የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን አረፉ

ከኢትዮጵያ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነት የነበራቸው ዕውቁ አሜሪካዊው የፖለቲካ ሶስዮሎጂስት ፕሮፌሰር ዶናልድ ናታን ሌቪን፣ መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. አረፉ፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ስለኢትዮጵያ በጻፏቸው “Greater Ethiopia” (‹ታላቋ ኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ ወደ አማርኛ መልሰውታል)፣ “Wax and Gold” እና “Interpreting Ethiopia” በተሰኙ መጽሐፎቻቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ለአምስት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረጉ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው ‹‹ጋሽ ሊበን›› ወይም ‹‹ሊበን ገብሬ ኢትዮጵያ›› የሚባሉት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ በዓለም ዘንድ ታዋቂ ያደረጉዋቸውን ሥራዎቻቸውን የሠሩበትን የቺጋጎ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ1962 ከመቀላቀላቸው በፊት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በ1996 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ በሠሯቸው ጥልቅ ሥራዎች የተነሳ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ ሴኔትና የአሜሪካ የሰላም ጓድ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በ84 ዓመታቸው ያረፉት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በሶስዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በዓለም ከሚጠቀሱ ተቀዳሚ ምሁራን አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ ስለኢትዮጵያ የጻፏቸው ሥራዎች ጥልቅና ለኅብረ ብሔራዊ የኢትዮጵያ ጥናት በር ከፋች እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በሽግግሩ ዘመን በመንግሥት ላይ የሚያቀርቧቸው የሰላ ትችቶች ከኢሕአዴግ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በአሉታዊ ጎኑ እንዲጀመር ቢያደርገውም፣ በሒደት ከተለያዩ ባለሥልጣናት ጋር በፈጠሩት ግንኙነት በተለይም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው ተከታታይነት የነበረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደኋላ ላይ የተለሳለሰ አቋም ማሳየታቸውን ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና እስከመጨረሻው የሕይወት ዘመናቸው ድረስ በኢትዮጵያ ላይ የጻፏቸው ሥራዎች ምክንያታዊና ሞጋች መሆናቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን የአንድ ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡

The post የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን አረፉ appeared first on ሳተናው .