎች አግባቢነት ቤቶቹን በመሸጥ ቅድመ ክፍያውን ከፍለው ከመንግስት ጋር ውል ከተዋዋሉ በኋላ የተረፈውን ገንዘብ የሚጠቀሙበት መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ነዋሪዎች ቅድመ ክፍያን መክፈል ችለው በኋላ ቤቶቹን መሸጥ ቢፈልጉ የሻጮች የመደራደር አቅም ከፍ እንደሚል የታወቀ ነው። በአንድ መልኩ በአካባቢው ሰው መኖር ስለሚጀምር፤ ይህ በራሱ የአካባቢውን እሴት ከፍ የሚያደርገው ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ እንደ ቅድመ ክፍያ ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለክፍያ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ነው።

     ለቅድመ ክፍያው የተሰጠው ጊዜ ሁለት ወራት በመሆናቸው ደላሎች አቅም የሌላቸውን ሰዎች በማግባባት አጋጣሚውን የመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መረዳት ችለናል። የሁለት ወር የቅድመ ክፍያ የጊዜ ገደብ እንዳለው እያወቀ በቂ ገንዘብ የሌለው ሰው እድሉን ላለማምከን ቤቱን ለመሸጥ ሲነሳ ዋጋን የመደራደር አቅሙ አነስተኛ መሆኑን ደላሎች በሚገባ ስለሚያውቁ፤ ቤቶቹ ዕጣ እንደወጣባቸው ግዢ ለመፈፀም የሚያደርጉት ርብርብ ከፍተኛ ነው። ቤቶቹን ከአምስት አመታት በፊት በሽያጭ ማስተላለፍ በህግ የተከለከለ በመሆኑ የሽያጭና የግዢ ውሉ ህጋዊ ሽፋን የለውም።    

Subscribe to Sodere YouTube channel. የዩቲዩብ ቻናልችን ደንበኛ ለመሆን ይመዝገቡ።

EBS Special Fasika Full Program with Teddy Afro’s family.

Some videos from Sodere YouTube channel
iPhone users say Goodbye to square boxes, welcome Amharic fonts ሶደሬ ዜና
Ethiopian Movie Sere Mizewa Full
Ethiopian Comedy Ber Lay Dereje and Habte Golden Times
Ethiopian Movie Kemaebelu Wedeh


Sodere Monthly Headline News April 12, 2015
Ethiopian Movie Yetekatelut Getsoch Full

Receive Ethiopian News, Movies and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።