በታንዛኒያ በ47 ኢትዮጵያውያን ግድያ የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ተጻፈ በ ታምሩ ጽጌ
-ከ30 ሺሕ በላይ ዜጐችን በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወራቸው ተጠቁሟል
በኬንያ በማድረግ በታንዛኒያ በማቆራረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ መንገድ በኮንቴይነር ውስጥ አሽገው ሲያስተላልፉ፣ ታንዛኒያ ውስጥ እንዳሉ ሕይወታቸው ላለፉት 47 ኢትዮጵያውያን ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ሁለት ኢትዮጵያዊያት ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡
አስካለ ዴዴሳ ዴዴቦ በቅጽል ስሟ ‹‹ቤቲ›› እና ሰሚራ ሐሰን ዓሊ የተባሉት ተጠርጣሪዎች፣ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በኬንያ የፀጥታ ኃይሎችና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ልዩ ክትትል፣ ኬንያ ውስጥ ተይዘው በኢንተር ፖል አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
በተለይ አስካለ (ቤቲ) የተባለችው ተጠርጣሪ፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሥራ ላይ በመሰማራት ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጐችን ወደተለያዩ አገሮች ከማሸጋገሯም በተጨማሪ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና እንግልት ምክንያት መሆኗ ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ከሚንቀሳቀሱባቸው አገሮች መካከል፣ በኬንያ ወደ ታንዛኒያ ከዚያም ወደ ደቡብ አፍሪካ በዋናነት የሚጠቀሰው መንገድ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት፣ በፌዴራል ፖሊስ የኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ግርማይ ካህሣይ ናቸው፡፡
‹‹ራሳቸውን ከደበቁና በምሥራቅ አፍሪካ ሲፈለጉ ከነበሩት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሥራ ውስጥ ከተሰማሩ ተጠርጣሪዎች አስካለ ዴዴሳ አንዷ ናት፤›› ያሉት ኮማንደር ግርማይ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በማቀነባበር፣ በመፈጸምና ኔትወርኩን በመምራት የታወቀች መሆኗ ተገልጾ፣ በሁለቱ አገሮች የተቀናጀ አሠራርና ልዩ ክትትል በቁጥጥር ሥር ውላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በእስር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
በተለይ በታንዛኒያ በኮንቴይነር ውስጥ እንዳሉ ሕይወታቸው ላለፈ 47 ሰዎች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ስቃይ ለደረሰባቸው 92 ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ ተጠያቂ እንደሆነችም እየተነገረ ነው፡፡
የአስካለ ዴዴሳ አጋር መሆኗ የተገለጸውና 138 ሰዎችን በማዘዋወር ላይ እንዳለች በቁጥጥር ሥር ውላለች የተባለችው ተጠርጣሪ ሰሚራ ሐሰንም፣ ከተጠርጣሪ አስካለ ጋር ፍርድ ቤት ቀርባ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባት በእስር ላይ ትገኛለች፡፡ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በተለይ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶችን በመመልመልና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጐች ላይ ከፍተኛ ችግር ማድረሳቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎች የወንጀል መረቦችን ለመበጣጠስ ከአካባቢ አገሮችና ዓለም አቀፍ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር፣ ክትትሏን እንደምትቀጥል ኮማንደር ግርማይ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢንተር ፖል ዋና ጽሕፈት ቤትን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ለማድረግም እየተንቀሳቀሰች መሆኗንና የሚሳካ ከሆነም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ተደራሽነት ከፍ ያለ እንደሚያደርገውም አክለዋል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ ራሳቸው ጭምር በተለያዩ ምክንያቶች ችግር የደረሰባቸው ሁሉ፣ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ቀርበው ሪፖርት በማድረግ የፍትሕ ሒደቱን እንዲያግዙ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የተደራጁ ወንጀሎች ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር በለጠ ጌታቸው ጥሪ አድርገዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
The post በታንዛኒያ በ47 ኢትዮጵያውያን ግድያ የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀረቡ appeared first on ሳተናው .