የሳይንቲስቱ ልጅ ጥያቄ

ባለፈው እሑድ፣ የትንሣኤ ዕለት ማልዳ ነው ከዕንቅልፏ የተነሣቺው፡፡ እናቷ ቤተ ክርስቲያን አድራ፣ አባቷ ደግሞ ሌሊት ከውጭ ሀገር ገብቶ ደክሟቸው እንደተኙ አልተነሡም፡፡ እርሷም በጠዋት የተነሣቺው ጓደኛዋ አደራ ስላለቻት ነው፡፡ ‹‹የቴሌቭዥን የትንሣኤ ፕሮግራም የተቀረጸው እኛ ቤት ነው›› ብላ አጓጉታታለቺ፡፡ የተነሣቺው ጓደኛዋን በቴሌቭዥን ለማየት ስትል ነው፡፡ ደግሞ ‹ዘፈን ምናምን አቅርቤያለሁ› ብላታለቺ፡፡ የጓደኛዋ አባት ‹ፍቅር እዚህም እዚያም›፣ ‹ትሄጅብኛለሽ› እና ‹ፍቅር በኪችን ውስጥ› የተሰኙ ሦስት አስቂኝ የፍቅር ፊልሞች ላይ የሠራ ‹ታዋቂ አርቲስት› ነው፡፡ ጓደኛዋ እንደነገረቻት ከሆነ የበዓሉ ፕሮግራም እነርሱ ቤት ሲቀረጽ የቀረ አርቲስት የለም፡፡ በዓሉ ራሱ ሕዝቡን ሊያዝናና ስለማይችል ‹ዘና እንዲያደርጉት› ተብሎ ቀልደኞቹ ሁሉ እነርሱ ቤት መጥተው ነበር፡፡ 

ከቀረፃው ማግሥት ጓደኛዋ ትምህርት ቤት ስትመጣ የታዋቂ አርቲስቶችን ፊርማ በየደብተሯ ሰብስባ መጥታ ጓደኞቿን ሁሉ ስታስቀናቸው ነበር፡፡ በርግጥ ክፍል ውስጥ እርሷና ጓደኞቿ ትምህርታቸውን ረስተው የአርቲስቶችን ፊርማ ሲያደንቁ ያዩዋቸው መምህራቸው እንደ መገሰጽ ቢያደርጉም፣ እንደመስማት ያላቸው ተማሪ ግን አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው ታዋቂ አይደሉማ፡፡ ደግሞ መምህር ከመቼ ወዲህ ነው ታዋቂ የሚሆነው፡፡ ይኼው ስንቱ አርብቶ አደርና አርሶ አደር ሲሸለም መምህር መቼ ተሸልሞ ያውቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙዎችን ተማሪዎች ያናደዳቸው ‹‹የዘፈነም፣ የተወነም፣ ፊልም የሠራም፣ ማስታወቂያ የሠራም አርቲስት አይባልም›› ያሉት ነገር ነው፡፡ ‹‹አርቲስት የሚለው ስም ለሰዓሊዎች የሚሰጥ ስም ነው፡፡  ያውም ስካልፕቸርና ፔይንቲንግ ለሚሠሩት ብቻ፡፡ እርሱም ቢሆን እንደ ደጃዝማችና ግራ አዝማች ማዕረግ ሳይሆን የሞያ መጠሪያ ነው፡፡ እስኪ አሁን አርቲስት ማይክል ጃክሰን፣ አርቲስት ቢዮንሴ ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ሰው ማዕረግ የሚያበዛው ስሙ ብቻውን ለመቆም ዐቅም ስለሚያጣ ነው፡፡ እስኪ ተመልከቱ፡፡ ዳቪንቼ፣ ሼክስፒር፣ ሞዛርት፣ ፒካሶ የሚለው ስምኮ ብቻውን የሚቆም ነው፡፡ ዕዝል ቅጽል አያስፈልገውም፡፡›› ያሉትን ነገር ተማሪዎቻቸው ‹‹እርሳቸው ከቴሌቭዥን ሊበልጡ ነው እንዴ›› ብለው ሙድ ያዙባቸው፡፡
ለነገሩ እርሳቸውም አብዝተውታል፡፡ ‹አርሶ አደርና አርብቶ አደር፣ ሠልጣኝና የትራፊክ ፖሊስ፣ ታራሚና ፍርደኛ፣ ጋዜጠኛና ጎዳና ተዳዳሪ ማዕረግ ሆነው ከስም በፊት በሚቀጸሉባት ሀገር ‹አርቲስት› ማዕረግ አይደለም ብለው ተማሪን ማሸበር በአሸባሪነት የሚያስከስስ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ እንዲያውም ኢቲቪ ቢሰማቸው ‹በአሸባሪነት ሊያስከስስ ይገባል ሲሉ አንዳንድ የሕግ ምሁራን አስገነዘቡ› ብሎ ለዜና ጥብስ ያውላቸው ነበር፡፡
እርሷ ሶፋ ወንበር ላይ ተቀምጣ ይኼንን ሁሉ ስታስብ ጓደኛዋ በቴሌ ቭዥን ዘገየች፡፡ እስኪጀመር ድረስ ያቺ የ12 ዓመት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ማሰቧን ቀጠለች፡፡ ‹‹ቆይ ግን አባዬ ምንድን ነው? አንድም ቀንኮ በቴሌቭዥን ታይቶ አያውቅም፡፡ ይኼው ኤልዳና እንኳን ስንት ጊዜ በቲቪ ልትታዪ ነው፡፡ አባዬ ግን ዶክተር ምናምን ከሚሆን አርቲስት ቢሆን ነበር ጥሩ፡፡ እርሱ ዶክተር ሆኖ ምንም አልጠቀመንም፡፡ አንዴ አሜሪካ አንዴ ጃፓን፣ አንዴ ጀርመን ለወርክ ሾፕ መሮጥ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ የኤልዳናም አባት ውጭ ይኼዳል፡፡ ግን እርሱ ሲሄድም ሲመጣም በሚዲያ ይነገርለታል፡፡ ሊሄድ ነው፣ እየሄደ ነው፣ ሊደርስ ነው፣ ደረሰ ይባልለታል፡፡ የኔን አባት መሄድና መምጣት ግን እኛና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡
ደግሞ የኤልዳና አባት ውጭ ሲሄድ ሰው ይከበዋል፣ ጉርድ ቀሚስ ያደረጉ ሴቶች፣ ቁጥርጥር የተሠሩ ወንዶች፣ አጅበውት ፎቶ ይነሣሉ፡፡ የኔ አባት ግን ፎቶዎቹን ሁሉ ሳይ ወይ ከራሰ በራ ሰው ጋር ወይ ድክምክም ካሉ ሴቶች ጋር ነው የሚነሣው፡፡ ደግሞኮ የኤልዳና አባት ሁልጊዜ የአበባ ጉንጉን ሲቀበል ነው የሚታየው፡፡ የኔ አባት ግን ሯጭ ይመስል ሜዳልያ ሲቀበል ነው የምናየው፡፡ ኤልዳና ቪዲዮውን በስልኳ ስታሳየን ሰው ሁሉ ኡኡ እያለ አዳራሽ ውስጥ ለአባቷ ይጨፍርለታል፡፡ የኔ አባት ግን አንድ ጠረጴዛ ነገር አጠገብ ይቆማል፤ የሆነ ነገር በፓወር ፖይንት ያሳያል፤ አንድ ጊዜ ይጨበጨብለታል፡፡ በቃ፡፡ አንድም የሚጨፍር ሰው አይታይም፡፡ አባዬ ግን ምንድን ነው?
ቆይ ግን እኛ ቤት ኢቲቪዎች የማይመጡት ለምንድን ነው? አባቴ አርቲስት ስላልሆነ ነው አይደል፡፡ የኔ አባትኮ እንኳን ለፋሲካ ለአርሂቡ ቀርቦ አያውቅም፡፡ እውነታቸው ነው፡፡ በአርሂቡኮ አርቲስቶች ሲቀርቡ ‹እንትናዬ አድናቂህ ነኝ፣ እወድሃለሁ፤ ቀጣዩ አልበምህ መቼ ነው የሚወጣው? ምን ፊልም ልትሠራልን ነው?›› የሚል ሰው ይደውልላቸዋል፡፡ አሁን አባዬ አርሂቡ ላይ ቢቀርብ ምን ሊባል ነው? ምን ተብሎ ሊጠየቅ ነው? ደግሞ ማንም አድናቂ አያገኝም፡፡ አልበም የለው፤ ፊልም የለው፣ ሰዎች በምን ያውቁታል፡፡
አባዬ ግን አርቲስት መሆን ነበረበት፡፡ ዶክተርነት ምን ያደርግለታል፡፡ አርቲስት ቢሆን ኖሮ በኋላ ሲያረጅ ‹የክብር ዶክትሬት› ተብሎ ይሰጠው ነበር፡፡ ‹የክብር አርቲስት› ብሎ ግን ማንም አሁን አይሰጠውም፡፡ ዶክተርነት ይደረስበታል፡፡ አርቲስትነት ግን አይደረስበትም፡፡ እንዲያውም እነርሱ ሲጠሩ ‹ክቡር ዶክተር› ነው የሚባሉት የኔ አባት ግን ‹ዶክተር› ብቻ ነው፡፡
እርሷ ይህንን ስታወጣና ስታወርድ የቴሌቭዥኑ ፕሮግራም ጀመረ፡፡ ጋዜጠኛውም ‹እያዝናናን እናስተምራለን› ብሎ የጓደኛዋን ቤት አሳየ፡፡ ምንም እንኳን የተቀረጸው በጾም ጊዜ ቢሆን ዶሮው፣ በጉ፣ ክትፎው፣ ቅቤው፣ ዕንቁላሉ ይታያል፡፡ ለነገሩ እንደ ኢቲቪ አቆጣጠር ጾሙ አንድ ሳምንት ሲቀረው ያልቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ቀረጻ ይቻላል፡፡ ጓደኛዋን አየቻት፡፡ ቤታቸው እየታየ ነው፡፡
እየሮጠች አባቷን ቀሰቀሰቺው፡፡
‹‹ጓደኛዬ በቴሌቭዥን እየታየች ነው›› ስትለው ድካሙ ባይለቀውም እርሷን ለማስደሰት ተነሥቶ ዓይኑን እያሸ ወደ ሳሎን መጣ፡፡ ‹እያት ኤልዳናን› አለቺው፡፡ ኤልዳና እየተጠየቀቺ ነው፡፡ ቃለ መጠይቁ ሲያልቅ ‹አባዬ አንተ መቼ ነው በቲቪ የምትቀርበው› አለቺው ልጁ፡፡
‹‹ሚዲያችን ከታዋቂ ይልቅ ለዐዋቂ ቦታ ሲኖረው›› አላት አባቷ፡፡
‹‹አንተ ግን ለምን ታዋቂ አልሆንክም››
‹‹ልጄ እኔኮ ታዋቂ ነኝ፡፡ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ግን አያውቁኝም፡፡ የቢቢሲ፣ የሲኤንኤን፣ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ያውቁኛል፡፡ እኔ አንድ ነገር ስለ ግብርና ከተናገርኩ ወይም ከጻፍኩ ያ ዜና ይሆናል፡፡ እዚህ አገር ግን ዕውቀት ዜና አይሆንም ልጄ፡፡ እዚህ ሀገር ዜና የሚሆነው ፖለቲካና ቀልድ ነው፡፡››
‹‹እሺ ለምን አርሂቡ ላይ አትቀርብም››
‹‹ያማ ጋዜጠኛውን ማሰቃየት ነው ልጄ››
‹‹ለምን ይሰቃያል?››
‹‹ምን ይጠይቀኛል? ጥናታዊ ጽሑፎቼን ማንበብ ሊኖርበት ነው፡፡ ምርምሮቼን መቃኘት ሊኖርበት ነው፡፡ ስለ እኔ የተሰጡ የሌሎች ሳይንቲስቶችን ምስክርነት ማገላበጥ ሊኖርበት ነው፡፡ ይሰቃያል ልጄ፡፡ ቀልድ የለመደን ሰው ዕውቀት ያሰቃየዋል፡፡በቀለላሉ የመጀመሪያ አልበምህ መቼ አወጣኸው? የመጀመሪያው ፊልምህ ምን ነበር? ገጠመኝህ ምንድን ነው? እያለ ሰዓቱን መሙላት ሲችል ምን በወጣው ሳይንቲስ አቅርቦ ይሰቃያል፡፡ ጋዜጠኞቹ መዘጋጀት ስለማይችሉም ስለማይፈልጉም አይደል እንዴ ‹እስኪ ራስሽን ለአድማጮች አስተዋውቂ› የሚሉሽ፡፡ ይኼኮ የጋዜጠኛው ሥራ ነበር፡፡ አንብቦ፣ ፕሮፋይል ሠርቶ ቢመጣ ኖሮ እንዲህ አይልም፡፡ ደግሞም አለቆቹም ላይወዱለት ይችላሉ፡፡ ዕውቀት የመለወጥ ኃይል አለው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንዲዝናና እንጂ እንዲለወጥ አይፈለግም፡፡››
‹‹ተዪው እኔን፡፡ አንድ ገበሬ በዓል እንዴት ነው የሚያከብረው? ድንበር ላይ ባሉ ወታደሮች ዘንድ እንዴት ይከበራል? ተረኛ ሆነው ሆስፒታል ወይም እሳት አደጋ መከላከያ ውስጥ ባሉ ባለሞያዎች ዘንድ ፋሲካ ምን ዓይነት በዓል ነው? በዕለቱ አየር ላይ በሚሆኑ የአውሮፕላን አብራሪዎችና አስተናጋጆች፣ መርከብ ላይ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን፣ ሆስፒታል በተኙ ሕሙማን፣ በዓል እንዴት ይከበራል? የሚለውን እንኳን መች ያሳዩናል፡፡ ለምን ይመስልሻል?
‹‹እነርሱ ታድያ አርቲስት ናቸው እንዴ?››
››ልጄ የኑሮ አርቱማ ያለው እዚያ ውስጥ ነበር፡፡ የኛነታችንን ሌላ ገጽታ የምናየውማ እዚያ ውስጥ ነበር፡፡ ግን ይኼ ማሰብ ይጠይቃል፤ መመራመርን፣ ማንበብን፣ መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ ማሰብ፣ ማንበብና መዘጋጀት ደግሞ እዚያ ቤት የሚወደዱ አይመስሉኝም››
‹‹እሺ ታድያ መቼ ነው የኛ ቤት በቴሌቭዥን የሚቀርበው?››
‹‹ወይ እኔ መቀለድ፣ ወይ እነርሱ ማወቅ ሲጀምሩ››